ኢራን በእስራኤል ላይ አዲስ ጥቃት ከከፈተች “ከባድ ዋጋ ትከፍላለች” ስትል አሜሪካ አስጠነቀቀች። እስራኤልም ኢራን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንዳትሆን ወታደራዊ አቅሟን የሚያዳክም ማዕቀብ እንዲጣልባት ጠይቃለች።
የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በእስራኤልና ኢራን ወቅታዊ ፍጥጫ ዙሪያ በመከረበት ወቅት ዋሽንግተን ማስጠንቀቂያውን አሰምታለች።
በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ኢራን በእስራኤልና በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ከፈጸመች “ያለምንም ማመንታት ራሳችን ለመከላከል እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ባለፈው ቅዳሜ እስራኤል በኢራን ላይ የወሰደችው የአጸፋ ርምጃ የመጨረሻው የተኩስ ልውውጥ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን ያሉት አምባሳደሯ፤ አሜሪካ ውጥረቱ እንዲባባስ እንደማትፈልግ አስታውቀዋል።
በመንግሥታቱ ድርጅት የኢራን አምባሳደር አሚር ሳይድ ኢራቫኒ ዋሽንግተን ለቴል አቪቭ “ህገወጥ እና ኢሞራላዊ ወታደራዊ ድጋፍ” እያደረገች ቴህራን የወሰደችውን ራስን የመከላከል ርምጃ ማውገዝ አትችልም ሲሉ ተቃውመዋል።
በሌላ በኩል ኢራን ለእስራኤል ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በእጇ “ያሉትን ሁሉንም መሳሪያዎች” እጠቀማለሁ ብላለች።
ኢራን ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ሁሌም ዝግጁ መሆኗን በመጥቀስም “በሉአላዊነታችን ላይ ለሚቃጣ ጥቃት ግን አጻፋውን የመመለስ መብት አለን” ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
እስራኤል በበኩሏ 15 አባል ሀገራት ባሉት የጸጥታው ምክር ቤት ኢራን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንዳትሆን ወታደራዊ አቅሟን የሚያዳክም ማዕቀብ እንዲጣልባት ጠይቃለች።
በጸጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን ያላት ቻይና በበኩሏ፤ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርስና የእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት የማስቆሙ ጉዳይ ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቃለች።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም