ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የዓመቱ ምርጥ እጩዎች ውስጥ ተካተዋል

በውድድር ዓመቱ ከስታድየም ውጪ በተካሄዱ ውድድሮች የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች እጩዎች ታውቀዋል፣

የዓለም አትሌቲክስ በየዓመቱ በሁሉም የውድድር ዘርፎች ምርጥ አትሌቶችን በተለያዩ መስፈርቶች አወዳድሮ ይሸልማል። በ2024 ለሽልማት እጩ የሆኑ አትሌቶችን ይፋ ሲያደርግ ‹‹ከስታድየም ውጪ በተካሄዱ ውድድሮች›› በሚል ዘርፍ አራት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በእጩነት ተካተዋል።

በውድድር ዓመቱ ከስቴድየም ውጪ በተለይም በጎዳና ላይ ውድድሮች ድንቅ ብቃት ያሳዩ አምስት ሴትና አምስት ወንድ አትሌቶች በእጩነት ሲቀርቡ ከነዚህ መካከል ሁለት ሴትና ሁለት ወንድ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካተታቸውን የዓለም አትሌቲክስ አሳውቋል።

በሴቶች አትሌት ትዕግስት ከተማና አትሌት ሱቱሜ አሰፋ ሲታጩ፤ በወንዶቹ ከቀናት በፊት በቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን የዓለም ክብረወሰን ያሻሻለው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻና የፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን ባለ ድል አትሌት ታምራት ቶላ ማካተት ችለዋል።

ዮሚፍና ታምራት እጩ በሆኑበት ዘርፍ ከዩጋንዳዊው አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ፣ ኬንያዊው ቤንሶን ኪፕሩቶና ኢኳዶራዊው ብርያን ዳንኤል ፒንታዶ የዓመቱ ምርጥ አትሌት ሽልማትን ለመውሰድ እጩ ሆነው ቀርበዋል። ትዕግስትና ሱቱሜ እጩ በሆኑበት ዘርፍ ኔዘርላንዳዊቷ አትሌት ሲፋን ሃሰን፣ ኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲችና የሀገሯ ልጅ አግኒስ ጂቤት ንጌቲች መካተት ችለዋል።

በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ የውድድሩን ክብረወሰን 2፡06፡26 በሆነ ሰዓት በማሻሻል ጭምር ማራቶንን ድል ያደረገው አትሌት ታምራት ቶላ፣ ሽልማቱን ለማሸነፍ ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል። ሌላው ኢትዮጵያዊ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በፓሪስ ኦሊምፒክ 10ሺ ሜትር ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ባይችልም ባለፈው እሁድ በቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን 57፡30 የሆነ ሰዓት በእጁ ማስገባቱ ብቻ ለዓመቱ ምርጥ አትሌት ሽልማት እጩነት አብቅቶታል።

ዩጋንዳዊው አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ በዓለም ሀገር አቋራጭና በቫሌንሲያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫዎች አሸናፊ በመሆኑ የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች ሽልማት እጩ ሆኖ ከኢትዮጵያውያኑ ጋር ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀርብ አስችሎታል። ኬንያዊው ቤንሶን ኪፕሩቶ በቶኪዮ ማራቶን ማራቶን ከማሸነፉ በተጨማሪ በፓሪሱ ኦሊምፒክ በርቀቱ የነሐስ ሜዳሊያ በማስመዝገብ እጩ ሆኗል። ኢኳዶራዊው አትሌት ብርያን ዳኒኤል ፒንታዶ ደግሞ በኦሊምፒክ 20 ኪሎ ሜትር እርምጃ የወርቅና፣ በኦሊምፒክ ድብልቅ የብር ሜዳሊያን አስመዝግቦ ከእጩዎች አንዱ በመሆን ተካቷል።

በተመሳሳይ ዘርፍ በሴቶች የቶኪዮ ማራቶን አሸናፊዋ አትሌት ሱቱሜ አሰፋ በውድድር ዓመቱ ያስመዘገበችው ፈጣን ሰዓት እጩ ሲያደርጋት፣ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ትዕግስት ከተማ በማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ በሮጠች አትሌት ፈጣን የሆነውን 2:16:07 ሰዓት ዱባይ ላይ አስመዝግባ ከማሸነፏ በተጨማሪ ከወር በፊት በበርሊን ማራቶን የቦታውን ሦስተኛ ፈጣን ሰዓት በ2:16:42 በማስመዝገብ ማሸነፏ በእጩነት አቅርቧታል።

ኔዘርላንዳዊቷ አትሌት ሲፋን ሃሰን በፓሪሱ ኦሊምፒክ ማራቶን በወቅቱ የርቀቱ ባለክብረወሰን የነበረችውን ኢትዮጵያዊት አትሌት ትዕግስት አሰፋን ተፎካክራ ወርቅ ማጥለቋ የዓመቱ ምርጥ አትሌት ተብላ እንድትታጭ አድርጓታል። በዚሁ ወር በተካሄደው የቺካጎ ማራቶን 2:09:56 ሰዓት በማጠናቀቅ የርቀቱን አዲስ የዓለም ክብረወሰን ያስመዘገበችው ኬንያዊቷ አትሌት ሩዝ ቺፕንጌቲች 42 ኪሎ ሜትርን ከ2፡10 በታች ያጠናቀቀች የመጀመሪያ አትሌት በመሆኗ ሽልማቱን የማሸነፍ የተሻለ እድል ይኖራታል ተብሎ ይጠበቃል። ሌላኛዋ ኬንያዊት እጩ አግኒስ ቺቤት በውድድር ዓመቱ ቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ላይ ያስመዘገበችው 1:03:04 ሰዓት ከኢትዮጵያዊቷ የርቀቱ ባለክብረወሰን ከተሰንበት ግደይ ቀጥሎ ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት መሆኑን ተከትሎ የሽልማቱ ተፎካካሪ መሆን ችላለች።

የዓመቱን ምርጥ አትሌቶች በበይነ መረብ የመመረጥ ሂደት ለስፖርት ቤተሰቡ ክፍት የተደረገ ሲሆን በመጪው ቅዳሜ ይዘጋል። በዚህም መሰረት በሦስት ዘርፎች አንድ ወንድና አንድ ሴት የዓመቱ መርጥ አትሌቶች በሶስት የመመረጫ መንገዶች ተለይተው የሚሸለሙ ይሆናል። የዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት 50 በመቶ፣ የአትሌቲክስ ቤተሰቦች 25 በመቶና በህዝብ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰበሰብ 25 በመቶ ድምፅ ነጥብ የሚይዝ ይሆናል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You