ሀገራቱ የጋራ ዕጣ ፈንታቸውን በጋራ የሚወስኑበት አዲስ የፖለቲካ ባሕል ያስፈልጋቸዋል

በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት፤ የአካባቢውን ሀገራት ሕዝቦች እውነተኛ ፍላጎት በአግባቡ መረዳት እና ለፍላጎታቸው በቅንነት እና በታማኝነት መሥራትን ይጠይቃል። ከዚህ ውጪ በአካባቢው ዘላቂ ሠላም ማስፈን እና ማፅናት ይቻላል ብሎ ማሰብ በራሱ ችግሮችን የሚያባብስ የተሳሳተ አካሄድ ነው።

አካባቢው ካለው ጂኦ ፖለቲካል ጠቀሜታ አኳያ፤ የብዙዎች ቀልብ የሚስብ፤ አይን ማረፊያ እና የትኩረት ምንጭ ነው። ከዚህ የተነሳ በየዘመኑ የተነሱ ኃያላን መንግሥታት ለአካባቢው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ሲንቀሳቀሱ ተስተውለዋል። አሁንም አብዛኞቹ የዘመናችን ኃያላን መንግሥታት በአካባቢው ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ ያዋጣል የሚሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው።

አካባቢው የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ የደም ስር ከመሆኑ አኳያም፤ በአካባቢው ሊፈጠር የሚችል የበላይነት በአንድም ይሁን በሌላ፤ በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ያለውን የሀገራት ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ አቅም የሚያጎናጽፍ ነው። ይህ ደግሞ ባለንበት ዓለም የቱን ያህል ከፍያለ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ አይደለም።

የአካባቢው ሀገራት በዚህ ዓለም አቀፋዊ እውነታ ውስጥ የራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም የጉዳዩ አካል ያደርጋቸዋል። ከዛም ባለፈ አካባቢውን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ትንቅንቆችን በስክነት ማየት ካልቻሉ የሌሎች አጀንዳ ተሻሚ በመሆን አላስፈላጊ ዋጋ መክፈላቸው የማይቀር ነው። ለዚህ ደግሞ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በአካባቢው የሚስተዋለውን ግጭት እና አለመረጋጋት ማየት በቂ ነው።

በየወቅቱ ወደ ሥልጣን የሚመጡ የአካባቢው ሀገራት መንግሥታት፤ የሕዝቦቻቸውን እውነተኛ ፍላጎት ወደኋላ በመተው፤ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት የሌሎች አካላት/ኃይላት አጀንዳ መፈጸሚያ ሲሆኑ ማየት የተለመደ ነው። አሁን አሁን ችግሩ በአካባቢው የፖለቲካ ባሕል እየሆነ መጥቷል።

በርግጥ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች እውነተኛ ፍላጎት ካሉበት አንገት አስደፊ ድህነት እና ኋላቀርነት መውጣት ነው። ለዚህ የሚሆንም በቂ የተፈጥሮ እና የሰው ሀብት ባለቤቶች ናቸው። የሚፈልጉት እነዚህን ሀብቶች አቀናጅቶ ወደ ልማት የሚቀይር ፤ በተለወጠ ማንነት የተለወጠ ሀገር መፍጠር የሚችል የፖለቲካ አመራር ነው።

የሀገራቱ ሕዝቦች እውነተኛ መሻት፤ በሀገራቱ መካከል ለዘመናት የቆየውን ድንበር ተሻጋሪ ተፈጥሯዊ ወንድማማችነት፤ ተጨባጭ የልማት አቅም በማድረግ፤ የጋራ ዕጣ ፈንታቸውን በጋራ የሚወስኑበትን አዲስ የፖለቲካ ባሕል የሚፈጥር የፖለቲካ አመራር ነው።

የሀገራቱ ሕዝቦች ለዓመታት ካሳለፏቸው ግጭቶች እና ጦርነቶች፤ የሠላም ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ በተጨባጭ አይተዋል። ተስፋ ያደረጓቸው ትውልዶቻቸው ተስፋ ቢስ ሆነው ሲያልፉ አስተውለዋል፤ ብዙ ዋጋ ያስከፈሏቸው የፖለቲካ ትርክቶች ትርጉም የለሽ ሆነው አንገት አስደፍተዋቸዋል።

ግጭቶች እና ጦርነቶች ቀድሞ ከነበሩበት ድህነት እና ኋላቀርነት ወደከፋ ድህነት እና ኋላቀርነት ወስደዋቸዋል፤ ተመፅዋችነት ብሔራዊ መገለጫቸው፤ ጠባቂነት ዕጣ ፈንታቸው ሆኗል። አንዳንዶች የአክራሪ እና ፅንፈኛ ኃይሎች መፈልፈያ ሆነዋል። በዚህም በዛሬዎቻቸው ላይ የመወሰን አቅም አጥተው ተቸግረዋል።

የሕዝባቸውን የእለት ተእለት ሕይወት በሠላም የሚመሩበት ሀገራዊ አቅም አጥተው፤ እንደሀገር የከፋ ችግር ውስጥ ያሉ ፤ በሌሎች የሕይወት መስዋዕትነት ዛሬን እየኖሩ ያሉም አሉ። ይህ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች አሁናዊ ተጨባጭ እውነታ ነው ፤ የሕዝቦቹም እውነተኛ ፍላጎት ከዚህ ለዘለቄታው መውጣት ነው።

ለዚህ ደግሞ በአካባቢው ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ያሉበትን ተጨባጭ እውነታ መረዳት ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ በእልህ እና በግትርነት፤ በሕዝቦች መካከል ጠላትነት እና ተቃርኖን በመስበክ፤ የሌሎችን አጀንዳ ስቦ በመሸከም በአካባቢው ዘላቂ ሠላም ማምጣት አይቻልም። በአካባቢው ዘላቂ ሠላም ማስፈን ካልተቻለ ደግሞ የሕዝቦቹን የመልማት ፍላጎት ተጨባጭ ማድረግ አይቻልም።

በመሆኑም የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦችን ካሉበት አንገት አስደፊ ድህነት እና ኋላቀርነት ለማውጣት ሠላምን እና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና የፖለቲካ አመራር ያስፈልጋል። በዚህም ሕዝቦቹ መካከል ለዘመናት የቆየውን ድንበር ተሻጋሪ ተፈጥሯዊ ወንድማማችነት፤ ተጨባጭ የልማት አቅም በማድረግ፤ የጋራ ዕጣ ፈንታቸውን በጋራ የሚወስኑበትን አዲስ የፖለቲካ ባሕል መፍጠር ይገባል። ያለው ብቸኛ አማራጭም ይሄው ነው።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም

Recommended For You