ከከበሩ ማዕድናት ልማት የመጠቀሚያው ሌላው መንገድ

ኢትዮጵያ በከበሩ ማእድናት ሀብቶቿ ትታወቃለች። እነዚህ እንደ ኦፓል ያሉት ሀብቶች እየለሙ ያለው በባህላዊ መንገድ ሲሆን፣ ማእድኑ ለውጭ ገበያ የሚቀርብበት መንገድም ምንም አይነት እሴት ባልተጨመረበት ሁኔታ በጥሬው ሆኖ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እነዚህን የከበሩ ማዕድናት በጥሬው ከመሸጥ በዘለለ፣ እሴት በመጨመር አስውቦና አስጊጦ ለገበያ ማቅረብ ላይ በስፋት እየተሰራ ይገኛል።

ማዕድናቱ እሴት እየተጨመረባቸው ለአንገት፣ ለጆሮ፣ ለእጅ እና ለመሳሰሉት ጌጣጌጥነት እንዲውሉ እየተደረገ ነው። ይህም ጥረት አገሪቱ ካሏት የከበሩና በከፊል የከበሩ ማዕድናት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ማድረግ እንደሚያስችል በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ።

በተለይ የሰሜኑ የአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በእነዚህ ማዕድናት የታወቁ መሆናቸውንና የተለያዩ አካላትም ማእድን በማውጣት ላይ መሰማራታቸውንም በመጥቀስ፣ በእነዚህ ማእድናት ላይ እሴት በመጨመር ስራ ላይ በደንብ መስራት እንዳለበት ይጠቁማሉ። ለዓለም ገበያ ቀርበው ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ምርቶችን ለማምረትም ብዙ መስራትን እንደሚጠይቅም ያመላክታሉ። በዚህ ሥራ ላይ ተሰማርተው ለሚሰሩ አካላት ተገቢው ድጋፍና ክትትል ቢደረግላቸው የተሻሉ ሥራዎች በመስራት ለውጦችን ማምጣት እንደሚቻልም ይመክራሉ።

በሀገሪቱ የከበሩ ማዕድናትን በማስዋብና ማስጌጥ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ በርካታ ድርጅቶች እንዳሉ ይታወቃል። ከእነዚህ መካካል አንዱ በጎንደር ከተማ የሚገኘው ፍቅሬ ኡስማንና ጓደኞቻቸው የከበሩ ማዕድናትን ማስዋብና ማስጌጥ ሥራ ድርጅት ነው። አቶ ፍቅሬ ሀብቴ እና ሦስት ጓደኞቹ ተደራጅተው የመሰረቱት ይህ ድርጅት የተቋቋመው ከስድስት ዓመታት በፊት ነው። ከድርጅቱ መስራቾች ሁለቱ የብርና የወርቅ ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ ሁለቱ ደግሞ የላፒደሪ (ማዕድናቱን የሚቆርጡና ዲዛይን የሚደርጉ) ባለሙያዎች ናቸው።

የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ፍቅሬ ሀብቴ እንዳሉት፤ የድርጅቱ መስራቾች ይህን ሥራ ለመጀመር አንዱ ምክንያት የሆናቸው ማዕድናቱ በክልላቸው በቅርበት ሊያገኙዋቸው የሚችሏቸው መሆናቸው ነው። ማዕድናቱ በጥሬው ለገበያ ከሚቀርቡ ይልቅ እሴት ተጨምሮባቸው ቢቀርቡ የተሻለ ተጠቃሚነት እንደሚፈጥር አስቀድመው መረዳታቸውም ሌላው ምክንያት ሆኗቸዋል።

ድርጅቱ ከክልሉ በሚመረቱ የከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር የማዕድን ስራውን ለማነቃቃት በማሰብ ወደ ሥራው መግባቱን ሊቀመንበሩ ይናገራሉ። ማዕድናት ወደ ማስዋብና ማስጌጥ ሥራዎች ሲገባም ‹‹ሜዳ ›› የተሰኘው የግብረ ሰናይ ድርጅት ድጋፍ እንዳደረግለትም ይገልጻሉ፡፡

