የብሪክስ አባልነት-ከፍ ያለ የዲፕሎማሲ ድል

በአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር 2009 ላይ የጋርዮሽ የፖለቲካ ስብሰባ ያገናኛቸው አራት የተለያዩ ሀገራት በሩሲያ ምድር ላይ ታደሙ። ቻይና፣ ብራዚል፣ ሕንድና አዘጋጇ ሩሲያ ጭምር። ሀገራቱ በ2001 ላይ ተወጥኖ የቆየውን የብሪክስ ድርና እርሾ ዳግም አንስቶ ለመወያየት አልዘገዩም። በርካታ አጀንዳዎችን በመምዘዝ በጠንካራ ውይይትና ክርክር የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አፀደቁ።

እነዚህ የቡድን ሀገራት ለጋራ ኅብረታቸው ሥያሜ ይሆን ዘንድ አንድ ገዢና ተፅዕኖ ፈጣሪ ስም መምረጥ ነበረባቸው። በጊዜው ለስያሜው የሚበጁ የተለያዩ ስሞች እንደ አማራጭ በዕጩነት ቀርበው ነበር። ቆይቶ ግን ሁሉንም በአንድ ሀሳብ የሚይዘው ስያሜ ልቦናቸውን ገዛ። ሀገራቱ በአንድ ሀሳብና ፍላጎት ስሙን ሊያጸኑት ተስማሙ። ለጋራ መጠሪያቸው ከየሀገራቸው ስም የመጀመሪያው ፊደል እንዲወሰድ ፈቅደው ቃሉን በይሁንታ አፀደቁ።

‹‹ብሪክስ ይሉት የስያሜ ምንጭ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድና ቻይና ከተባሉት ሀገራት ላይ የተቀዳ ነው። ሁሉም ከመጀመሪያዎቹ ፊደላት አንደኛውን ለስያሜያቸው መጠሪያነት አዋጥተዋል። 2001 ላይ ተመሥርቶ የቆየው የብሪክስ ቡድን ሀገራት ከአንድ ዓመት በኋላ በ2010 ዳግም ሲገናኝ ደቡብ አፍሪካን በማከልና ቁጥሩን ወደ አምስት ከፍ በማድረግ ነበር።

የብሪክስ ቡድን ሀገራትን ለመመሥረት ምክንያት የሆኑ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ነጥቦች ይነሳሉ። በዋንኛነት ግን የዓለም ፋይናንስ ሥርዓት በምዕራባውያን ሀገራት ክንድ ስር የመውደቁ እውነታ አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአሜሪካ ዶላር የዓለማችን ብቸኛ መገበያያ ገንዘብ ሆኖ መዝለቁ ለቡድኑ መመሥረት አንዱ ምክንያት ነው።

የቡድን ሀገራቱ ለዘመናት ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ ያመዘነው የዓለም ሥርዓት ሊበቃው ይገባል ሲሉ የመሠረቱት ኅብረት ውጤታማ እንደሚሆን አምነዋል። ይህ የብሪክስ ሀገራት እርምጃ ነባሩን የዓለም እንቅስቃሴ ማስደንገጡ አልቀረም። ብሪክስ ዓለም ዓቀፍ ተደማጭነትንና ትኩረትን በማግኘቱ የአባል ሀገራት ጠያቂዎችም ቁጥር እየጨመረ ሄደ።

በየጊዜው የሚስተዋለው የምዕራባውያን መልከ ብዙ ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ ለታዳጊ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ጭምር ድምፅ ሆኖ ለመወከል የቡድኑ መመሥረት ወሳኝ የሚባል ሆኗል። በነዚህ ቡድን አባላት እሳቤ እንደ አይ.ኤም.ኤፍ እና የዓለም ባንክ የመሳሰሉ የፋይናንስ ተቋማት ለአሜሪካ ጥቅም ማስከበሪያ ሆነው ቆይተዋል። የተለያዩ ሀገራትን ኢኮኖሚ ለማዳከም ደግሞ በፖለቲካ የመጠቀም ስልታቸው የሚያህላቸው የለም።

