እግር ኳሱን የማነቃቃት ትልቅ ርምጃ!

ስፖርት ረቂቅ ነው፤ ምክንያቱም፣ በስፖርት የማይታየው፣ የማይሰማው፣ የማያገናኘው ክስተት ስለሌለ ለአንድ ሀገር ኃይል ነው። ከዚህ በመነሳትም ስፖርት ሀገራዊ የልማት ማስፈፀሚያ መሣሪያ ስለመሆኑም ይነገራል። ይሄን ከሚያስብሉ ጉዳዮች መካከልም፣ ታላላቅ የሀገር መሪዎችን በአንድ የስፖርት መድረክ በማገናኘት ስለ ሀገራቸው የስፖርት ልማት ብሎም ሀገራዊ ብልፅግና የሚመክሩበት እንዲሁም ውሳኔ የሚያሳልፉበት በመሆኑ ነው።

ለዚህም ነው ዛሬ ላይ ሀገራት ስፖርትን በመጠቀም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ገፅታቸውን ለመገንባት ሲሠሩ የሚታየው። በዚህም በርካቶች ስፖርትን በመጠቀም ገጽታቸውን ገንብተዋል፤ ኢኮኖሚያዊ እድገታቸውንም አሳይተውበታል። ማህበራዊ ሁነትና እሴቶቻቸውንም ከፍ አድርገው ገልጠውበታል። ለዚህ ደግሞ የኦሎምፒክ ውድድሮች፣ የዓለም ዋንጫ እና የአህጉራት ስፖርታዊ ውድድሮች ከፍ ያለ ቦታ አላቸው፡፡

በአፍሪካ ደረጃም ስናይ፣ የአፍሪካ ዋንጫንና ሌሎች መሰል አህጉራዊም ሆነ ዓለምአቀፋዊ ውድድሮችን ለማስተናገድ ያለው ፍላጎት ከፍ ያለ ነው። ብዙ የአፍሪካ ሀገራትና ከተሞቻቸው እነዚህን ሁነቶች ለማስተናገድ ጥያቄን ከማቅረብ ጀምሮ የቻሉትን ሁሉ ሲጥሩ የሚታየውም ውድድሮቹ የሚያስገኙትን ከፍ ያለ ፋይዳ በመገንዘብ፤ እነዚህ ትልልቅ የስፖርት ሁነቶችም ለአጭር ጊዜም ይሁን ለረጅም ጊዜ ለማህበራዊ እና ለኢኮኖሚያዊ እድገት ጥቅም ስለሚያስገኙ፤ እንዲሁም የገፅታ ግንባታ ላይ ጉልህ ሚናን ስለሚጫወቱ ነው።

ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉ ትላልቅ የስፖርት ሁነቶችን ማዘጋጀት እጅግ በጣም ፈታኝ ነው። ምክንያቱም ለሁለቱ የሚውሉ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎችም ሆኑ ለደህንነት ሥራዎች ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃሉ። ይሄን ከፍ ያለ የወጪ ጫና ተቋቁሞና ከሁነቱ የሚገኘውን ሁሉን አቀፍ ፋይዳ ተገንዝቦ ሁነቶች ለማዘጋጀት መወሰንና ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት ደግሞ ከፍ ያለ ኃላፊነትን የመወጣት ውሳኔን ይጠይቃል፡፡

ምክንያቱም፣ እነዚህ ሁነቶች ከፍ ካለው ወጪያቸው ባሻገር ለአዘጋጁ ሀገርና ከተማ ትልቅ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ ልማት አወንታዊ ተፅእኖ አላቸው። በተለይም የምጣኔ ሀብት እድገትን፣ የመሠረተ ልማት ግንባታን፣ ጤናማና ታታሪ ትውልድን የማፍራትን፣ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት መጨመርን፣ የሥራ እድልን መፍጠርን እና የከተሞች መስፋፋትን እድል ይዘው የሚቀርቡ ናቸው፡፡

በዚህ ረገድ የስፖርት ቱሪዝምን ማነቃቃት፣ የስፖርት ኢንቨስትመንትን ማሳደግ፣ የስፖርት ቤተሰቡን ማቀራረብ፣ የስፖርት ዲፕሎማሲን ማሳደግ እንዲሁ በሀገራዊ ገፅታ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት የኢትዮጵያን ስፖርት በበላይነት ከሚመራው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በኃላፊነት ሊያከውናቸው ከሚገቡ ተግባራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

በዚህ ረገድ ከ46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን ሰሞኑን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪ ሞትሴፔን የተሳተፉበት፤ እንዲሁም የቀድሞው የካሜሮን ኮኮብ ተጫዋች ሳሙኤል ኢቶና ሌሎችም እንዲሁም አንጋፋ የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ያካተተ የወዳጅነት ጨዋታ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

የዘንድሮው ኢትዮጵያ እያስተናገደች የሚገኘው የካፍ ጠቅላላ ጉባዔም በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የስፖርት እንቅስቃሴን ገፅታ ከመገንባት አንጻር የተለየ ምዕራፍ ከፍቷል። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ ከ53 ዓመት በኋላ ለአራተኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን በ2029 ለማዘጋጀት ለካፍ በይፋ ጥያቄ ያቀረበችበትም ነው።

ለዚህም መንግሥት ከፍተኛ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን አቅሙና ቁርጠኝነቱ እንዳለው ማሳየቱ በተለይም ቁልቁለት ጉዞ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ለማነቃቃት ትልቅ ርምጃ ነው። የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት የታየው ቁርጠኝነት ውድድሩን ከማሰናዳት የዘለለ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ግልፅ ነው።

ለምሳሌ፣ ውሳኔው ለዓመታት ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ ዛሬም ድረስ በተለያዩ ከተሞች ቆመው የሚገኙ ስቴድየሞችን ለማጠናቀቅ ትልቅ እድል ነው። ይህም የካፍን መስፈርት የሚያሟላ አንድ ስቴድየም አጥቶ ባለፉት አራት ዓመታት ገደማ ጨዋታዎቹን በሌሎች ሀገራት ለማድረግ ለተገደደው ብሔራዊ ቡድን ጥያቄም ዘላቂ መልስ የሚሰጥ ይሆናል።

ከዚህ ባሻገር፣ መንግሥትም የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ሲያስብ ከስቴዲየሞቹ ባሻገርም ተተኪ ስፖርተኞች የሚወጡባቸው ትንንሽ ሜዳዎች (Mini stadium) ታሳቢ እንደሚደረጉ እና ውድድርን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ተጨማሪ የመሠረተ ልማቶች ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አረጋግጧል። ይህም የበርካታ ዓመታት ጥያቄ የሆነውን የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ጥያቄ በመቅረፍ ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። በየአካባቢው ታዳጊዎችን በብዛት ከማፍራት አኳያም ፋይዳው የጎላ ነው።

እነዚህ እና ሌሎችም ከፍ ያሉ የዝግጅቱን ፋይዳዎች ለተገነዘበ ደግሞ፣ ኢትዮጵያ ከግማሽ ክፍለዘመን በኋላ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ቆርጣ መነሳቷ ቅንጦት አይደለም። ምክንያቱም ውድድሩን ማዘጋጀት በራሱ ካለው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ባሻገር የ‹‹ይቻላል›› አስተሳሰብን ለመፍጠር ፋይዳው ቀላል አይደለም። ትውልዱም የአህጉሪቱን ታላቅ ውድድር በሀገሩ የመመልከት እድል ይሰጠዋል።

መንግሥት ውድድሩን ለማስተናገድ ጥያቄ ከማቅረብና ፍላጎቱን ከመግለፅ ባሻገር፣ ይህ ውጥን የተሳካ እንዲሆን በሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ ያሳየውን ፈጣን የአፈፃፀምና ቁርጠኝነት ለዚህ ሁነት በሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች ላይ በመድገምም የመፈጸም አቅም ክህሎቱን ከሀገር አልፎ ለዓለም ለመግለጥ እድል ይሰጠዋል፡፡

ስቴድየሞችን በሚፈለገው ጥራትና ደረጃ እንዲጠናቀቁና እንከን እንዳይኖርባቸው ከማድረግ አኳያም በዘርፉ እውቀትና ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር በመስራትም ለሌሎች መሰል ሥራዎች የልምድ፣ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠርም ያስችላል። በጥቅሉም ርምጃው እንደ ሀገር ከፍ ያለ ገጽታን የመገንቢያ፣ ዘርፉንም የማነቃቂያ አቅም የሚፈጥር እንደመሆኑ ለስኬታምነትና ውጤታማነቱ ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You