ድሬዳዋ ከተማ በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የምትገኝ ከተማ ናት። ከተማዋ የኦሮሚያን ክልል እና የሶማሌን ክልል የምታዋሰን ሲሆን፤ በሀገሪቱ ካሉት ሁለት የከተማ አስተዳደሮች አንዷ ናት። ድሬዳዋ ከተማ በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞች አራተኛዋ ዝነኛ ከተማ ናት።
ከተማዋ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ ያለባት እና የተለያየ የአኗኗር ባሕል ያለባት ከተማ ናት። የፍቅር ከተማ፣ የበረሀዋ ገነት የሚባሉ ቅጽል መጠሪም አላት። ድሬዳዋ በምሥራቁ አቅጣጫ ለኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ያለች እንደመሆኗ እና በመተማ በኩል ያለው መንገድ በመዘጋቱ ሥራ ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚሻገሩ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚመጡ ሕገ ወጥ ፍልሰተኞች አሁን ላይ ወደ ከተማዋ ፍልሰታቸው እየጨመረ መጥቷል።
ፍልሰተኞቹ ድንበር ለመሻገርም ሆነ ተመልሰው ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ፤ ባጋጣሚ ያሰቡት ሳይሳካላቸው ሲቀር እዛው ከተማው ላይ የሚቀሩበት ሁኔታ አለ።
በሌላ በኩል እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ዓለም አቀፍ ስለ ሕገ ወጥ ስደት አስከፊነት በርካታ ነገር ተብሏል። ለስደት የወጡ ዜጎች የሚያጋጥማቸው አደጋ በተለያዩ ዘጋቢ ፊልሞች፣ ዜናዎች እና ሌሎች የጥበብ መንገዶች ሲነገር ቆይቷል፤ አሁንም እየተነገረ ነው።
ዜጎችን ለሕገ ወጥ ስደት በሚዳርጉ ደላሎች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ርምጃ መወሰዱም ይነገራል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን እነዚህ ሕገ ወጥ ደላሎች አሰራራቸውን በመቀየር ሥራቸውን ማስኬዳቸው አልቀረም።
ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዱረህማን ሙሳ አደን ጋር፤ በከተማው እየጨመረ የመጣውን የሕገ ወጥ ፍልሰተኞች ቁጥር፣ ለመፍለሳቸው መንስኤ፣ ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ ስላለው ጉዳይ እና መሰል የሆኑ ጥያቄዎችን አንስተናል። በከተማ አስተዳደሩ የሴቶች ጥቃት ለመከላከል ምን ተሰራ? ምን ውጤት ተገኘ? የሚሉትን ጥያቄዎች አካትተን ከኃላፊው ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን፡- የድሬዳዋ ከተማ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊነቶች ምንድን ናቸው?
አቶ አብዱረህማን፡- አጠቃላይ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ሕፃናት እና ማህበራዊ ዘርፍ የሚሰራው ትላልቅ ሥራዎችን ነው። በስፋት የሚሰሩ ሥራዎች ሰው ተኮር ሥራዎች ናቸው።
ሴቶች ላይ፣ አካል ጉዳተኝነት ላይ፣ ድህነት ቅነሳ ላይ፣ አረጋውያን ላይ፣ ሕገ ወጥ ስደትን መከላከል ላይ ያተኮሩ ሥራዎች ይሰራሉ። በሂደት ትውልድን የማነጽ ሥራ ስለሆነ በዘርፉ የሚሰሩት በርካታ ተግባራት ናቸው።
እውቀት እና አቅም ያላቸው አረጋውያንም እውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያካፍሉ እየተደረገ ነው። በኢኮኖሚው ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ እየተመቻቸ ነው። እንደ ሀገር ካለው የሕዝብ ቁጥር 20 በመቶ የሚሆኑት አካል ጉዳተኞች መሆናቸው ይነሳል፤ እንደ ድሬዳዋ ከተማም አካል ጉዳተኞችን በአካቶ ትግበራ ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተሰራ ነው።አዲስ ዘመን፡- በከተማ አስተዳደሩ ከሴቶች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች ምንድን ናቸው? እንደ ቢሮ በሴቶች ረገድ ምን ዓይነት ሥራዎች እየተሰሩ ነው?
አቶ አብዱረህማን፡- ከለውጡ በፊት እና ከለውጡ በኋላ ባሉ ነገሮች በጣም ሰፊ ልዩነት ነው ያለው። አሁን ላይ ለሴቶች፣ ለሕፃናት፣ ለአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል እንደ ሀገርም እንደ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም እየተሰራ ነው።
እንደ አጠቃላይ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና የልማቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። በአሁኑ ወቅት ሴቶችን በኢኮኖሚ እና በአቅም የመደገፍ ሥራዎች ተጀምረዋል። በዚህም ሴቶችን የማደራጀት፣ ሴቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ እና አካቶ ትግበራ ላይ የሴቶች ተሳትፎ በጣም የመጨመር ሁኔታ አሳይቷል።
የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል ኢትዮጵያ ተቀናጅታ በሰራቻቸው ሥራ፤ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቷ ይታወሳል፤ ይህን ተከትሎ ክልሎች በሴት ልጅ ጥቃትን ለመከላከል በሰሩት ሥራ እውቅና ሲሰጣቸው፤ እውቅና ካገኙ ክልሎች አንዱ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሴቶች ጥቃት በድሬዳዋ አስተዳደር የቀነሰበት ሁኔታ አለ። የተሻለ አፈጻጸም ካላቸው ቢሮዎች አንዱ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሴቶች ጥቃትን ከመከላከል ረገድ ቢሮው እውቅና ማግኘቱን የገለጹበት ሁኔታ አለና፤ ከዚህ በፊት የጉዳዩ አስከፊነት ምን ያህል ነበር? የተሰሩ ሥራዎችና አሁን ያለው ሁኔታስ ምን ይመስላል?
አቶ አብዱረህማን፡- ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ከዚህ በፊት ለሴቶችና እንደ አጠቃላይ ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት በጣም ያነሰ ነበር፤ ሁለተኛው ነገር አሁን ላይ ለዘርፉ ትኩረት ለመስጠት በማሰብ፤ ያቀድነው እቅድ በጣም የተለጠጠ እቅድ ነው። ያቀድነውም 50 በመቶ እና ከዛ በላይ እናሳካለን ብለን ነው።
ሴቶች እንደመሆናቸው የኢኮኖሚ አቅማቸውን የማጠናከር ሥራ ተሰርቷል። በዛው ደረጃ የሴቶችን መብት በማረጋገጥ ደረጃ ከፍትህ አካላት ጋራ እየተሰራ ነው። ለዚህም ሴቶች ጥቃት ካጋጠማቸው ደውለው እንዲያሳውቁ ነፃ የስልክ መስመር ተዘጋጅቷል። የስልክ መስመሩ ያለው በድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን ነው። ችግር ሲያጋጥም ማንኛውም ሰው በዛ እንዲደውሉ የተመቻቸ ነው። በዚህም ጥቆማዎች ሲደርሱ ወዲያውኑ ምላሽ የመስጠት ነገር አለ።
ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን እንደ ሀገር አቀፍ አንድ ለየት የሚያደርገው፤ የጥቃት ማገገሚያ ማዕከል የሚል ትልቅ ህንጻ ተገንብቷል። ይህም ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች የሚያገግሙበት ማዕከል ነው። ከጤና ቢሮ ጋር በመነጋገር አንድ ሆስፒታል ላይም የጥቃት ማዕከል ተገንብቶ ከጥቃት የማገገሚያ እና የኢኮኖሚ ማጠናከሪያ ሥራ እየሰራ ነው የሚገኘው።