‹‹ሜዳ›› በማዕድን ዙሪያ የሚሰራ ድርጅት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለድርጅታቸው የተለያዩ ድጋፎች ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰዋል፤ ድርጅቱ በክልሉ ማዕድን ከሚያወጡ ማህበራት ማዕድናት በመውሰድ እሴት በመጨመር የማስዋብና የማስጌጥ ሥራዎችን በመስራት ወደ ተለያዩ ጌጣጌጥነት እንደሚቀየር ይገልጻሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ ወደ እሴት መጨመር ሥራው ከመግባታቸው በፊት በስራው ላይ ያላቸው ውስን እውቀት ነበር። ‹‹ሜዳ ›› በተሰኘው የግብረ ሰናይ ድርጅት ድጋፍ በጎንደር ቴክኒክና ሙያ ተቋም አማካኝነት በማዕድናት ማስዋብና ማስጌጥ ሥራ (የላፒደሪ) ስልጠና አግኝተዋል። ስልጠናው የማእድናቱን አይነትና ባሕሪያት፣ እሴት ማከል፣ መቁረጥና ማስዋብ እና የገበያ ሁኔታን ያካተተ ነበር። የጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች የቢዝነስ ስልጠና እንዲያገኙም እድሉ ተመቻችቶላቸዋል። ከስልጠናው በኋላ ነው በማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ወደ ማስዋብና ማስጌጥ ሥራ የገቡት።

ማዕድናቱን በመቁረጥ፣ ከብር፣ ወርቅ እና ሌሎች ጌጣጌጦች ጋር በመስራት ጌጣጌጦችን የማምረት ሥራን አሃዱ ብለው እንደ ጀመሩ አቶ ፍቅሬ ያስታውሳሉ። እነዚህን ምርቶቻቸውን ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች ላይ በማቅረብ ያስተዋውቃሉ። በባህር ዳርና በአዲስ አበባ በተዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች ላይ ብዙ ጊዜ መሳተፍ ችለዋል፤ ይህም የገበያ ትስስር ለመፍጠር አስችሏቸዋል።

ኤግዚቢሽንና በባዛሮችን በአብዛኛው የገበያ ትስስሩን ለመፍጠርና ማዕድናቱን ለማስተዋወቅ እንደሚጠቅሟቸው ጠቅሰው፣ ማዕድናቱን በሀገር ውስጥ ገበያ በማስተዋወቅ ሕብረተሰቡ ስለ ማዕድናቱ ግንዛቤው እንዲሰፋ በማድረግ ምርቱ በሀገር ውስጥም ሰፊ ገበያ እንዲኖረው ማድረግ መቻሉን ይገልጻሉ። አግዚቢሽንና ባዛሮቹ ማዕድናቱን ከማስተዋወቅ በዘለለ ምርቶቻቸው በብዛት የሚሸጡባቸው ቦታዎች እንደሆኑም አስታውቀዋል፡፡

በየኤግዚቢሽኖቹና ባዛሮቹ እንድንሳተፍ የተለያዩ ድጋፎች ሲያደርግልን የቆየው አሁን የቆይታ ጊዜውን ያጠናቀቀው ሜዳ የተሰኘው ድርጅት ነበር የሚሉት አቶ ፍቅሬ፤ ድርጅቱ ለሥራው የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ድጋፎች እንዳደረገላቸውም አስታውቀዋል። እነዚህ ቁሳቁስ ምርታማነታቸው እንዲጨምር እንደሚያስችላቸው አስታውቀዋል። ማዕድናቱ ላይ እሴት መጨመር የሚያስችላቸው እና መሸጫ ቦታ ተከራይተው እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በጎንደር ቴክኒክና ሙያ ተቋም ወርክሾፕ ተፈቅዶላቸው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

አቶ ፍቅሬ እንዳብራሩት፤ የማዕድናቱ አይነት የተለያየ እንደመሆኑ እያንዳንዱ ተጠቃሚ የሚፈልገው ማዕድን አንድ አይነት ላይሆን ስለሚችል፣ ከሁሉም በአገሪቱ ከሚገኙ ከበሩ ማዕድናት ልዩ ልዩ ጌጣጌጦችን መስራት ይቻላል። ድርጅቱ በሁሉም አይነት ማዕድናት ላይ በሚባል ደረጃ እሴት በመጨመር የማስዋብና የማስጌጥ ስራ ይሰራል፤ የኦፓል ማዕድን ከዋጋ አንጻር በጣም ውድ በመሆኑ የድርጅቱ አቅም በፈቀደ መጠን የተወሰኑ የኦፓል ጌጣጌጦችን በመስራት ለገበያ ያቀርባል። በተለይ እንደ ጃስበር፣ ሞሳጌት፣ አሜቲስት፣ ኳርትስ እና የመሳሳሉ ከፊል የከበሩ ማዕድናት ከዋጋ አንጻር የተሻሉ ስለሆኑ፣ እነዚህ ላይ እሴት በማከል በብርና በወርቅ በመሰራት ለገበያ ያቀርባል።

