የተዛቡ አስተሳሰቦችን ለዘለቄታው መግራት ያስፈልጋል!

በየትኛውም ሁኔታ እና አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶች በሰው ህይወት ፣ በንብረት እና አጠቃላይ በሆነው የሰዎች የእለት ተእለት እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያስከትሉት አሉታዊ ተጽእኖ ከፍ ያለ ነው። ቀናትን ተሻግረው በማህበረሰብ ላይ ሊያስከትሉ የሚችለው የስነልቡና ስብራትም ከግምት በላይ እንደሚሆን ይታመናል።

ሕዝባችን በግጭቶች እና በጦርነቶች የተጣበበ የታሪክ ትርክት ባለቤት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ፣ ግጭቶች እና ጦርነቶች ሊያስከትሉት ስለሚችሉት ጥፋት ለመንገር መሞከር “ለቀባሪው አረዱት“ ያህል ነው። ይህም ሆኖ ግን ሕዝባችን ዛሬም የችግሮቹ ሰለባ ነው።

በየወቅቱ በተፈጠሩ ግጭቶች እና ጦርነቶች ልጆቹን ፣ ሀብት እና ንብረቱን፣ ከዛም ባለፈ ተስፋውን ገብሯል። ህይወቱ ተጎሳቁሏል ፣ ብዙ ዛሬዎችን በጣር ለማሳለፍ ተገድዷል። ይህ የአንድ ታሪክ ሳይሆን ፣ የብዙ የታሪክ ምእራፎቹ ተረክ ነው። ሆኖም ዛሬም ይሄን ተረክ መሻር በሚያስችል መንገድ ላይ መራመድና የሰላሙ ባለቤት ሊሆን አልቻለም።

እንደ አንድ በብዙ የሰላም እጦቶች እንዳለፈ እና የሰላም ዋጋ እንደገባው ትልቅ ማህበረሰብ፣ በእጁ ያለውን ሰላም ጠብቆ ለማስቀጠል የሚያስችል ማህበረሰባዊ ቁርጠኝነት መፍጠር አልቻለም። ለግጭት እና ለጦርነት የሚያነሳሱ አጀንዳዎችን እምቢ የማለት ልምምዶችን አሳድጎ ማህበረሰባዊ ማንነቱ ማድረግ አልቻለም።

ከዚህ የተነሳ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይም “ይዋጣልን!“ የሚሉ ፖለቲከኞች በሚፈጥሩት ሁከት እና ግርግር፤ ከዚህ በሚመነጭ ግጭት እና ጦርነት ብዙ ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል ተገድዷል። በስሙ እየማሉ እና እየተገዘቱ ወደ ፊት ቀድመው ሲያበቁ፤ ተመልሰው ለራሱ የመከራና የስቃይ ምንጭ የሆኑ ጽንፈኛ እና አክራሪ ኃይሎች እንዲበራከቱ ሰፊ እድል ፈጥሯል።

እነዚህ ኃይሎች እንደ ሀገር ከፈጠሩት ስጋት በከፋ እንወክለዋለን በሚሏቸው ማህበረሰቦች ላይ እያደረሱት ያለው መከራ እና ስቃይ ምን እንደሚመስል ባለፉት አራት ዓመታት በትግራይ ፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ማየት በቂ እና ከበቂ በላይ ነው። ችግሩ የቱን ያህል ሀገር እና ሕዝብን ዋጋ እንዳስከፈለ እና እያስከፈለ እንዳለ ለመገመትም የሚከብድ አይደለም።

ግጭቶቹ አንድም ፖለቲከኞቻችን ለስልጣን ካላቸው የተዛባ አመለካከት፤ ከዚያም በላይ ክፍተቶችን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ወደ ስልጣን ለመውጣት ከሚደረጉ ያልተገቡ አካሄዶች እና የተሳሳቱ ስሌቶች የሚመነጩ ናቸው። በዚህ መልኩ የሚፈጠሩ ችግሮችም ለዘመናት ዋጋ ሲያስከፍሉን የኖሩ ስለመሆኑም ታሪኮቻችን አብዝተው ይነግሩናል።

ለዚህም ባለፉት አራት ዓመታት ከፍ ባለ የሕዝብ ይሁንታ ወደ ስልጣን የመጣውን መንግሥት ከስልጣን በኃይል እና በሴራ ለማስወገድ የተደረጉ ያልተገቡ ጥረቶች ምን ያህል ፖለቲከኞቻችን ለስልጣን ያላቸው አመለካከት የተዛባ ስለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለስልጣን የቱን ያህል ርቀት እንደሚሄዱ በተጨባጭ ያመላከተ ነው።

እነዚሁ ፖለቲከኞቻችን በአንድም ይሁን በሌላ የተፈጠሩ ፣ የሀገርን ህልውና አደጋ ውስጥ የከተቱ ክፍተቶችን ሳይቀር በተሳሳተ ስሌት እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ወደ ስልጣን ለመምጣት የሄዱበት የጥፋት መንገድ የቱን ያህል ሀገር እና ሕዝብን ዋጋ እንዳስከፈለ ለሁሉም ዜጋ የተሰወረ አይደለም። ችግሩ ያልፈተነው ዜጋም የለም።

በአንድም ይሁን በሌላ ከማህበረሰባችን የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ክፍተት ጋር የተቆራኘው ይህ ሀገራዊ ችግር፤ በማህበረሰቡ ውስጥ አክራሪ እና ጽንፈኛ አስተሳሰቦች እንዲያቆጠቁጡ እና ትውልዱን እንዲፈታተኑት እድል ፈጥሯል። የአስተሳሰቡ ሰለባ የሆኑ ዜጎችም ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርጓል።

ይህንን የፖለቲከኞቻችን ያልተገራ እና ዘመኑን የማይዋጅ/ የማይመጥን የፖለቲካ እሳቤ ለዘለቄታ ለመግራት ከሁሉም በላይ የማህበረሰባችንን የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ማሳደግ የተገባ ነው፡፡ ለዚህም ማህበረሰባችን የራሱን እጣ ፈንታ በራሱ የሚወሰንበት የፖለቲካ እውቀት እንዲኖረው የሚያስችል የተጠናከረ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል።

እንደ ሀገር ይህንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ፤ፖለቲከኞቻችንን ከተበላሸ አስተሳሰባቸውም ሆነ ከጥፋት መንገዳቸው የምናቆማቸው። ከግጭት አዙሪት ወጥተንም ሰላማችንን ለዘለቄታው የራሳችን አድርገን በጀመርነው የልማት ጎዳና በስኬት ወደምንመኘው ብልጽግና ልንደርስ የምንችለው። በመሆኑም የፖለቲከኞቻችን ያልተገባ እሳቤ እና መንገድ በማህበረሰቡ የነቃ የፖለቲካ እሳቤ ሊገራ ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You