ሕገ ወጥነት ዘረፈ ብዙ ብቻ ሳይሆን፤ መልከ ብዙም ነው፡፡ ዘርፈ ብዙነቱ፣ የሕገ ወጥ ተግባራት በየትኛውም እና በማንኛውም ቦታና ሁኔታ ውስጥ ያለ ወሰን የሚከናወን ተግባር በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሕገ ወጥነት በማኅበራዊ ዘርፎች፣ በፖለቲካዊ መስኮች፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ዓውዶች፣ በሠላምና ፀጥታ ምኅዳሮች፣ በጤና እና ፍትሕ ሰፈሮች፣… ብቻ የማይገባበት ጓዳ ጎድጓዳ፣ መስክና ዓውድ የለውም፡፡
በእነዚህ መስኮች ያለ ገደብ ሲካሄድ ደግሞ እንደየዘርፎቹ ተጨባጭ ሁኔታ መልኩን፣ ቴክኒክና ታክቲኩን እየቀያየረ የሚከሰት ነው፡፡ ትናንት ውስብስብ የሕገወጥነት ስልት የተባሉት አካሄዶች ዛሬ ላይ ኋላ ቀር በመሆናቸው፤ እሱም ለአካሄዱ የሚውል ዘመናዊ የሕገወጥ ተግባራትን መከወኛ ብልሃቶችን ፈጥሯል፡፡ ካልሆነም ዘመን አመጣሹን ቴክኖሎጂ ለራሱ በሚሆን መልኩ አበጃጅቶ ጥቅም ላይ አውሏል፡፡
በዚህ ረገድ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ከማዘዋወር ጀምሮ፤ የጦር መሣሪያ፣ የመድኃኒትና ምግብ፣ የአልባሳትና መዋቢያዎች፣ የኤሌክትሮኒክስና ተሽከርካሪ፣ የአደንዛዥ ዕፅና ጌጣጌጥ፣ የቁም እንስሳትን ጨምሮ የግብርና ምርቶች፣ ማዕድናት እና ሌሎችም የሀገር ውስጥ ሃብቶች ወደ ውጪ የሚሸሹበት፤ ለሀገርና ሕዝብ ጎጂ የሆኑ ምርቶችን ጨምሮ ደግሞ ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡና እንዲወጡ ሲደረግ ማየትና መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡
እነዚህ ሕገወጥና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች ታዲያ፣ ሀገርን እንደ ሀገር፤ ሕዝብንም እንደ ሕዝብ ዋጋ የሚያስከፍሉ፤ የመንግሥትንም ሕልውና በእጅጉ የሚፈታተኑ ተግባራት ናቸው፡፡ ምክንያቱም፣ ሕገወጥና ኮንትሮባንድ በመጀመሪያ ኢኮኖሚን ይጎዳል፡፡ ይሄ ሲባል በሕገወጥና ኮንትሮባንድ ፍሰቱ ምክንያት ሀገር ማግኘት ያለባትን ገቢ በእጅጉ ያሳጣል፡፡ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥርዓቱንም ይረብሻል፡፡
በዚህ መልኩ መንግሥት ከንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች ማግኘት የሚገባውን ገቢ አላገኘም፤ ግብርና ቀረጥም አልሰበሰበም ማለት ደግሞ፤ እንደ መንግሥት የሕዝቦችን ጥያቄ ለመመለስ፣ የሀገርንም ልማት ለማፋጠን አቅም የሚሆነው የገንዘብ ሃብት ያጥረዋል ማለት ነው፡፡ አንድ መንግሥት ደግሞ የሥራ ማስኬጃ ሃብት አጠረው ማለት በማኅበራዊውም፣ በፖለቲካዊውም፣ በኢኮኖሚና ሌሎችም መስኮች የመፈጸም አቅሙ ችግር ይገጥመዋል ማለት ነው፡፡
ይሄ ሲሆን ደግሞ፣ ሕገወጦችና ኮንትሮባንዲስቶች አቅም እየፈጠሩ፣ በመንግሥትና በዜጎች መካከል መራራቅና መጠራጠር እንዲፈጠር ሁሉን አቀፍ ሴራ እየፈጸሙ፤ አለፍ ሲልም ዜጎች በመንግሥታቸው ላይ እምነት እንዲያጡና በሕገወጦችና ኮንትሮባንዲስቶች እሳቤ እንዲጠለፉ የሚሆኑበትን ዕድል እስከመውለድ ሊደርስ ይችላል፡፡
ምክንያቱም፣ መንግሥት ሃብት አጥቶ የሕዝቦችን የልማት፣ የማኅበራዊ ጉዳይ፣ የፖለቲካ እንዲሁም የሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች በልኩ መመለስ የሚችልበት አቅም ከተፈተነ፤ ዜጎች እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳታቸው አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አንድም ከለውጡ በፊት የነበረውን ሀገራዊ እውነት ማስታወሱ ተገቢ ሲሆን፤ ለውጡም የዚሁ የሕዝቦች ጥያቄ ማደግ እና የመንግሥት የሕዝብን ጥያቄ የመመለስ አቅም ማጣት ፍሬ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