ድርጅቱ በከፈል የከበሩ ማዕድናት ለጆሮ፣ ለአንገት እና እጅ ጌጥነት በሚውሉ መልኩ በመስራት ለሀገር ውስጥ ገበያ ያቀርባል። በሀገር ውስጥ ገበያም ቢሆን ግን አብዛኛዎቹን ማዕድናት የሚገዙት የውጭ ሀገር ዜጎች (ቱሪስቶች) ናቸው። በተለይ ማዕድናቱን የሚገዙ የውጭ ሀገር ዜጎች ማዕድናቱ በሀገር ውስጥ ባማረና ውብ በሆነ መልኩ ተሰርተው ሲመለከቱ በጣም ደስተኛ ሆነው እንደሚገዙ አቶ ፍቅሬ ይገልጻሉ፡፡

ማዕድናቱን በክልሉ ካሉ ወረዳዎች ቆፍረው ከሚያወጡ ማህበራት ጋር የገበያ ትስስር ፈጥረው እንደሚገዙ የሚጠቅሱት አቶ ፍቅሬ፣ ኦፓል ከወሎ ደላንታ አካባቢ ሌሎቹን ደግሞ በአቅራቢያቸው ካሉ ወረዳዎች እንደሚያገኟቸው ይገልጻሉ። በከፊል የከበሩ ማዕድናትን ግን በበቂ ሁኔታ ከአካባቢው እንደሚገኙም ያስረዳሉ፡፡

ድርጅቱ ከመነሻው ጀምሮ እሴት የተጨመረባቸውን የጌጣጌጥ ምርቶች ገበያውን እያሰፋ ለውጭ ገበያ እስከ ማቅረብ /ኤክስፖርት ማድረግ/ ደረጃ ለመድረስ ማቀዱን አቶ ፍቅሬ አስታውቀዋል። ለውጭ ገበያ የማቅረብ ስራ ደረጃቸውን የጠበቁ ማዕድናትን የማምረት ስራንም ይጠይቃል ሲሉ አመልክተው፣ ይህንንም አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ ኦፓል፣ ኤምራልድ፣ ሳፋየር፣ ሩቢ የተሰኙት የከበሩ ማዕድናት በዋጋ ውድ የሚባሉ በግራም እስከ 150ሺ ብር ይሸጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ጥራት ያለው ኦፓል በግራም ከሁለት እስከ ሶስት ሺ ብር እንደሚያወጣ ጠቅሰው፣ ድርጅቱ እነዚህን ማዕድናት ገዝቶ፣ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የአቅም ውስንነት እንዳለበትና ግብይቱ በሀገር ውስጥ ላይ መወሰኑን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ወርቅ የተለያዩ ደረጃዎች እንዳሉት ሁሉ የከበሩ ማዕድናትም የተለያየ ደረጃ አላቸው። ብርሃን የሚያስተላልፍና የማይስተላልፍ ወይም ድፍን በሚል ደረጃ ይወጣላቸዋል። ሁሉም ማዕድናት የራሳቸው የሆነ ባህሪም አላቸው። አንዱ ማእድን ከሌላው በባሕሪም፤ በዋጋ ከሌላው ይለያል።

አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጎች እሴት ያልታከለበት የከበረ ማእድን መግዛት እንደሚፈልጉ ተናግረው፣ እሴት ጨምረው ሀገራቸው ማሰራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ እሴት ተጨምሮባቸዋል የሚባሉ ጌጣጌጦች ክፍተት እንዳለባቸው እንደሚጠቁሙም አስታውቀዋል። ‹ እነሱ የተሟላ የማምረቻ ቁሳቁስ ወይም ቴክኖሎጂ እንዳላቸው አቶ ፍቅሬ ጠቅሰው፣ ማዕድኑን ወስደው አሳምረው በመሰማራትና በከፍተኛ ዋጋ ሊሸጡ የሚችሉበት አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል። ሌሎች የውጭ ዜጎች ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ እሴት የተጨመበረባቸውን የከበሩ ማእድናት ጌጣጌጦች ደስ ብሏቸው እንደሚገዙም ገልጸዋል።

አቶ ፍቅሬ እንዳስታወቁት፤ የከበሩ ማዕድናት በባሕሪያቸው አንጻር እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይታወቃል። ጠቀሜታቸውን የሚያወቁ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ዜጎች እየገዙ ይገለገሉባቸዋል። በተለይ የውጭ ሀገር ዜጎች ስለማዕድናቱ ባሕሪያት በጥልቀት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ይጠቀሙባቸዋል።

የኛ ሀገር ሕዝብ የከበሩ ማዕድናትን ከሚገዛ ወርቅና ብር ቢገዛ እንደሚመርጥ ይታወቃል፤ ይህም የሚሆነው ሲቸግረኝ እሸጠዋለሁ ብሎ ስለሚያስብ ነው›› የሚሉት አቶ ፍቅሬ፣ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ወርቅና ብር ያላቸውን ጠቀሜታ ተረድተው ቢጠቀሙባቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉ ጠቁመዋል። የሀገራቸውን ምርቶች በሚሄዱባቸው ቦታዎች ሁሉ የሚያስተዋወቁበት አጋጣሚም እንደሚፈጠር ተናግረዋል።

የማዕድናት ጌጣጌጥን በብዛት የሚፈልጉት ቱሪስቶች መሆናቸውን የገለጹት አቶ ፍቅሬ፣ በከበሩ ማእድናት ላይ እሴት የመጨመር ሥራ በሚያካሂዱት አካባቢ በርካታ ቱሪስቶች የክልሉን ጥንታዊ ከተማ ጎንደርን በተደጋጋሚ እንደሚጎበኙ አስታውቀዋል። ይህ ለድርጅቱ ምርቶች ጥሩ ገበያ ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ የታየው አለመረጋጋት ቱሪስቶች ወደ አካባቢው በላይ ባሳደረው አሉታዊ ተጽእኖ ሳቢያ ገበያው መቀዛቀዝ ማሳየቱን አመልክተዋል፡፡

አቶ ፍቅሬ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው በትዕዛዝ ላይ ተመስርቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይ አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጎችና ዲያስፖራዎች በሚልኩት ትዕዛዝ መሰረት የከበሩ ማእድናት ጌጣጌጥን እንደሚያመርት ተናግረዋል። እነዚህ የውጭ ዜጎችና ዲያስፖራዎች በተለይ ከልደት ቀናቸው ጋር አያይዞው ከከበሩ ማእድናት ጌጣጌጦች እንዲሰሩላቸው እንደሚፈልጉ አስታውቀው፣ እኛም በሚፈልጉት የማዕድን አይነት የፈለጉትን አይነት ጌጣጌጥና በፈለጉት ዲዛይን እንሰራለን ብለዋል።

ድርጅቱ ቀደም ሲል ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ትስስር በመፍጠር ይሰራ እንደነበር አስታውሰው፤ ከሌሎች ድርጅቶች ጋርም እንዲሁ እየተነጋገረ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። በቀጣይ የማዕድን ገበያውን በማስፋፋት በትብብር ከሚሰሩት ድርጅቶች ጋር በኦንላይን ገበያ ተደራሽ ለመሆን እየሰሩ መሆኑንም አስታውቀዋል። በቀጣይ እሴት የተጨመረባቸው የከበሩ ማእድናት ምርትና ምርታማነት በማሳደግ እንዲሁም የገበያ ተደራሽነቱን በማስፋት እነዚህን ጌጣጌጦችና ማዕድናት በቀጥታ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ድርጅቱ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አቶ ፍቅሬ ጠቁመዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ ዓለም ላይ የማይገኙ እጅግ የከበሩ ማእድናት በስፋት እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ ይህን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በተለይ በከበሩ ማእድናት ላይ እሴት በመጨመር ስራ የተሰማሩ አካላትን በመደገፍና ምርቶቹን ለውጭ ገበያ በስፋት በማቅረብ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬን ማግኘት እንደሚቻልም አቶ ፍቅሬ አመልክተዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም

Recommended For You