ለሰላም ጊዜው አልረፈደም

የሰላምን ዋጋ በተጨባጭ የሚያውቅ ግለሰብ ሆነ ማህበረሰብ በሰላም እጦት ውስጥ ያለ ወይም በታሪክ አጋጣሚ ስለ ሰላም ብዙ ዋጋ ለመክፈል የተገደደ ነው ። ከዚህ ውጪ ስለ ሰላም በመዘመር ሆነ ብዙ በማውራት ዋጋውን ማወቅ አይቻልም ። በዚህ መልኩ የሰላምን ዋጋ ለመገመት የሚደረግ የትኛውም አይነት ጥረት የተሟላ ሊሆን አይችልም ።

እኛ ኢትዮጵያውያን ካሳለፍናቸው የሰላም እጦት ዘመናት እና ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ በየዘመኑ ለመክፈል ከተገደድነው ያልተገባ ዋጋ አንጻር ፤ የሰላም ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ አውቆ እና ተረድቶ ለመገመት ሆነ በተጨባጭ ለመናገር የሚከብደን አይደለም ። የሄደውም ፣ ያለው ሆነ የሚመጣውም ትውልድ ስለሰላም ዋጋ ከማንም በላይ መናገር ይችላል።

በአንድ በኩል የሰላምን ሁለንተናዊ ዋጋ ከፍ አድርገው በሚያስተምሩ መንፈሳዊ ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች ውስጥ ማለፋችን ፤ ከዛም ባለፈ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ሕልሞቻቸውን ኖረው ማለፍ አቅቷቸው ፤ ህልሞቻቸውን ከሩቅ ተሳልመው የማለፋቸው እውነታ የሰላም ዋጋ የቱን ያህል እንደሆነ ለመገመት ፈተና አይሆንብንም ።

በርግጥ እያንዳንዱ ትውልድ ዘመኑን የሚመጥን የመለወጥ /የለውጥ አስተሳሰብ ባለቤት ነው። ይህን የለውጥ አስተሳሰብ ስጋና ደም አላብሶ ሕይወት እንዲዘራ ለማድረግ ከሁሉም በላይ ሰላም ያስፈልጋል። ያለ ሰላም እንኳን ነገን ፣ ዛሬን ፤ የሚቀጥሉትን ደቂቃዎች በእርግጠኝነት ማሰብ አይቻልም።

ስለሚቀጥሉት ደቂቃዎች በእርግጠኝነት ማሰብ የማይችል ትውልድ ደግሞ በየትኛውም መንገድ ስለ ሀገሩ /ማህበረሰቡ ማሰብ የሚያስችለውን አቅም ሊፈጥር አይችልም ፤ ይህ ደግሞ የትውልዶችን ወጥቶ መሄድ ትርጉም አልባ ከማድረግ ባለፈ፤ በትውልዶች መተካካት ውስጥ ሊኖር የሚገባውን የመለወጥ መነቃቃት ይገድለዋል ።

የለውጥ መነቃቃት የሌለው ትውልድ ትናንት ውስጥ እንዲኖር የሚገደድ ነው ፤ የትናንቶች አድናቂ እና አፍቃሪ በመሆን የራሱን ዛሬዎች የሚያባክን ነው ፤ የትናንት ታሪክ ተራኪ እንጂ የራሱን ታሪክ የማይሠራ ፤ ራስ ወዳድ እና ጠባቂ ትውልድ መሆኑ የማይቀር ነው ።

በትውልዶች መካከል የሚኖር የሰላም እጦት በቀጥታ ሀገር እና ሕዝብን ከሚያስከፍለው ሞት ፣ ስደት ፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት በተጨማሪ በትውልዶች መካከል ሊኖር የሚገባውን ቅብብሎሽ በመፈታተን ፤ ማህበረሰባዊ የአስተሳሰብ ልቀትን ፤ ከዚህ የሚመነጭ የለውጥ መሻትን ያደበዝዛል ።

ከዚህም ባለፈ ፤ ለድህነት እና ኋላቀርነት የሚዳርግ ፤ ሀገር እንደሀገር በዘመናት ያካበተችውን ሞገስ በማደብዘዝ ፤ ብሄራዊ ክብርን በማጉደፍ አንገት የሚያስደፋ ነው። በዚህም ማንነትን እስከመጥላት ለሚያደርስ የሥነልቦና ቀውስ የሚዳርግ ጭምር ነው።

ይህ እውነታ በየዘመኑ እንደሀገር አደባባዮቻችንን የሞሉ የለውጥ ፍላጎቶች ፤ በፍላጎቶቹ ውስጥ ዘር የነበሩ የነገ ብሩህ ተስፋዎች እንዲመክኑ አድርጓል ። ከእያንዳንዱ የታሪክ ምእራፍ ትውልዶች ተገቢውን ትምህርት መውሰድ አቅቷቸው በተመሳሳይ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ዋጋ ለመክፈል ተገድደዋል።

እንደ ሀገር ስለሰላም በየዘመኑ ብዙ ያልተገባ ዋጋ እየከፈልን ፤ ከምንከፍለው ዋጋ መማር አለመቻላችን የታሪካችን ሆነ የማህበረሳባዊ ማንነታችን ተጠየቅ ሆኗል ። ስለ ሰላም አብዝተን እየዘመርን ፤ ስለሰላም በብዙ አስተምሮ ውስጥ እያለፍን የሰላም ዋጋ ተረድተን በተጨባጭ ለሰላማችን ዘብ መቆም አለመቻላችን የዘመናት እንቆቅልሻችን አካል ነው ።

ዛሬም ላይም ቢሆን እየሆነ ያለው ከትናንቶች የተለየ አይደለም ። እንደ ማህበረሰብ በትልቅ የለውጥ መነቃቃት ውስጥ ነበርን ፤ መነቃቃታችን እንደቀደሙት የለውጥ ዘመናት በሰላም እጦት ምክንያት እለት እለት እየተፈተነ እንደ ትውልድ ተስፋ ያደረግናቸውን ብሩህ ነገዎች እያደበዘዘ ነው።

በብዙ ሀገራዊ መነቃቃት አደባባይ ሞልቶ የነበረው የትውልዱ የለውጥ መሻት፤ ትውልዱ ሰላሙን አስጠብቆ ማስቀጠል ባለመቻሉ እንደቀደሙት ትውልዶች የለውጥ መሻቱ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እየተንገጫገጨ ነው ። ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍልም እያስገደደው ነው ።

በተለይም ተፈጥሯዊ የለውጥ መነቃቃቱን ጠልፈው ለግል እና ለቡድን የፖለቲካ ህልማቸው ግብአት ለማድረግ ያደቡ ሃይሎች ፤ ቋንቋውን እየተናገሩ ፤በስሙ እየማሉ እየተገዘቱ ፤ በማንነቱ እየፎከሩ ፤ ከማህበረሰባዊ ማንነቱ አጣልተው ለገዛ ሰላሙ ጠላት ሆኖ ዋጋ እንዲከፍል እያደረጉት ነው።

በየለውጥ የታሪክ ምእራፋችን የሚያጋጥመንን ይህንን ሀገራዊ ፈተና ለመሻገር ፤ ሰለማችንን ጠብቀን ለማስቀጠል ፤ በመዘናጋታችን ከከፈልነው ያልተገባ ዋጋ ብዙ ተምረን ፤ በሰላማችን ላይ ያነሳነውን ጠበንጃ አውርደን ተስፋችንን ተጨባጭ ለማድረግ ከቀደመው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ከራሳችን የትናንት ታሪክ ተምረን ልንመለስ ይገባል ። ለዚህ ደግሞ ጊዜው አልረፈደም !

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም

Recommended For You