አምስቱ የብሪክስ ሀገራት ለዘመናት ዓለምን በተፅዕኖ ተቆጣጥሮ የቆየውን የአሜሪካ ዶላር ግብይት በሌላ ገንዘብ የመተካት ዓላማን ይዘው ተነስተዋል። ከተቋቋሙበት ዕቅድ ውጭ የአሜሪካ ፖለቲካ መጠቀሚያ የሚሆኑ የፋይናንስ ተቋማትን ፈተና የሚያሸንፉ አቻዎችን የመመሥረት ትልም ይዘዋል።

የብሪክስ ቡድን ሀገራት 40 በመቶውን የዓለም ሕዝብ እንደሚይዙ ይነገራል። የአምስቱ ሀገራት የጋራ ምጣኔ ሀብትም የዓለምን 26 በመቶ ይሸፍናል። ይህ ሀብት በየግዜው የመጨመር አቅም አለው። በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖም ከፍተኛ ነው።

እነዚህ አምስት ሀገራት በዓለማችን ያላቸው የሀብት መጠንና የሕዝብ ብዛት ኃያል የሚባል ነው። ፍትሐዊና ዓለም አቀፍ አሰላለፍን የያዘው የብሪክስ መስመር 32 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ኢኮኖሚ የምርት ጥቅል በእጃቸው ያደረጉ ኃያላን ሀገራት የሚገኙበት ቡድን ነው።

ቡድኑ የራሱ የሆነ የልማት ባንክ አቋቁሟል። ዓለም አቀፍ ተደማጭነትና በጎ ተፅዕኖ ያተረፈው ስብስብ ጠቀሜታውን ባስተዋሉ ሀገራት ዓይኖች ፈጥኖ መግባት ከጀመረ ቆይቷል። እንዲህ መሆኑ ከዓመታት በፊት የዓለም ኢኮኖሚን ከሚዘውሩት ምዕራባውያን ላይ የተተከሉ ዓይኖች እንዲነሱ አስገድዷል።

የቡድን አባላቱን ሰፊና ጠንካራ ዕቅድ በግልጽ የተረዱ ሌሎች ሀገራት እነሱን የመቀላቀል ፍላጎት እያሳዩ ነው። በአሁኑ ጊዜም ከአርባ በላይ ሀገራት የአባልነት ጥያቄን አቅርበዋል። ሀገራችን ኢትዮጵያም ብሪክስን ለመቀላቀል ፍላጎት ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ሆናለች። ፍላጎቷን በተግባር ለማሳየትም የአባልነት ጥያቄ አቅርባ ተሳክቶላታል። ይህን አስመልክቶ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞችና ፍላጎቷን ከሚያስከብሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የመሥራት ጽኑ ፍላጎት አላት።

ባለፈው ዓመት በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው አስራ አምስተኛው የፈጣን አዳጊ ሀገራት ጉባኤ ላይ ሀገራችን ተሳታፊ ነበረች። በዚህ ቆይታዋም ኢትዮጵያ በአባልነት እንድትቀጥል ይሁንታውን አግኝታለች። ሀገራችን ብሪክስን የመቀላቀሏ እንድምታ ውጤቱ መልካም እንደሚሆን ታምኖበታል።

ኢትዮጵያ በዚህ ውሕደቷ በየግዜው በምታደርጋቸው የኢኮኖሚ ለውጦችና አዳዲስ እንቅሰቃሴዎች መሠረቱን የሚያጸና ግንብ ይኖራታል። ይህ እውነታም ለሀገራችን የዲፕሎማሲው ድል ማስመስከሪያና ዋንኛ ማሳያ ነው። የሚሉ በርካቶች ናቸው። ብሪክስን ለመቀላቀል ፍላጎት ካላቸውና ጥያቄውን ካቀረቡ ከአርባ በላይ ሀገራት ስድስቱ ብቻ በመመዘኛ ተለይተው ተመርጠዋል። ከነዚህ መሐል ሀገራችን አንዷና ዋንኛዋ መሆኗ የዲፕሎማሲውን ፈጣን ርምጃ በገሐድ ያሳየ ምስክርነት ነው።