ጥቃትን ከመከላከል ረገድ በሚዲያዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች በስፋት ተሰርቷል። ሌላው ነገር እንደሚታወቀው ድሬዳዋ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ ቅን ነው። ስለዚህ ሴቶችን ከማህበረሰብ ለይቶ የማግለል ነገር የለም። ከመጀመሪያውም እንደ ባሕሉ ለሴቶች በጣም ትኩረት ይሰጣል።
ከተማውም ሰላማዊና ሰው ተዋዶ የሚኖርበት እንደመሆኑ ብዙም በሴቶች ላይ የሚደርስ ማህበራዊ ተጽዕኖ የለም። በተጨማሪም ስልጡን ሕዝብ በመሆኑ ከዚህ በፊትም ቢሆን ሴቶች ላይ የሚደርሰው ተጽዕኖ ብዙም አልነበረም። ነገር ግን ባለፉት አምስት ዓመታት ከሴቶች ጋር ተያይዞ ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል።
አዲስ ዘመን፡- ሴቶች ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ጥቃቶች አሉ፤ ችግሩን ለመቅረፍ ባለፉት አምስት ዓመታት የትኞቹ ላይ ነው ትኩረት ተደርጎ የተሰራው?
አቶ አብዱረህማን፡- ባለፉት አምስት ዓመታት ትኩረት ተሰጥቶ የተሰራው ቤተሰብ ማጠናከር ላይ ነው። ሌላው ደግሞ በሁለት አካላት በፍትህ እና በሚዲያ አካላት ላይ የተሰራ ሥራ ነው።
ቤተሰብን ማጠናከር ሲባል አባት ሊሆን ይችላል፤ ወንድም ሊሆን ይችላል፤ እናት ልትሆን ትችላለች ችግር በሚፈጠርበት ወቅት ቶሎ ብለው ወደ ሕግ አካላት ከመሄድ ይልቅ፤ እያንዳንዱ የራሱን ኃላፊነት በመውሰድ ችግሩን እዛው ተነጋግሮ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የማድረግ ሥራ ነው።
ምክንያቱም እያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ ነው ሴቷ የምትጠቃለለው፤ ቤተሰብን የማጠናከር ሥራ በዋነኝነት የተያዘው ለዛ ነው። እንደ ሀገር ደረጃም የተያዘው የቤተሰብ ጉዳይ ነው። ስለዚህ እንደ ከተማ አስተዳደር ቤተሰብ ላይ ሰፋፊ ሥራ በመሰራቱ ጥቃቱ ሊቀንስ ችሏል። ቤተሰብ ማለት ሀገር ነው፤ ስለዚህ ሁሉም አካባቢዎች በዚህ ላይ ቢሰሩ መልካም ነው የሚል እምነት አለኝ።
ሌላኛው ነገር የሴቶችን ጥቃት ከመቀነስ ረገድ ከእኛ ጋር ትላልቅ ሥራዎችን ሲሰሩ የነበሩ እና ሊመሰገኑ የሚገባቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች አሉ። በእነሱ ርዳታም ጭምር ጥቃቶች ሊቀንሱ ችለዋል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሴቶች ጥቃት በምን ያህል መጠን መቀነስ እንደተቻለ በቁጥር ቢገልጹ?
አቶ አብዱረህማን፡- ከሴቶች ጥቃት ጋር ተያይዞ ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ በዚህም የጥቃት መጠኑ ከ60 እስከ 63 በመቶ ቀንሷል። ቅድም እንዳነሳሁት ድሬዳዋ ላይ የሴቶች ጥቃት ብዙም የተለመዱ አይደሉም። በአካባቢው እንደዚህ ዓይነት ሥነ ምግባርም የለም። እንደቢሮም የበለጠ በሴቶች ረገድ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የተሰራው ሥራ ሴቶችን በኢኮኖሚ የማጠናከር እና የግንዛቤ ሥራ ነው።
በዚህም ሴቶችን በአስተሳሰብ የማጠናከር ሥራ የተሰራ ነው እንጂ፤ የሴቶች ጥቃት ብዙም በዛ ደረጃ በተለየ ሁኔታ የከፋ አይደለም። ግን ባለን እቅድ አኳያ ተሻሽሎ ብዙ ሥራ ተሰርቷል የሚል አንድምታ ነው ያለን።
አዲስ ዘመን፡- ከሴት ልጅ ግርዛት ጋር ተያይዞ ያለው ነገር ምን ይመስላል?