ይሄ የሕገወጦችና ኮንትሮባንዲስቶች ተግባር ታዲያ የለውጡን የመጀመሪያ ዓመታት ጉዞ ፈትኖ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ምክንያቱም በኮንትሮባንድ ላይ ተመሥርቶ ሀገር መበዝበዝና ሀገር መናጥ የለመደ ግለሰብና ቡድን፤ ከዚህ የፈረጠመ የፈላጭ ቆራጭነት መስመሩ መውጣት አይችልም፡፡ እናም የሕዝቦችን ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ በማባባስ፣ የማኅበራዊ ጉዳዮች በማመሳቀል፣ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች በመጥለፍ እና የሠላምና ፀጥታ አደጋዎችን በመጋበዝ በዜጎች ችግርና ሰቆቃ ውስጥ ሕልውናውን ለመገንባት መታተሩ አይቀሬ ነው፡፡
ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታትም አንዴ ሞቅ፣ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያሉ እዚህም እዚያም የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሕገወጥና ኮንትሮባንድ ጉዳይ ዛሬም ድረስ ሕለው ሆኖ የመዝለቅ አንድ አብነቶች ናቸው፡፡ ምክንያቱም፣ ዛሬም ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሩ በተለያየ ቦታ ያሉ አማፅያንን ለመደጎም እየዋለ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በሠላምና ፀጥታ ሥራው ላይ የራሱ ችግር መፍጠሩ አይቀርም፡፡
በተመሳሳይ የማዕድን፣ የግብርና ምርቶች፣ የቁም እንስሳት፣ የገንዘብ እና ሌሎችም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ምርቶች ከውስጥ ወደ ውጪ፤ ከውጪም ወደ ውስጥ የሚመላለሱበት ሁነት አለ፡፡ ይሄ ደግሞ እንደ ሀገርና ሕዝብ ከሚፈጥረው የኢኮኖሚ ጫና ባሻገር፤ በመንግሥት ገቢ ላይ ጫና የሚፈጥር፤ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎችንም ተወዳዳሪነትን የሚያቀጭጭ ነው፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር መልክና ስልቱን እየቀያየረ መከሰት፤ በዜጎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ከፍ ያለ ጫና እየፈጠረ ያለ፤ በተለይም ከጤና እና የአዕምሮ ብሎም የሥነልቡና ችግሮችን በመፍጠር አምራች ዜጎች ወደ ጥገኝነት እንዲሸጋገሩ የሚያደርግ ነው፡፡ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርም የዚሁ አንድ ዘርፍ ሲሆን፤ ይሄ ደግሞ በሰው ልጅ አካልም፣ ሕይወትም ላይ ከፍ አደጋን እያስከተለ ያለ ነው፡፡
እነዚህ እና ሌሎች በርካታ ማሳያዎች የሚጠቀሱለት ሕገወጥነትና ኮንትሮባንድ ታዲያ፤ ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ያለውን ጉልህ አሉታዊ ተፅዕኖ በመገንዘብ እንደ መንግሥት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ በዚህም በተግባሩ ላይ ተሰማርተውም፣ ተሳትፈውም የተገኙ አካላት ላይ እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎች ዓቢይ ማሳያ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ ከችግሩ ስፋትና ረቂቅነት አኳያ በመንግሥት ብቻ ተሠርቶ ግቡን የሚመታ ባለመሆኑ፤ ሁሉም ዜጋ ችግሩን መከላከል ማለት ከፍ ያለ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም የሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ የራስን አበርክቶ ማድረግ መሆኑን በመገንዘብ ሕገወጥነትንና ኮንትሮባንድን የመከላከል ኃላፊነትን መወጣት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም