ብራዚል፣ ሩስያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን በጋራ ያሰባሰበው እና በእንግሊዘኛው ምኅጻረ ቃል (BRICS/ ብሪክስ) ተብሎ የሚጠራውን ህብረት፤ በአንድ ጎራ ተሰልፎ ዓለምን ወደ አንድ ቦይ እንድትፈስስ አማራጭ ያሳጣውን የምዕራቡ ዓለም ስብስብን ተገዳዳሪ ሆኖ የቀረበ ብቻ ሳይሆን፤ የዓለምን ሚዛን የማስጠበቅ ተስፋ የተጣለበት ስብስብ ነው።
ይሄ ህብረት ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅምና ተጽዕኖ ፈጣሪነቱን እያሳደገ የመጣ፤ በብዙ ሀገራት ዘንድም የአባልነት ጥያቄ እየጎረፈለት ያለ ሲሆን፤ ስብስቡን ለመቀላቀል ከቀረቡ በርካታ ጥያቄዎች መካከልም ለመጀመሪያ ጊዜ ስድስት ሀገራትን (ኢትዮጵያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አርጀንቲና፣ ኢራን እና ግብጽ) በአዲስ አባልነት ተቀብሎ የኅብረቱን አባላት ቁጥር ወደ አስር ማድረስ ችሏል።
ኢትዮጵያም በብራዚል፣ ሩስያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ በተመሰረተው የብሪክስ አባል ከሆነች ወራቶች ተቆጥረዋል። ከዓለም 47 ከመቶ የሚጠጋውን ሕዝብ ባቀፈው፤ ከዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ 30 በመቶ ድርሻ ባለው፤ በተናጥልም የባለግዙፍ ኢኮኖሚ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት ስብስብ በሆነው ኅብረት ውስጥ አባል ሆና መገኘቷም በብዙ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርጋት ነው።
በተለይም እንደ ሀገር ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ሀገራዊ ጉዞ መሳካት የሚያስፈልገውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ (ቴክኖሎጂ፣ ገንዘብ፣ የእውቀትና እና ሌሎችም አዎንታዊ ድጋፎች) ለማግኘት ትልቅ እድል የሚሰጣት ነው። በሁለትዮሽ በተለይም በባለብዙ ወገን የትብብር ሂደት ላይ የዲፕሎማሲ እና ሌሎች አቅሞችን በመፍጠርም በዓለም ኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚኖረንን ተጽዕኖ ፈጣሪነትና ተሰሚነት ከፍ የሚያደርግ ነው።
በዋናነት መሠረተ ልማት እና ቀጣይነት ያላቸው የልማት ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ለማድረግ በብሪክስ አባል ሀገራት ከተመሰረተው “ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ“ እንደ ሀገር ስትራቴጂክ ተጠቃሚነትን ይሰጣል። ያለብንን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመቅረፍም አማራጭ ይሆናል፤ አማራጭ የገንዘብ አጠቃቀም ሥርዓትንም ያሰፋል።
ከዚህም ባለፈ በፍጥነት እያደገ ላለው የሀገራችን ኢኮኖሚ፤ በኢንቨስትመንት፣ በኢኮኖሚ ትብብርና በንግድ ወሳኝ የሆኑ አዳዲስ ዕድሎች ይዞ ይመጣል። ሀገሪቱ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶች አልምታ ለመጠቀም የሚያስፈልጋትን ቴክኖሎጂ እና ሀብት በማሟላት ሂደትም አበርክቶ ከፍያለ አለው።
በተለይም በኅብረቱ የተመሰረተው ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ ፣ እንደ ሀገር የታቀዱ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ለማድረግ ያለብንን የሀብት ውስንነት ለመሻገር በምናደርጋቸው ጥረቶች ውስጥ የሚያጋጥሙንን አላስፈላጊ የፖለቲካ ጫናዎች በቀላሉ ተሻግረን ፕሮጀክቶቻችንን ማስፈጸም የምንችልበትን የተሻለ እድል የሚፈጥር ነው።
የሀገሪቱ የውጪ ፖሊሲ የሀገር እና የሕዝብ ጥቅምን የሚያስቀድም እና አካታችነትን መርሑ ያደረገ ነው። የብሪክስ አባልነቷም ከዚህ እውነታ የተቀዳ ሲሆን፤ ከሁሉም በላይ ለሀገር እና ለሕዝብ ዘላቂ ስትራቴጂክ ጥቅም ማስገኘትን ያስቀደመ ነው። ለዚህ ጉዞው መሳካት ደግሞ ወዳጆችን በማፍራት የጋራ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እውን የማድረግ ግብን ያስቀመጠ ነው።
እንደ ሀገር ከኋላቀርነት እና ከድህነት ፈጥነን ለመውጣት የምናደርገው ጥረት፤ ተለዋዋጭ በሆነው አሁናዊ ዓለም ያሉትን አማራጮች በሙሉ መጠቀምን የሚጠይቅ ነው። ከዚህ አንጻር መንግሥት ሀገሪቱን የብሪክስ አባል ለማድረግ የሄደበት መንገድ ጥልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ከመሆን ባለፈ፤ ነገዎቻችንን ብሩህ ለማድረግ ለጀመርነው አዲስ የታሪክ ጉዞም ተጨማሪ አቅም ነው።
ለዚህም በአፍሪካ ብሎም በዓለም በመንገደኞችና በጭነት አገልግሎት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ እንደ ሀገርም ለጎረቤት ሀገራት ጭምር በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርበው የታዳሽ ኃይል፤ ወጣት፣ የተማረና በቀላሉ ሊሰለጥን የሚችል የሰው ኃይል እና ሌሎችም አቅሞቿ ሀገሪቱን ለኢንቨስትመንትና ንግድ ሳቢ ያደርጋታል።
ለዚህ ተደማሪ አቅም በሚሆን መልኩም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለቢዝነስ ምቹ ለማድረግ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ የተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፤ ቴሌኮሙኒኬሽንና ፋይናንስን ጨምሮ ቁልፍ ሴክተሮች ላይ የተደረጉ ለውጦችና ማሻሻያዎች፤ በቅርቡም የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ ለማድረግ የተወሰደው እርምጃ እና ሌሎችም ተግባራት ሀገሪቱን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ የሚያደርጋት ነው።
እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች የአባል ሀገራቱ ባለሀብቶች እንደ እድል ወስደው በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በታዳሽ ኃይል፣ በማዕድንና በቱሪዝም መስኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያነቃቃ ነው። ከዚህም ባለፈ ብዙዎቹ የብሪክስ አባል ሀገራት በቴክኖሎጂና በኢኮኖሚ ትልቅ አቅም የፈጠሩ መሆናቸው፤ ኢትዮጵያ ኅብረቱን መቀላቀሏ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ትልቅ እድል ይፈጥርላታል።
በመሆኑም በእነዚህና በሌሎች ብዙ ምክንያቶች ዛሬ ላይ እንደ አንድ የብሪክስ አባል ሀገር በህብረቱ ውስጥ ያለን ተሳትፎ፣ ጅማሬውም ሆነ ፍጻሜው የሀገር እና የሕዝብን ተጠቃሚነት እውን ማድረግ እንደመሆኑም፤ ለጀመርነው በልማት ድህነትን ታሪክ የማድረግ አዲስ የታሪክ ምእራፍ ተጨማሪ አቅም የመፍጠር ስትራቴጂክ ጉዞ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም