ኢትዮጵያ የምትሻው ሰላምንና ወንድማማችነትን ነው

የሰው ልጅ ከራሱ አልፎ ፍቅርን ፣ወንድማማችነትን እነ ሰላምን ከእንስሳት መማር ይችላል። ለመማር የፈለገ ማለቴ ነው። በተለይም ለሰው ልጆች አብሮ ለመኖር እና ኑሮንም በደስታ ለማሳለፍ ሰላም የማይተካ ሚና አለው። ሰላም ሁሉም ነገር ማጠንጠኛ ነው። አርሶ ለመብላት፣ወልዶ ለማሳም ፣ነግዶ ለማትረፍ፣ተምሮ ለመመረቅና እና ሥራ ለመያዝ ሰላም መሰረታዊ ነገር ነው።

ሆኖም ይህንን እውነታ በመዘንጋት ዓለም ሰላሟን ካጣች ውላ አድራለች። በአራቱም ማእዘናት የሚተኮስ ጥይት፣የሚፈናዳ ፈንጂ የትየለሌ ነው። በዚህም የሰዎች ሕይወት ይቀጠፋል፣ አካል ይጎድላል፣ስደት እና መፈናቀል ይበዛል፣የሰዎች ሕይወት ይመሰቃቀላል፣ይህቺ ዓለምም ገሃነም ትሆናለች። በዚህ ውስጥ ደግሞ ሴቶችና ህጻናት የበለጠ ተጎጂዎች ይሆናሉ፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም 126 የሚጠጉ ሀገራት በሳል እጦት ውስጥ ይገኛሉ። በዚህም ዓለማችን ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እና ሰብአዊ ኪሳራዎችን እያስተናገደች ትገኛለች። ጦርነት እና ግጭቱ በፈጠረው ምስቅልቅል ምክንያት ሸቀጦችን ከአንዱ አህጉር ወደሌላው መጓጓዝ አዳጋች ሆኗል። የሰዎች ዝውውርም ተገድቧል። በዚህም የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር እና የኑሮ ውድነት በዓለም ደረጃ እንዲባባሳ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከኑሮ ውድነቱ ባሻገር የሰው ልጅ እርስ በራሱ ሲጫረስ ማየት ያሳዝናል። ህጻናት በየቦታው ወድቀው፤አረጋውያን ተጎሳቁለውና እና የጥይት እና የቦንብ እራት ሆነው መመልከት በእጅጉ ያሳቅቃል። ድርጊቱም የሰው ልጅ ከእንስሳት ያነሰ ወንድማማችነት እና አንድነትን እያጣ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡

ውሻ ለማዳ የቤት እንስሳ ሲሆን ከቀበሮ፣ ተኩላ እና ጅብ ተዛማጅ ነው፤የከሳቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ውሻ የቤት እንስሳ ቤትን የሚጠብቅ ሲለው ተኲላን ደግሞ ሥጋን የሚበላ የጅብ የቀበሮ የውሻ ዘመድ በቆላ በሙቀት ሀገር የሚኖር በግን ፍየልን እየነጠቀ የሚበላ በሚል ይፈታዋል፡፡ቀበሮንም እንደ ውሻ ያለ በግ የሚበላ ጉድጓድ እየቆፈረ የሚኖር ይለዋል፡፡

ውሻ ከሰዎች ጋር ረጅም ዘመን ከኖሩና ካገለገሉ የቤት እንስሳት ይጠቀሳል። የሚለየው ከበድ ያለ ሥራ የማይጠበቅበት መሆኑ ነው። አንዳንዶች ግን ለአሳዳሪዎቹ ጭራውን እየቆላ የሚኖር ይሉታል። እርግጥ ነው በአንዳንድ ሀገሮች ቤትና ንብረትን መጠበቅ ሰራቂን መጠበቅ ጭምር ነው። ሰዎች ውሻን ሲያሳድጉት ቤት እንዲጠብቅላቸው ሌባ እንዲይዝላቸው ነው። ከዚህ አልፎ በዘመናችን ውሻ እየሠለጠነ ለፖሊስ አጋዥ እየሆነ ነው። በተጨማሪም በፖሊስ ሰልጥኖ ድንበሮችንና የጉምሩክ ቦታዎችን ይጠብቃል። እንደ አደንዛዥ ዕጽ፣ የጦር መሣሪያ የመሳሰሉ መሣሪያዎችን ከተደበቁበት ያጋልጣል።

በእኛም ሀገር በፖሊስ የሠለጠኑ ውሾች አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ተይዘው፤የተደበቁ የጦር መሣሪያዎችን የተቀበሩ አደንዛዥ ዕጾችን ያጋልጣሉ። ለፖሊስ አገልግሎት በአጋዥነት የሚሰለጥነው ውሻ፤ በቁመቱ ዘለግ ያለ እንደ ተኩላ ዓይነት ቁመና ያለው ነው።

አሜሪካ ብቻ በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ውሾችን ከሌሎች ሀገራት የምታስገባ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ አሁን ከፍተኛ የእብድ ውሻ ስጋት አለባቸው ተብለው እገዳ ከተጣለባቸው ሀገራት የሚመጡት ውሾች መጠን 60 በመቶውን እንደሚሸፍን መረጃዎች ያሳያሉ። አሜሪካ ውስጥ ውሾች በመደበኛነት የሚከተቡ ሲሆን የእብድ ውሻ በሽታ ከ15 ዓመት በፊት ከሀገሪቱ እንደጠፋ ይነገራል።

በሳይንስ እንስሶች በሦስት እንደሚከፈሉ ይነገር ነበር። ሣርና ቅጠል በል Herbivorous ሥጋ በል (Carnivorous) እና Omnivorous ሁለቱንም የሚበሉ። በወቅቱ ትምህርት ሥጋም አረንጓዴ ቅጠልም የሚበላው ሰው ብቻ ነበር። ግን ዘግይቶ ስንረዳው ድመትና ውሻም ቅጠላ ቅጠሉንም ሥጋውንም ይበላሉ፤ ቅጠላ ቅጠሉን ስል ደግሞ እንደ በግና ፍየል ሣር እየነጩ ውሃ እየተጎነጩ ይኖራሉ አለማለቴ ይሰመርበት። ያው ቂጣውን ዳቦውን እንጀራውን ጣል ሲደረግላቸው ይበላሉ ለማለት ነው። አይጥም ስትፈልግ እንጨቱን በጥርስዋ ትነጨዋለች በቤት ያለ የሚበላም የማይበላም በመብላት ቀዳሚ ነች። አዲስ ልብስ ገዝታችሁ ስታበቁ የቆዳም ይኹን የጨርቅም በጥርስዋ በመቦጨቅ ማን ይችላታል? እርሷም እንዲሁ በኔ እሳቤ ሥጋውንም ቅጠሉን ከሚበሉ የምትመደብ ነች።

በመዲናችን ብቻ በ2012 በወጣ መረጃ ሩብ ሚሊዮን የሚጠጉ ውሾች ይገኛሉ፤ አብዛኞቹ ደግሞ ጎዳና ተዳዳሪዎች (ባለቤት አልባ) ናቸው ውሻ የእብድ ውሻ በሽታን Rabbis በማስፋፋት ትታወቃለች። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየጨመረ የመጣውን የባለቤት አልባ ውሾች ቁጥር ለመቀነስ ሴት ውሾችን እንዳይወልዱ የማምከን ሥራ ቢሠራ ሸጋ ነው። በሽታው ለሰዎችም ሆነ ለሌሎች እንስሶች ጠንቅ ስለሆነ በቀደሙት ዘመናት በመዲናዋ፤ጎዳና ተዳዳሪ ውሻ አይገኝም ነበር። አሁን እናቴ መዲናው ሰፍቶ ፓስተርም ውሾቹን ለማስወገድ ተቸገረ። ቀደም ሲል በተለምዶ ፓስተር የሚባለው ጤና ተቋምና ማዘጋጃ ቤት በሌሊት በየሠፈሩ እየዞሩ ውሾችን ገድለው በመኪና ጭነው ይሄዱ ነበር። አሁን በግል ግቢያቸው ውሻ ያላቸው በተወሰኑ ወራት ልዩነት ወደ ፓስተር እየወሰዱ ውሾችን ያስከትባሉ። በአንዳንድ ብሔራዊ ፓርኮችም የቤት ውሾች ከፓርክ እንስሶች ጋር የሚገናኙባቸው አጋጣሚዎች ስላሉ ቀይ ቀበሮ፣ ዋሊያ የመሳሰሉ ውድና ብርቅ እንስሶቻችንንም እንዳናጣቸው የሚመለከታቸው አካላት እንዲመለከቱት አመለክታለሁ።

ውሾች የሚበሉት ሲያገኙ እርስ በርስ ሊባሉ ይደርሳሉ። ግን ሌባ ሆነ ጅብ በአካባቢያቸው ቢመጣ ልዩነታቸውን ጥለውት በኅብረት ሊያጠቁትና ሊያባርሩት ይጮኹበታል። በክረምት ወራት ውሾች ሙቀት ለማግኘትና ዓለማቸውን ለመቅጨት ተሰብስበው ይሳረራሉ፤ሲጮሁ ያድራሉ፤ እርስ በርስም የሚጣሉበት አጋጣሚ አለ። ሰው የሚሞት ከሆነም በመጮህና በማላዘን ሌሊቱን ስለሚረብሹት አዋቂ ሰዎች በሠፈሩ የሚሞት ሰው አለ ማለት ነው ይላሉ። በጎዳና ተዳዳሪዎች ዘንድ ውሻ ሌሊት በሚያድሩበት አይለያቸውም በ‹ቴክኒክ› ስህተት ባመሸሁባቸው ቦታዎች ውሾች ጎዳና ተዳዳሪዎች ከተኙበት ጎን ወይም ባደረቡት ልብስ ላይ ሲተኙ አይቻለሁ።

በገጠር ከብቶች በበረት እህል በጎተራ ስላለ ውሻ ሌሊት ከጅቦችም ከቀማኞችም ሀብቱን ከብቱንም በሉት ኩበቱንም ይጠብቃሉ። ጅብ ሲመጣ እንደሚጠቃ ስለሚሰጋ በጥንቃቄ ሳይጠጋ ይጮሀል። ተረቱም ‹‹ውሻ ካልቀበጠ ጅብ አይበላውም›› ይላል። በአንዳንድ ገጠሮች ከአንጀት ጋር ተደርጎ በሚሰጣቸው ቂጣ ለጅብ ፈሪ ሳይሆን ዐይን አውጣ ሆነው ይገኛሉ። ጅብም ሊበላቸው አይደፍርም የሚሉ ሰምቻለሁ። ብዙ ውሾች ከሆኑም አንዱን ጅብ አሳደው ነካክሰው ማባረርና መብላት ይችላሉ።

በርዘመሃር የተባለ ፈላስፋ፤ ውሻ አንዳንዴ የሚልከሰከስና ርኩስ ተብሎ ቢናቅም ስድስት ነገሮች ገንዘብ ያደረገ ነው ይላል። ፍቅር፣ ትህትና፣ መስማማት፣ ልቦና፣ ተስፋ እና ምስጋና ናቸው። ርኩስ ተብሎ የሚናቀው ውሻ ከላይ የጠቀስናቸውን ጠባያት ያሳያል። ሰው ግን አንዳንዴ ስሜታዊ ሆኖ የተጠቀሱትን ጠባያት ባለመተግበር ከውሻ አንሶ ይገኛል። በሀገራችን ለውጥ የመጣው ነውጥ ስለተከሰተና ሕዝብ ግጭት በቃኝ ስላለ ነው፤ለውጥ ሲመጣ ደግሞ ዜጋው እንደ ውሻ ወደ ጥፋቱ (ውሻ ያስታወከውን ምግብ መልሶ እንደሚልሰው) መላስና መመለስ አማረው። ይህ ከውሻ ማነስ ነው። በየቦታው የጎበዝ አለቃ መሆን ያማራቸው ነፍጥ እያነገቡ የሚያቅራሩትና ሁከት የሚፈጥሩት ሰው የሚያግቱት ፈራንካ የሚጠይቁት ጥቅማቸውንም ሽተው ነው። በየጫካው ሰው የሚያግቱ ይገቱ እንጂ ወንበር ከያዙ ዲክታተር እንደሚሆኑ ዕኩይ ድርጊታቸው ማሳያ ነው።

ውሻ ቢሰድቡት ቢደበድቡት እስኪሞት ከጌታው ቤት አይለቅም፤ መስማማቱ ነው። ውጣ ቢሉት ይወጣል፤ ቁጣውን በትዕግሥት ተቀብሎ ይሄዳል እንጂ ተቆጡኝ ብሎ ጌታውን አይጠላም ልቦናው ይኽ ነው። ውሻ ውጣ ሲሉት ይወጣል፤ ና ሲሉት ይመጣል ይህ ትህትናው ነው። ውሻ በመጮህ እየዞረ የጌታውን ቤት ተግቶ ነቅቶ ይጠብቃል ማመስገኑ ነው። ጌታውን ሲያይ ጭራውን እየቆላና እየቆለመመ ራሱን እያጎነበሰና ቀና እያደረገ መተሻሸቱም ፍቅሩን ሲገልጽ ነው፡፡

