የባህር በር ጉዳይ በአንድ ሀገር የእድገት ስትራቴጂ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጠዋል። በተለይም ባለንበት ዘመን የባህር በር ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አንደምታ አኳያ ባህር በር አልባ ለሆኑ ሀገራት ይዋል ይደር እንጂ ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑ አይቀርም።
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ላይ ላሉ ሀገራት ፣ የጀመሩትን ልማት በማስቀጠል የሕዝቦቻቸውን የእለት ተእለት ሕይወት ለማቅለልም ሆነ የመልማት ፍላጎታቸውን ተጨባጭ ለማድረግ የባህር በር ጉዳይ ወሳኝም፣ የሕልውና ጉዳይም ነው።
ይሄን መነሻ በማድረግም ኢትዮጵያ ያቀረበችው እና በዲፕሎማሲ መንገድ ተጉዛ ምላሽ ያገኘችበት የባህር በር ጥያቄ ታዲያ፤ ከሞራልም ሆነ ከአለም አቀፍ ህግ አኳያ ተገቢነት ያለው በአግባቡ እና በልኩ ሊተረጎም የሚገባው የመብት ጥያቄ ነው። ዓለም አቀፉ ህብረተሰብም ጥያቄውን በኃላፊነት መንፈስ ተቀብሎ ማስተናገድ የሚያስችል በቂ ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅበታል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀደሙት ዘመናት ከአንድም በላይ የሁለት እና ሶስት ወደቦች ባለቤት በሆነችባቸው የታሪክ ምእራፎች ውስጥ አልፋለች። በእነዚህ የታሪክ ምእራፎች ውስጥ የባህር በር ባለቤትነቷ የነበረው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም ሆነ በማህበረሰቡ ውስጥ ፈጥሮት የነበረው የስነልቦና ከፍታ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።
ይህችው ሀገር በሌላ የታሪክ አጋጣሚ ያሏትን የባህር በሮች በሙሉ አጥታ ፤የገቢና ወጪ ንግዷን እንኳን ለማከናወን የሌሎችን ወደብ ለመጠቀም የተገደደችበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከባህር በአጭር ርቀት ላይ እያለች ፈጣን እና ቀልጣፋ የወደብ አገልግሎት የምታገኝበት እድል አጥታም ቆየች፡፡ ይህም በሕዝቦቿ የመልማት መብት እና ጥያቄ ላይ ፈተና ሆኗል።
ይሁን እንጂ አሁን ባለንበት ዘመን፣ የመልማት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ የመሆኑን ያህል፤ የባህር በር ጉዳይም ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ አኳያ በተመሳሳይ መልኩ የህልውና ጉዳይ ሆኗል። በተለይ ለኛ ለኢትዮጵያውያን አሁን ለመልማት ካለን መሻት እና መሻታችን ከወለደው መነቃቃት አኳያ የባህር በር ጥያቄያችን አጠቃላይ የህልውና አጀንዳችን ነው።
የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ሆነ ማለት ደግሞ፤ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ እጣ ፈንታቸው ለተሳሰሩት የአካባቢው ሀገራትም ሆነ ለቀጣናው ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርተው አቅምን በጋራ ደምሮ በጋራ የመልማት እሳቤን መላበስ የግድ ይላቸዋል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሕዝቦች ውድቀትም ሆነ መነሳታቸው፤ ድህነትም ሆነ ብልጽግናቸው በአብሮነታቸው ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ስለሆነም ጉዳዩን አቅልሎ የአንድ ሀገር አጀንዳ አድርጎ ማየትና ለጉዳዩ ያልተገባ ትርጓሜ መስጠት አይገባም ።
በተለይ በአንዳንድ ሀገራት እንደሚታየው ጥያቄውን የሀገር ውስጥ ፖለቲካ አጀንዳ ከማድረግ ጀምሮ፤ የጣልቃ ገብነት መልካም አጋጣሚ አድርጎ ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይሄን እያደረጉ ያሉ ሀገራት አካሄዳቸው የአካባቢውን ሀገራት ሕዝቦች ወንድማማችነት እና ከዚህ የሚመነጭ አብሮ የማደግ ፍላጎትን ታሳቢ ያላደረገ፤ ድርጊታቸውም አካባቢውን ለተጨማሪ ግጭት ይዳርጋል።
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገቷን የሚመጥን የባህር በር የማግኘት ጥያቄ አቅርባለች፤ ጥያቄዋም በአካባቢው ለሚገኙ የወደብ ባለቤት ለሆኑ ሀገራት በሙሉ የቀረበ ነው። ይህ ደግሞ በቀጣናው ያሉ አቅሞችን አቀናጅቶ በአካባቢው አዲስ የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር የሚያስችል ተጨባጭ ተሞክሮ መፍጠር የሚያስችል ጅማሮ ነው ።
የአካባቢው ሀገራት መንግሥታት ይህን አዲስ የትብብር ምእራፍ ፤ለሕዝቦቻችው የመልማት ፍላጎት እንደመልካም አጋጣሚ ሊወስዱት፤ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን ትልቅ አቅም አድርገው በቅን መንፈስ ሊረዱት እና ለተግባራዊነቱ እራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይገባል። በዚህ አግባብም የሶማሌላንድ እድሉን መጠቀም የሚያስችላትን ርምጃ ወስዳለች፡፡ ይሄ ርምጃ ደግሞ ተገቢም፣ የቀጣናውን የመልማት ጥም ለማስታገስ አቅም ይሆናል፡፡
ከዚህ ውጪ የሀገሪቱን የባህር በር ጥያቄ በእልህ እና በማን አለብኝነት ፣ በግትርነት እና በጠላትነት መንፈስ በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ላለማስተናገድ የሚደረግ ጥረት ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ ስህተትም ብቻ ሳይሆን በተለይ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ ስምምነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን ለማድረግ እየሄዱበት ያለው መንገድ ተገቢ አይደለም።
በተለይም የሶማሊያ መንግሥት ኃላፊነት በማይሰማው መልኩ እያከናወነ ያለው ተግባር፣ ጉዳዩ የማይመለከታቸውን ኃይሎች ለጥፋት ከመጋበዝ የዘለለ የሚያተርፈው ነገር የለም። የአካባቢውን ሕዝብ የሰላም እና የመልማት ጥያቄ ሊመልስ የማይችል፣ አካባቢውን ለተጨማሪ ግጭት ፣ የሶማሊያን ወንድም ሕዝብ ለተራዘመ ችግርና የከፋ አደጋ የሚጋብዝ ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ መነሻ አድርገው የሚታዩ ተገቢ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች፤ ከምቀኝነት፣ ከቅኝ ግዛት እሳቤ እስራት እና በቀጣናው ላይ ውጥረትና ግጭትን ከመጋበዝ በጸዳ መልኩ፤ የቀጣናውን ወንድማማች ሕዝቦች አቅምን አሰባስቦ የጋራ ብልጽግናን እውን የማድረግ ከፍ ያለ እሳቤን ሊላበሱ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/ 2017 ዓ.ም