በቅርቡ በተካሄደው የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በተለያዩ ዘርፎች ላቅ ያሉ እድገቶች መመዝገባቸው ተመላክቷል። የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ደግሞ ለእዚህ የተሻለ አፈጻጸም አስተዋጽኦ ማድረጉም ተገልጿል። ይህ አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ እንዲመዘገብ የተቀመጠው እድገት እንደሚሳካ አመላካች መሆኑም ተጠቁሟል።
በተለይ በወጪ ንግድ ፣በመንግሥት ገቢ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና በውጭ ምንዛሬ ግኝት የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል። ከወጪ ንግድ አኳያም በማዕድን በተለይ በወርቅ የወጪ ንግድ እጅግ ስኬታማ ተግባር ተከናውኗል። በዚህ ረገድ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ፤ በ2016 በጀት ዓመት ዓመቱን ሙሉ ወደ ብሄራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን አራት ቶን ብቻ የነበረበት ሁኔታ፤ በተያዘው በጀት አመት የመጀመሪያው ሩብ አመት ወይም ሶስት ወራት ብቻ ሰባት ቶን ወርቅ ወደ ብሄራዊ ባንክ መግባቱ ነው።
ይህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምን ያህል ለውጥ እንዳመጣ ይጠቁማል፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የወርቅ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገ መሆኑን የማእድን ሚኒስቴር መረጃም አረጋግጧል። በተለይ ማሻሻያው የማእድን አምራቾችን ተጠቃሚ በማድረጉ አምራቾች የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ገዝተው ወደ ማምረቱ መግባት እንደቻሉም ነው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ያመላከተው።
ማሻሻያው በአነስተኛ ደረጃ የሚመረተውን የማእድን ምርት በከፍተኛ መጠን እያሳደገው ሲሆን፤ በተለይ የወርቅ ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው። ለዚህም ነው በ2017 በጀት ዓመት ስምንት ነጥብ ስድስት ቶን ወርቅ ለማምረት ታቅዶ፣ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ የዚህን እቅድ 70 በመቶውን ማሳካት የተቻለው።
በተመሳሳይ መልኩ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራውን ተከትሎ ብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ግብይት አስተዳደር ሥርዓቱ በገበያ እንዲወሰን የወሰደው እርምጃ፤ በተለይ ግብይታቸው ከውጭ ምንዛሪ ጋር ትስስር ላለቸው እንደ ወርቅ ላሉት ምርቶች ግብይት ይዞት የመጣው መልካም እድል ስለመኖሩ አፈጻጸሙ በሚገባ አሳይቷል።
ባለፉት ዓመታት ለብሄራዊ ባንክ ይቀርብ የነበረው የወርቅ ምርት መጠን በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆሉ ይታወሳል። ምርቱ ለጥቁር ገበያ ሲሳይ በመሆኑ ሀገር ከምርቱ ማግኘት የነበረባትን ጥቅም ስታጣ ቆይታለች።
ከሕገወጥ ድርጊቱ ጋር በተያያዘ ከዓመታት በፊት ለብሄራዊ ባንክ ይገባ ከነበረው በእጅጉ ያነሰ የወርቅ ምርት ነው ለባንኩ ሲቀርብ የነበረው። አንዳንድ ወርቅ በማምረት ሥራ የሚታወቁ ክልሎችም አመረትን ይሉት የነበረው የወርቅ መጠንም ከቀደሙት ዓመታት የወርቅ ምርታቸው ያንስም ነበር።
ወርቅ አምራቾች ችግሩ የተፈጠረው ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ ካለማግኘት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ሲገልጹ ቆይተዋል፤ በአንጻሩ ብሄራዊ ባንክም ይህን ቅሬታ ለመፍታት ወርቅ ለሚያቀርቡለት አካላት በወርቅ መረከቢያ ዋጋ ላይ በተደጋጋሚ ማሻሻያ ሲያደርግ ነበር። ሆኖም ችግሩ ከጥቁር ገበያ መንሰራፋትም ጋር ጭምር የተያያዘ ነበር፤ ህገወጦቹ የወርቅ ግብይቱን ብቻ ሳይ ሆን የማምረት ስራውን ጭም ር እየተቆጣጠሩ የመ ጡበት ሁኔታም ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል።
መንግሥት የሀገርን ጥቅም በእጅጉ የሚጎዳውን ይህን ሕገወጥ ድርጊት ለመቆጣጠር በሀገር ደረጃ ግብረ ኃይል በማቋቋም በሕገወጥ የወርቅ ማምረትና ግብይት ተግባር በተሰማሩ አካላት ላይ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ መውሰድ ውስጥ በመግባቱ፣ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች እና ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል።
ይሄም ሕገወጥ ድርጊቱን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መቆጣጠር የተቻለበትን ሁኔታ የፈጠረ ቢሆንም፤ ዘላቂ መፍትሄ ግን መሆን ሳይችል ቆይቷል። በአንዳንድ ክልሎችም ችግሩ በመሠረታዊነት እንዳልተፈታ ሲናገሩ የነበረውም ለዚህ ነው። አሁንም ድረስ ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የወርቅ ማምረቱም ሆነ የግብይቱ ሥራ በሕገወጦች ተጽእኖ ስር የወደቀባቸው አካባቢዎች እንዳሉ እየተጠቆመ ነው።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተሆኖም ነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረግ እና ችግሩን በሌላ መንገድ ለመፍታት ወደ ርምጃ የተገባው። መንግሥትም በዚህ መልኩ ርምጃ መውሰድ በመቻሉ ለእዚህ ግዙፍ ችግር ፍቱን መፍትሄ መስጠት ችሏል። የ100 ቀናት ግምገማውም በሚገባ ያመላከተው ይሄንኑ እውነት ነው። በመሆኑም ቀጣዩ ሥራም ይህን ጥሩ አፈጻጸም ዘላቂ ለማድረግ ጠንክሮ መሥራት ሊሆን ይገባል።
ለአብነትም፣ ማእድን ሚኒስቴር ባህላዊ ወርቅ አምራቾች በአነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ወርቅ አምራችነት እንዲሠሩ የፈጠረው ምቹ ሁኔታና ያንን ተከትሎም በወርቅ ምርት ላይ እየመጣ ያለው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ይኖርበታል። ምክንያቱም ጅምር ተግባሩ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ድጋፍ ጋር ተዳምሮ ለብሄራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን እንዲጨምር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነውና።
ማሻሻያው አምራቹንም ሀገርንም በእጅጉ የሚጠቅም እንደመሆኑ ትግበራው በወርቅ ግብይት ላይ ይስተዋል ለነበረው ሕገወጥ ተግባር መፍትሄም ይዞ መጥቷል። ባለፉት ሶስት ወራት ወደ ብሄራዊ ባንክ የገባው ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ምርትም ይህንኑ በሚገባ አመላክቷል። ስለዚህ ይህን ውጤታማነት ዘላቂ ለማድረግ ባለፉት ሶስት ወራት በተካሄደው የማሻሻያው ትግበራ የተገኙ ተሞክሮዎችን በማስፋት ለላቀ ውጤታማነት ርብርብ ማድረግ ከሁሉም ባለድርሻዎች የሚጠበቅ ተግባር ነው።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም