ለትራንስፖርት ዘርፍ ታዳሽ የኃይል አማራጭን ያቀረቡት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች

ኢትዮጵያ ከመኪና ጋር የተዋወቀችው ከ115 ዓመታት በፊት፣ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው። በ1900 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያና የመኪና ትውውቅ፣ ብዙ ደረጃዎችን አልፎ ዛሬ ካለበት ደርሷል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ተሽከርካሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እድሜያቸው የገፋ (አሮጌዎች) እና ከፍተኛ የነዳጅ ፍጆታ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በነዳጅ ከሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች የሚወጣውና ለአየር ብክለት ከፍተኛ ድርሻ ያለው ጭስ፣ ለአካባቢ ስነ ምኅዳር ትልቅ አደጋ ሆኖ ቀጥሏል።

የነዳጅ ዋጋ መጨመር ያደጉትንም ሆኑ ታዳጊ ሀገራትን አማራጭ የትራንስፖርት ዘርፎችን እንዲያማትሩ እያስገደዳቸው ነው። ከእነዚህ አማራጮች መካከል አንዱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ነው። ቻይና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በብዛት በመጠቀም ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በየጊዜው በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እየተሻሻሉና ተጠቃሚያቸውም እየጨመረ ይገኛል። ተሽከርካሪዎቹ በነዳጅ ከሚንቀሳቀሱት ተሽከርካሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ የራሳቸው የሆኑ ጥቅሞች አሏቸው። ለአብነት ያህል ከወጪ አንፃር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹን ባትሪ ሙሉ (Full) ለማድረግ የሚፈጀው ወጪ፣ የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ከሚፈልጉት ወጪ በ24 በመቶ ይቀንሳል።

ተሽከርካሪዎቹ ለመንቀሳቀስ የሚጠቀሙት በሀገር ውስጥ የተመረተ የኤሌክትሪክ ኃይል ነው። የሀገር ውስጥ ኤሌክትሪክ የሚገኘው ደግሞ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች ስለሆነ ይህ ዓይነቱ የኃይል አጠቃቀም እንደሀገር ጭምር ለነዳጅ የሚጣውን ወጪ ለመቀነስ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ከዚህ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምንም ዓይነት ጭስ ወደ ከባቢ አየር የማይለቁ በመሆናቸው የአየር ብክለትን በማስወገድ የአካባቢ ጥበቃን አስተማማኝ ለማድረግ ያስችላሉ።

ኢትዮጵያም በየዓመቱ ለነዳጅ ግዢ ከፍተኛ ገንዘብ ታወጣለች፤ይህም በውጭ ምንዛሬ ክምችቷ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። በሀገሪቱ የሚገኙት አብዛኞቹ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ የነዳጅ ፍጆታ ያላቸው በመሆናቸው ከተሽከርካሪዎቹ የሚወጣው ጭስ ለአየር ብክለት ምክንያት በመሆን በከፍተኛ ደረጃ ይጠቀሳል። እነዚህን ፈተናዎች ለመቀየር ከተጀመሩት ስራዎች መካከል አንዱ የማበረታቻ ስርዓቶችን በመዘርጋት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትና አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ነው፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥትም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ ከሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ ያላቸውን አንፃራዊ ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩ ኢንዱስትሪዎችንና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል። የታክስ ማሻሻያው ዓላማ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የተሽከርካሪዎች ቁጥር በፖሊሲ ማሕቀፍ ከአካባቢ ደህንነት ጋር የሚስማማ ለማድረግ፣ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የማያስከትል፣ በአየር ንብረትና በብዝሃ ህይወት ላይ ተጽእኖ የማያሳርፍ እና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በአግባቡ የሚጠቀም የመጓጓዣ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲቀርቡ ለማስቻል እንደሆነም መገለፁ ይታወሳል፡፡

በዚህ የታክስ ማሻሻያ ከውጭ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት አውቶሞቢሎች እና የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ዝቅተኛ የጉምሩክ ታሪፍ የሚጣልባቸው ሲሆን ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይዝ ታክስና ከሱር ታክስ ነፃ ይደረጋሉ። በታክስ ማሻሻያው መሰረት የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎችን በተመለከተም ሙሉ በሙሉ ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎች ከጉምሩክ ቀረጥ፣ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

በከፊል ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎች አምስት በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን፣ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል። ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው ያለቀላቸው የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ወደ ሀገር ሲገቡ ደግሞ 15 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተወስኗል። የታክስ ማሻሻያው ከተደረገ በኋላም በርካታ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ በመገጣጠም እና ከውጭ በማስመጣት ለገበያ የሚያቀርቡ ድርጅቶች አሉ። መኪኖቹን በሀገር ውስጥ በመገጣጠም ለገበያ ከሚያቀርቡት ድርጅቶች መካከል ‹‹በላይነህ ክንዴ ግሩፕ›› አንዱ ነው። ድርጅቱ ደብረ ብርሃን እና ገላን በሚገኙ ፋብሪካዎቹ የኤሌክትሪክ ሚኒባሶችንና አውቶቡሶችን በሀገር ውስጥ ገጣጥሞ ለገበያ በማቅረብ ፈር ቀዳጅ ተቋም መሆን ችሏል።

የ‹‹በላይነህ ክንዴ ግሩፕ›› የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰጠኝ እንግዳው እንደሚናገሩት፣ ድርጅቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እየገጣጠመ ለገበያ ማቅረብ የጀመረው ባለፈው ዓመት (በ2016) ነው። ‹‹ድርጅታችን ‹በላይነህ ክንዴ ግሩፕ› ከተሰማራባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች መካከል አንዱ የአውቶሞቲቭ ዘርፍ ነው። በአውቶሞቲቭ ዘርፍ ስራ ከጀመረ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል። በእነዚህ ዓመታት የደረቅና ፈሳሽ ጭነት መኪኖችን፣ በተለይም የ ‹IVECO› ብራንድ መኪኖችን እየገጣጠመ ለገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ደግሞ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ገጣጥሞ ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ አመልክተው፣ በመጀመሪያው ዙር 15 ሰው የመያዝ አቅም ያላቸውን፣ በአንድ ጊዜ ቻርጅ ከ270 እስከ 350 ኪሎ ሜትር ድረስ መጓዝ የሚችሉ 216 የኤሌክትሪክ ሚኒባሶችን ገጣጥመን ለገበያ አቅርበናል ብለዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ሚኒባሶቹ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋሉ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 150 የሚሆኑትን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማቅረብ የተለያዩ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ሴክተር ተቋማት እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። ሌሎች ተቋማትም መኪኖቹን ገዝተው ጥቅም ላይ አውለዋቸዋል። የደብረ ብርሃኑ ፋብሪካ በቀን አራት ሚኒባስና ሁለት አውቶቡሶችን እንዲሁም የገላኑ ደግሞ በቀን አራት ሚኒባሶችን የመገጣጠም አቅም አላቸው።

አቶ ሰጠኝ እንደሚገልፁት፣ ድርጅቱ ከኤሌክትሪክ ሚኒባሶች በተጨማሪ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችንም እየገጣጠመ ለገበያ እያቀረበ ነው። በአሁኑ ወቅት እስከ 70 ሰው የሚይዙ 10 የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች ለገበያ ቀርበዋል። የመጀመሪያዎቹን አራት የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስረክቧል። ሁለት ተጨማሪ አውቶቡሶች ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በቅርቡ ተጨማሪ አውቶቡሶች እና 120 የኤሌክትሪክ ሚኒባሶች ተገጣጥመው ለገበያ ይቀርባሉ።

ድርጅቱ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችንና ሚኒባሶችን ገጣጥሞ ለገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ፣ በኤሌክትሪክ መኪኖች የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ነው። የኤሌክትሪክ መኪኖችን ወደ ስራ ይዞ ገብቷል። ‹‹ቬሎሲቲ›› በሚባል የድርጅቱ እህት ኩባንያ አማካኝነት 20 ሚኒባሶችንና ሁለት አውቶቡሶችን ይዞ በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አገልግሎት ላይ የማዋሉ ተግባር ስኬታማ እንዲሆን ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል አንዱ ለተሽከርካሪዎቹ ኃይል የሚያቀርቡ የባትሪ መሙያ ጣቢያዎችን (Charg­ing Stations) መገንባት ነው። በርካታ ግለሰቦችና ተቋማት የእነዚህን መሰረተ ልማቶች እጥረትን እንደዋና የዘርፉ ተግዳሮት አድርገው ሲጠቅሱት ይስተዋላል። ‹‹በላይነህ ክንዴ ግሩፕ›› ገጣጥሞ ለገበያ የሚያቀርባቸው የኤሌክትሪክ መኪኖች የቻርጀርና የመለዋወጫ እጥረት እንደሌለባቸው አቶ ሰጠኝ ይገልፃሉ። ድርጅቱ በዓለም ላይ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ ቻርጀሮችንም ከቻይና በማስመጣት ለገበያ ማቅረቡን አስታውቀዋል።

‹‹በሀገር ደረጃ ያለው አንዱ ችግር የኤሌክትሪካ ቻርጀሮች በበቂ ሁኔታ አለመኖር ነው። የኤሌክትሪክ መኪና ስላስመጣን ብቻ የኤሌክትሪክ መኪኖቹን መንገድ ላይ እናያለን ማለት አይደለም። ባትሪያቸው የሚሞላበት ቻርጀር ያስፈልጋል። የኤሌክትሪክ መኪኖች ሁለት ዓይነት ቻርጀሮች አሏቸው። አንደኛው ሁሉም ሰው በቤቱ ውስጥ ከሚገኝ የኃይል ምንጭ ባትሪ ሊሞላበት የሚችለው ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በአጭር ጊዜ (ቢበዛ በ45 ደቂቃ) ባትሪ የሚሞሉ ፈጣን ቻርጀሮች (Fast Char­gers) ናቸው›› ሲሉ አቶ ሰጠኝ ያብራራሉ።

‹‹በመጀመሪያ ከ60 እስከ 180 ኪሎ ዋት ከፍተኛ አቅም እንዲሁም ዋስትና ያላቸውን 120 ፈጣን ቻርጀሮችን አስመጥተናል። መኪና ለሚገዙም ሆነ በቻርጀር አቅርቦት ላይ ለተሰማሩ አካላትም እያቀረብን ነው። የስልጠና አገልግሎትም እንሰጣለን›› ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ ከመንግሥት ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ቻርጀሮችን ለመግጠም ስራ እንደጀመረም ጠቁመዋል።

አቶ ሰጠኝ እንዳብራሩት፤ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ተጠቃሚነት የማበረታታት ሀገራዊ እቅድ የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖረው የኤሌክትሪክ መኪኖቹ ጥንካሬ ኖሯቸው በተሻለ ጥራትና አስተማማኝነት ለገበያ እንዲቀርቡ ይደረጋል። የሚገጣጠሙት የመኪኖቹ ክፍሎች ከመሰራታቸውና ወደ ሀገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ከኢትዮጵያ የአየር ፀባይ ጋር ተስማሚ እንዲሆኑ ጥናት ተደርጓል። ለሞተር መቀመጫ የሚሆኑት ቦታዎች ከኢትዮጵያ የመሬት አቀማመጥ፣ የመንገድ ሁኔታ ጋር የሚስማማ መሆኑም ተጠንቷል። ድርጅቱ መኪኖቹን ለገዢዎች ሲያስረክብ ስልጠናና ዋስትና ይሰጣል። ደንበኞች መኪኖቹን ከወሰዱ በኋላም በድርጅቱ ባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ ይደረግላቸዋል።

በነዳጅ ዋጋ መጨመርና በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምክንያት የኤሌክትሪክ መኪኖች ፍላጎት እየጨመረ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ ሰጠኝ፣ እንደሀገር ደግሞ ታዳሽ ኃይልን በስፋት ከመጠቀም አንፃር የኤሌክትሪክ መኪኖችን የመጠቀም ፍላጎት እያደገ እንደሚሄድ ያላቸውን እምነት ይገልፃሉ። ‹‹በላይነህ ክንዴ ግሩፕ››ም በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ መኪኖች ልማት ላይ በስፋት በመሳተፍ በሀገር ደረጃ የራሱን አሻራ የማሳረፍ እቅድ እንዳለው ይናገራሉ። የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለማስፋፋት በመንግሥት በኩል ያለው ጥረት አበረታች መሆኑ ለዚህ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ገልፀው፣ ኃይል አቅርቦትን ማሻሻል፣ መሰረተ ልማቶችን (በተለይም የባትሪ መሙያ ጣቢያዎችን) ማሟላት እንዲሁም ኅብረተሰቡ ስለኤሌክትሪክ መኪኖች ያለውን አስተሳሰብ ማሳደግ እንደሚገባም ይመክራሉ።

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ይዘንጋው ይታይህ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ካላቸው አካባቢያዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ አንፃር መንግሥት ተሽከርካሪዎቹ በሀገር ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያበረታቱ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ይገልፃሉ።

ይህን ለማሳካትም ስትራቴጂዎች፣ የማበረታቻ ስርዓቶች እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ስታንዳርዶች ተዘጋጅተዋል። ስትራቴጂው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እንዲሁም በሀገር ውስጥ እንዲገጣጠሙና በስፋት ጥቅም ላይ እንዲዉሉ ያበረታታል። ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችና መሰረተ ልማቶቻቸው በአነስተኛ ታክስ ብሎም ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል።

መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማበረታታት በወሰዳቸው እርምጃዎች ምክንያት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር እንደጨመረ የሚጠቁመት አቶ ይዘንጋው፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ የሚገጣጥሙ ድርጅቶች 15 እንዲሁም ተሽከርካሪዎቹን የሚያስመጡት ደግሞ ከ200 በላይ እንደሆኑ ይገልፃሉ። ከዚህ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ወጭንና የአካባቢ ብክለት በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ ጥቅም ስላላቸው፣ ኅብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ሊጠቀም እንደሚገባም አቶ ይዘንጋው ይመክራሉ።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You