የአፍሪካ የደህንነት ስጋቶችን በጠንካራ ህብረት

የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥተና ሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ በቅርቡ በአዲስ አበባ ባካሄዱት ጉባዔ ትብብርን ማጠናከር የሚለው አጀንዳ ጎልቶ ወጥቷል፡፡ በወቅቱ፤ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በአፍሪካ ጸጥታን ጨምሮ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ሌሎችን መመልከት ሳይሆን በአንድነት መቆም ይገባል ማለታቸውም አይዘነጋም። ለመሆኑ በአፍሪካ የተረጋጋ የጂኦ ፖለቲካ ሁኔታ እንዲኖር ምን መደረግ አለበት?

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ፤ የአፍሪካ የፀጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውስብስብ እየሆነ መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡ የጸጥታ ችግሮቹ ሽብርተኝነትን፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትን እና የሳይበር ስጋቶችን ጨምሮ በበርካታ የተጠላለፉ ተግዳሮቶች የተሞሉ ናቸው ይላሉ። በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔና ሌሎች አፍሪካዊ አጀንዳ ያላቸው ሁነቶች እነዚህን ተግዳሮቶች በጋራ ለመፍታት አስፈላጊ መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ። “አንድ ሀገር ብቻውን እነዚህን ተግዳሮቶች ሊጋፈጥ አይችልም” በማለት፤ በአፍሪካ ሀገሮች መካከል የተቀናጀ አካሄድ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ቀጣናዊ ትብብርን በማጎልበት ረገድ በተለይም የአፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ለመመሥረት እና ሌሎች ውጥኖችን ለማሳካት የህብረቱ አባል ሀገራት ጠንካራ አንድነት መፍጠር እንዳለባቸውም ነው የሚመክሩት፡፡ እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ እነዚህ ጥረቶች በቂ የገንዘብ ድጋፍ ባለመኖሩ እና በአባል ሀገራቱ መካከል የፖለቲካ ፍላጎት ባለመኖሩ ብዙ ጊዜ አፍሪካ የሚጠበቅባትን ያህል ተጉዛለች ማለት እንደማይቻል ሌሎች ያነሳሉ፡፡

በአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮችና የፀረ ሽብር ማዕከል ኃላፊ ባባቱንዴ አባዮሚ እንደሚሉት፤ በትብብሩ ምንም እንኳን መሻሻል ቢኖርም፤ በፖለቲካዊ ፍላጎት እና ፋይናንስ እጥረት ምክንያት አሁንም በጋራ ጉዳዮች ላይ መላላቶች ይስተዋላሉ፡፡ ይህ መቀዛቀዝ የአፍሪካ ለችግሮች ውጤታማ ምላሽ የመስጠት አቅምን በእጅጉ ይጎዳል።

ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የጸጥታ ችግሮች፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የጂኦ ፖለቲካ ፉክክርና ሌሎች ከጸጥታ ጋር የተገናኙ ችግሮች አህጉሪቱን እየፈተኑ ይገኛሉ በማለት፤ ለአፍሪካ የጸጥታ ችግሮች የአፍሪካ አባል ሀገራት በተጠናከረ የጋራ ትብብር ሊሠሩ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ የአፍሪካ ህብረትም ለመሰል የትብብር ሥራዎች ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

የውጭ ኃይሎች በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር መሞከር አንዱ ተግዳሮት መሆኑን በማንሳት፤ በአፍሪካ ጉዳይ የኃያላን ሀገራት ፍላጎቶች መጨመር ወደ ሀብት ፉክክር እየገባ እንዳለ፤ ይህም ብዙውን ጊዜ የአፍሪካን አንድነት ሊያቀዘቅዝ እንደሚችል ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ ውድድር በአህጉሪቱ የገጠማትን የጸጥታ ችግር የበለጠ ያባብሰዋልም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

የጂኦፖለቲካል ፉክክር እና የኃያላን ሀገራት ፉክክር እየጨመረ በመምጣቱ የአፍሪካን የጋራ ጥረት እያናጋ፣ የድንበር ግጭት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ብሎም የአፍሪካ ህብረት 2063 አጀንዳን ስኬታማነት ላይ መሰናክል እየሆነ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

ይህ ሃሳባቸው አፍሪካ የብዙ ግጭቶች መነሻ ከቅኝ ግዛት ይዞቸው ከመጣው ጦሶች ጋር የተቆራኘ ነው የሚሉትን የባለሙያዎችን ሃሳቦች የሚደግፍ ነው፡፡

አዲባጆ እና ራሺድ የተባሉ አጥኚዎች እኤአ በ2019 በጸጥታ ዙሪያ ባደሩገት ጥናት መሠረት እነዚህ የቅኝ ግዛት ድንበሮች አለመግባባቶችን ዘርተዋል፤ ይህም አሁን ያለውን የጥታ ሁኔታ አወሳስቦታል ይላሉ፡፡

አሁን ላይ የሚታዩት ፉክክሮች ኢኮኖሚያዊ ውጤቶችም ከፍተኛ መሆናቸውን ያመላከቱት አጥኚዎቹ፤ የውጭ ኃይሎች ከአፍሪካ ፍላጎቶች ይልቅ ስልታዊ ጥቅሞቻቸውን ሊያስቀድሙ ስለሚችሉ የጂኦፖለቲካ ውድድር ብዙውን ጊዜ አስፈላጊ ከሆኑ የልማት አጀንዳዎች ትኩረትን ይሰርዛል ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

እንደ ቦኮ ሃራም እና አልሸባብ ባሉ ቡድኖች ከሽብርተኝነት እስከ የሳይበር ዛቻዎች ድረስ ያለው የደህንነት ስጋቶች ጠንካራ እና የተቀናጀ ምላሽ ያስፈልገዋል ያሉት ባባቱንዴ፤ ለዚህ ደግሞ የተሻለ የፖለቲካ ቁርጠኝነት አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት መስጠት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡ በአዲስ አበባ የተካሄደው ጉባዔ የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ስልታቸውን እና የትብብር ማዕቀፎቻቸውን እንደገና እንዲገመግሙበት ወሳኝ ጊዜ ሆኖ እንደሚያገልግል የባባቱንዴ አባዮሚ ጠቅሰዋል፡፡

የግሎባል ሽብርተኝነት ኢንዴክስ እኤአ በ2022 “አፍሪካ የዓለማችን ገዳይ አሸባሪ ድርጅቶች መገኛ ናት” በማለት፤ አስቸኳይ የአንድነት ግንባር እንደሚያስፈልግ አመልክቷል፡፡

የጎሳ ግጭቶችን ጨምሮ ከመፈንቅለ መንግሥት የሚመነጩ አካሄዶችና የፖለቲካ አለመረጋጋት በሚያስደነግጥ ሁኔታ ተደጋጋሚ በሆነ መልኩ የጸጥታ ምህዳሩን እያወሳሰቡ መሆናቸውን አትቷል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን “በአፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች መካከል ያለውን ትብብር” በተመለከተው ጽሑፋቸው፤ አሸባሪዎች፣ ጽንፈኛ ቡድኖች፣ የባህር ላይ ወንበዴዎችና የድንበር ግጭቶች አፍሪካን እያመሷት መሆኑን ገልፀዋል። በዚህም አህጉሪቱ በአሁኑ ወቅት በርካታ ማኅበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እየተጋፈጠች መሆኗን አመላክተዋል፡፡

የውጭ ኃይሎችም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አህጉራዊ የደህንነት ስጋት መፍጠራቸውን ያነሱት አምባሳደር ሬድዋን፤ አፍሪካ እያጋጠሟት ያሉትን ችግሮች የውጭ ኃይሎች እንዲፈቱልን ማማተር አይገባም በማለት፤ “ከውጭ የሚመጣ መፍትሔ ቢኖር እርስ በርስ እየተጋጨን ልዩነቶቻችንን አስፍተን በችግር እንድንማቅቅ የሚያደርግ ነው” ይላሉ፡፡

ለዚህ ደግሞ መተማመን ላይ የተመሠረተ የሀገራት ግንኙነት፣ ችግሮችን በሰላማዊ ድርድር የመፍታት ባህል፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን በፍትሃዊነት መጠቀም ግጭቶችን አስወግዶ አፍሪካዊ የጋራ የብልፅግና እና የሰላም ራዕይን ማሳካት እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ ይህ የአምባሳደር ሬድዋን ምልከታም ከተመራማሪዎቹ አዲባጆና ረሺድ ምልከታ ጋር የሚዛመድ ብሎም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ አስፈላጊነትንም የሚጠቁም ነው፡፡

አፍሪካ በተባበረ ክንድ ሰላሟን እንድታስጠብቅ የአፍሪካ አንድነት ታሪካዊ ሁኔታም ጉልህ ሚና ይጫወታል የሚሉት ባባቱንዴ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 የበለፀገች፣ የተዋሃደች አፍሪካን የመገንባት ራዕይ ሊሳካ የሚችለው በአባል ሀገራት መካከል አንድነት ሲኖር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ የተለያዩ ቀጣናዊ ግጭቶች፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትን ለመፍታት ብቃቱ ከፍ ያለ ጠንካራ ህብረት እንደሚያስፈልግ ያብራራሉ፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች እንደሚገልጹት፤ በአፍሪካ ውስጥ ጠንካራና የተዋሃደ የመከላከያ ማዕቀፍ መመሥረት የአህጉሪቱን የፀጥታ ሁኔታ በእጅጉ ሊለውጠው ይችላል። የአፍሪካ ሀገራት የፖለቲካ ፍላጎትን እና ትብብርን ማጎልበት ከቻሉ ያሉትን ስጋቶች ማቃለል ብቻ ሳይሆን በጋራ የሚያድጉበት ሁኔታም ይፈጠራል፡፡ ለዚህ ደግሞ አህጉራዊ ስትራቴጂዎችን በተሳካ ሁኔታ መተግበሩ ለተረጋጋ እና አስተማማኝ አፍሪካ መንገድ ሊከፍት ይችላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በውጭ ኃይሎች ርዳታ ላይ ያለውን ጥገኝነት ተባብሶ የአህጉሪቱ ደህንነት ስጋት እየሆነ ይቀጥላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You