ለዲፕሎማሲው ግንኙነት ቅርበት ያላቸው ምሑራን እንደሚሉት ብሪክስን ለመቀላቀል በነበረው ጥረት ከእያንዳንዱ አባል ሀገራት ጋር በመገናኘት ጥበብና ብቃት የተመላበት ድል ለማስመዝገብ ተችሏል። በዚህም ሀገራቱ በኢትዮጵያ ማንነትና ወቅታዊ ቁመና ላይ ጽኑ አመኔታ ኖሯቸው በአባልነት እንዲመርጧት ምክንያት ሆኗል። ሀገራችን በዚህ የድል ጎዳና ላይ ለመቆም የተጓዘችባቸው መንገዶች ግን አልጋ በአልጋ አልነበሩም። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ይህ ልፋትና የበዛ ጥረት የተጀመረው ከዛሬ አስራ አራት ዓመታት በፊት ነበር።

ሀገራችን ከሌሎች ሀገራት ይበልጥ ለምርጫ እንድትታጭ ከሆነችባቸው ምክንያቶች አንዱ ለዘመናት በቅኝ ያለመገዛቷና ነፃነቷን አስከብራ የመኖሯ ሐቅ ነው። ከጥንት እስከዛሬ የዓለም አቀፍና አሕጉራዊ ዲፕሎማቶች መገኛና መቀመጫ የመሆኗ እውነትም ምርጫውና አመኔታው እንዲጣልባት ምክንያት ነበር። በበርካታ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በመሪነት ሚና የነበራት ድርሻም የተለየ ግምት አግኝቷል።

ኢትዮጵያ በበርካታ እሾሃማ መንገዶች እያለፈችም ቢሆን ከሰሐራ በታች ካሉ ሀገራት በበለጠ ያስመዘገበችው ፈጣንና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከዓይን የሚገባና ለአርዓያነት የሚጠቀስ ነው። በነዚህና በሌሎች ተመራጭነት ብሪክስን መቀላቀሏ የዲፕሎማሲ አቅሟን የሚያሳድግና ተጨማሪ ገበያን የሚያሰፋ እንደሚሆን ጭምር ይታመናል። በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ላይ ለሚኖራት ኢኮኖሚያዊ ተደራሽነትም ድርሻውን የጎላ ያደርገዋል።

ሰሞኑን ሞስኮ ላይ በተካሄደው የብሪክስ ቢዝነስ ፎረም ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቪዲዮ ባስላለፉት መልዕክት በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የሚገኘው ኢኮኖሚ ለብሪክስ አባላት አገራት ለኢንቨስትመንት፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብርና ንግድ ታላቅ ዕድልን ይዞ መጥቷል። ኢትዮጵያ ያላት ዕምቅ የተፈጥሮና የግብርና ሀብት ሰፊውን የአፍሪካ ገበያና ከዚያም በላይ የሚፈልግ ነው። በካርጎ ጭነትና መንገደኞችን በማጓጓዝ ግንባር ቀደም የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድም ተጨማሪ ዕድል ሆኖ እንደሚያገለግል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሪክስ አባላት መካከል የጋራ ተጠቃሚነት መኖር ወሳኝነትን አንስተዋል። የዓለም አስተዳደራዊ መዋቅር ለታዳጊው ኢኮኖሚ ምላሽ ሰጪ እንዲሆንም በንቃት መሥራት ግድ እንደሚል አሳስበዋል። ዐቢይ (ዶ/ር) የብሪክስ አባል አገራት ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በቀጥታ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በኢንቨስትመንቱ መሳተፍ ለሚፈልጉ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በቴክኖሎጂና ቱሪዝም፣ ዘርፎች ትልቅ ዕድል መኖሩን በመግለጽ ሀገራቸው የ2025 የብሪክስ ኢኮኖሚ ትብብር ስትራቴጂ ስኬታማ እንዲሆን የበኩሏን ድርሻ እንደምትወጣ ጭምር መልዕክታቸውን አድርሰዋል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም

Recommended For You