የሰው ልጆች ጎጥን እምነትንም ሆነ ፖለቲካን ተገን አድርገው እርስ በርስ ሲጣሉ ችግራቸውን መፍታት የሚፈልጉት በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ሳይሆን በጦርነትና በግጭት ነው። እገሌን በሉት ገለመሌ፤ የወንዜ ልጅ በሉት የመንዜ ፤ በጎሳ መጠዛጠዝ፣ መመዛመዝ የሚሉት ዕኩይ አባዜ ይታይባቸዋል።

የብሔር ሰበዝ እየመዘዙ ሊያጋጩን የሚሞክሩ እንዳያፍሩ ይጠንቀቁ። ጉዳዩ በቀላሉ የሚተው ስላልሆነ ትኩረት ይሰጠው። በአንዳንድ ቦታ ጥፋተኞች ሲያዙ ይታያል፤ጥፋተኞች ተጠያቂ መሆን ያልቻሉባቸው ቦታዎች አሉ። ፍትሐዊነት ለሁሉም ይዳረስ፡፡

ብሔር ጠል እሳቤዎች ግጭቶችና ሁሉንም አክሳሪ እንጂ አትራፊ አለመሆኑን መገንዘብ ያሻናል። ግጭቶች መንግሥት አይታገስም በሚል መግለጫ ብቻ አይፈቱም። የብሔር ግጭት ሲቀጣጠል ብዙሃኑ በእሳቱ እንደሚለበለብ መገንዘብ ይገባል። ግጭቶቹ በተነሱባቸው ክልሎች ፍትሐዊነት ነግሦ ጥፋተኞች ሁሉ ለፍርድ ሲቀርቡ ማየት እንሻለን። አንዱን እየከሰሱ ሌላውን እያሞገሱ ግዜ መግዛት ግጭት ማባባስ ይመስለኛል። የሚፈለገው የሕዝብ እንባ የሚያባብሱ ሳይሆን የሚያብሱ ነው። በሀገራችን ያለው ግጭት ይህንኑ የሚያስተምረን ነው። መናቆርን ጥለን ፍቅርን አንጠልጥለን መሄዱ ተመራጭ ነው። በመንግሥት ዙሪያ እየተሰማ ያለው ብሔራዊ ምክክር ብዙሃኑን አካታች ሆኖ፤ ግጭቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ፈተን ፍቅር ትህትናን መስማማትን ልቦና ተስፋና ምስጋናን ገንዘብ ለማድረግ ከላይ ከጠቀስናቸው ግን ከምንንቃቸው ውሾች እንማር።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀግንነቱን ያህል ሰላም ወዳድም ነው። በየትም ሥፍራ ቢኖር፣ የትኛውንም እምነት ቢከተል፣ በተለያዩ ቋንቋዎች ቢገለገል፣ ባህሎቹና ልማዶቹ ቢለያዩም ለሰላምና አብሮነት ሰፊ ቦታን ይሰጣል፡፡ሰላም የእሴቶቹ አንዱ መገለጫ ነው።

ሆኖም ከዚህ የኢትዮጵያውያን ባህል ባፈነገጠ መልኩ ፍላጎታቸውን በነፍጥ ማሳካት የሚፈልጉ ብድኖች እየተበራከቱ መጥተዋል። ከውይይት ይልቅ ነፍጥ ማንሳት የሚቀናቸውና ሰላም ወዳዱን ህዝብ የሚረብሹ፤አብሮነቱን የሚያውኩ፤ የኢትዮጵያን መረጋጋትና ሉአላዊነት የሚገዳደሩ ቡድኖች እዚህም እዚያም አቆጥቁጠዋል፡፡

እነዚህ ወገኖች በሚፈጥሩት ሁከትና ብጥብጥም ልማት ተደናቅፏል፤የሰዎች ወጥቶ መግባት ተስተጓጉሏል፤አለፍ ሲልም የሀገር ህልውናም አደጋ ላይ ወድቋል። ስለዚህም ነፍጥ አንስቶ ይዋጣልን ማለት ጊዜ ያለፈበት ጀብድ መሆኑን መረዳት ይገባል።

ይቤ.ከደጃች ውቤ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You