በመዲናዋ የአካባቢ ብክለት ባስከተሉ 701 ተቋማት ላይ ርምጃ ተወሰደ

  • ፎቅ ላይ ጭፈራ ቤት ከፍተው የድምጽ ብክለት የሚያስከትሉ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል

አዲስ አበባ፡– በመዲናዋ በ2017 በጀት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የአካባቢ ብክለት ባስከተሉ 701 ተቋማት ላይ ርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ ከፍ ባለ ቦታዎች በተለይም ፎቅ ላይ ጭፈራ ቤት ከፍተው የድምጽ ብክለት የሚያስከትሉ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ባለስልጣኑ አሳስቧል።

ባለስልጣኑ የ2017 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም መድረክ አካሂዷል፤ በተጨማሪ “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሃሳብ ላለፉት ስድስት ወራት ሲያካሂድ የቆየውን አካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ የማጠቃለያ ሪፖርት ትናንት አቅርቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ እንዳስታወቁት፤ በመዲናዋ በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 701 የአካባቢ ብክለት ባስከተሉ ተቋማት ላይ ርምጃ ተወስዷል፡፡

የአካባቢ ብክለት ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ከማጠናከር አንጻር ባለፉት ሦስት ወራት በሁለት ሺህ 316 ተቋማት ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች መሰራቱን አስታውሰዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሦስት ወራት 190 በላይ የአካባቢ ብክለት ይወገድልኝ አቤቱታዎች ከህብረተሰቡ መቅረባቸውን ጠቁመው፤ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የድምጽ ብክለት መሆናቸውን አቶ ዲዳ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ከከፍታ ላይ የሚሰማ ድምጽ ብዙ ቦታ የሚረብሽ በመሆኑ ፎቆች ላይ ጭፈራ ቤት የሚከፍቱና የተለያዩ የድምጽ ብክለቶች የሚያስከትሉ ተቋማት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የድምጽ ብክለትን ለመከላከልም አራት የባለሙያ ቡድኖች ተዋቅረው በሦስት ቀናት ውስጥ ከ200 በላይ ቤቶች ላይ የቁጥጥር ስራ አከናውነው ከሚጠበቀው መስፈርት በላይ የድምጽ ብክለት ያስከተሉት ተለይተው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የአካባቢ ብክለት ለመከላከል፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋም የሚችልና ስነ-ምህዳሩ የተጠበቀ ከተማ ለመገንባት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ዲዳ ገልጸዋል።

በስድስቱ ወራት የተከናወኑት የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ ስራዎች ህብረተሰቡ ስለ አካባቢ ብክለት ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ጠቁመዋል።

በስድስት ወራት የተካሄደው የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ መደበኛ ሥራ ሆኖ ይቀጥላል ያሉት አቶ ዲዳ፤ በቀጣይም የአካባቢ ብክለት የመከላከል ሥራው በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ዲዳ ገለጻ፤ በከተማው እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች የመዲናዋን የአካባቢ ብክለት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You