አቶ አብዱረህማን፡– የሴት ግርዛት ከሃይማኖትም ጋር ተያይዞ የቆየ ባሕል ነው። ሰው ሃይማኖት የሚፈቅድ ይመስለዋል እንጂ አይደለም። በዚህ ረገድ ያደረግነው ነገር ከሁሉም አካላት ጋር ጥምረት መፍጠር ነው። ከሃይማኖት አባቶች፣ ከፍትህ አካላት እንዲሁም ከማህበረሰብ ውስጥ ተሰሚነት ካላቸው ሰዎች እና ግርዛት የሚያከናውኑ ሰዎችንም የጥምረቱ አካል በማድረግ በየትምህርት ቤቱ ባሉ ሚኒሚዲያዎች የግንዛቤ ሥራ ተሰርቷል። አሁን ላይ የሴት ልጅ ግርዛት በብዙ ቁጥር ቀንሷል። ምናልባት በቀጣይ ትውልድ ይህ ነገር ይኖራል የሚል ሃሳብ የለኝም። ምክንያቱም ቤተሰብ እንደ ጃንጥላ ነው። በዚህ መሰረት ቤተሰብን የማጠናከር እና ከሴት ልጅ ግርዛት ጋር ተያይዞ ግንዛቤ እየተሰራ ነው።
የሃይማኖት ተቋማትም በየመስጊዱ፣ በየቤተክር ስቲያኑ እና በየጸሎት ቤቱ የሴት ልጅ ግርዛት ያለውን ጉዳት እንዲረዱት የማስተማር እና ለተከታዮቻቸው ግንዛቤ እንዲሰጡ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ከግንዛቤ ሥራው ጎን ለጎን አንዳንዴ በድብቅ የሴት ልጅ ግርዛት የሚከናወንበት ሁኔታ አለ፤ በዚህ ረገድ የሕግ ቁጥጥሩ ምን ይመስላል?
አቶ አብዱረህማን፡- ከሴት ልጅ ግርዛት ጋር ተያይዞ ያለው አስከፊነት በቅድሚያ ግንዛቤ ለሴት ልጆች ይሰጣል። እንደዚህ ዓይነት ጥሰቶች በሚፈጠሩበት ወቅት ትምህርት ቤት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በነፃ የስልክ መስመር እንዲያሳውቁ ይደረጋል።
እንደዚህ ዓይነት ጥሰቶች ሲከሰቱ ከማህበረሰቡ ከተወጣጣው የጥምረት አካላት ጋር በመቀናጀት ይሰራል። በተጨማሪም ቢሮው ከፍትህ አካላት ጋርም ይሰራል እንደዚህ ዓይነት የሕግ ጥሰቶች ሲኖሩ፤ ወንጀለኞቹ ላይ ርምጃ ይወሰዳል።
ስለዚህ ይህን ጥቃት ለመከላከል ቀድሞ የሚሰጠው ግንዛቤ ነው። ነገር ግን በረጅም ጊዜያት እንደዚህ ዓይነት ተፈጥሮ ጥቆማ ሲደርስ ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- በከተማ አስተዳደሩ የሴቶች ጥቃት ዝቅተኛ እንደሆነ ገልጸው ነበረ፤ በዚህ ረገድ ለሌሎች ክልሎች እንደተሞክሮ ሊነሳ የሚችል ነገር ምንድን ነው?
አቶ አብዱረህማን፡– በአካባቢው ለሴት ልጅ ትልቅ ቦታ ከመስጠት ረገድ ያለው ሥነ ምግባር ትልቅ የሚባል ነው። ለዚህም ደግሞ አንዱ ምክንያት፤ ማህበረሰቡ የነቃና ስልጡን መሆኑ ነው። ይህን ስል ግን ሌላው የማህበረሰብ ክፍል ስልጡን አይደለም ማለቴ እንዳልሆን እንዲታሰብልኝ እፈልጋለሁ። ስለዚህ የሴት ልጆችን ጥቃት ለመከላክል ማህበረሰብን ማንቃት ያስፈልጋል እላለሁ።
በከተማ አስተዳደሩ እንደዚህ ዓይነት ሥነ ምግባር እንዲፈጠር ያደረገው ማህበረሰቡ አንዱ ከአንዱ ጋር ያለው ውህደት ነው። የአካባቢው ሕዝብ አንዱ ከአንዱ ጋር ያለው መተሳሰብ፤ አብሮ መብላት ብቻ ሳይሆን፤ በሃሳብ የመደጋገፍ ነገርም አለ። ስለዚህ ማህበረሰቡ ግላዊነት ሳይሆን፤ አብሮነትን የሚያንጸባርቅ ነው። ሌላው ማህበረሰብ ይህንን ልምድ ቢቀስም የሚል ሃሳብ አለኝ።
በሌላ በኩል ማንሳት የምፈልገው ነገር ከሕገ ወጥ ስደት ጋር ተያይዞ ያለውን ነገር ነው። ድሬዳዋ ለምሥራቁ የሀገራችን ክፍልና እና እንደ አጠቃላይ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ቦታ ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። ለወደብም በጣም ቅርብ ቦታ ላይ ናት። ከጁቡቲ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለች ናት።
ከተለያዩ ቦታዎች ከደቡብ፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ እና ከትግራይ ክልል ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሥራ ፍለጋ የሚመጡ ሰዎች ፍሰት አሁን ላይ በከተማዋ በጣም የጨመረበት ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል። በሕገ ወጥ መንገድ፣ በሕገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት መጥተው ሳይሳካለቸው ሲቀር በከተማው ለጎዳና ሕይወት ተጋልጠው የመቅረት ነገር በስፋት ይታያል።
በተለይ የሱዳን ጦርነት ተቀስቅሶ የመተማ መንገድ ከተዘጋ በኋላ፤ የሕገ ወጥ ስደተኞች ጫና በድሬዳዋ ከተማ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። ወደ ስደት ሲሄዱም ሆነ ሲመለሱ ሳይሳካላቸው ሲቀር ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ነው የሚቀሩት።
እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያዊ እንደመሆናቸው በተለያየ ጊዜ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ የሚደረግ ሥራ እንሰራለን፤ ነገር ግን ክልሎቹ በዚህ ዙሪያ በጣም ሰፊ ሥራ ሊሰሩ ይገባል። ሚዲያዎችም በግንዛቤ በኩል የራሳቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል።
በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር መሻገር በጣም አደጋ እንዳለው ሊያውቁት ይገባል። በተለይ በዚህ ጉዳይ ሴቶች በጣም ተጎጂዎች ናቸው፤ በተጨማሪም ወጣቶች እና ሕፃናትም እንደዚያ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ፍልሰተኞቹ ከአካባቢያቸውም የሚወጡበት ምክንያት ምንድነው? ከወጡ በኋላ በከተማው እንዲቀሩ የሚያደርጋቸው ምን ዓይነት ሁኔታ ነው? በጉዳዩ ዙሪያ የተሰራ ጥናት ይኖር ይሆን?
አቶ አብዱረህማን፡- ማግኘት ከቻልነው መረጃ አንጻር ፍልሰተኞቹ ከሚኖሩበት አካባቢ እንዲወጡ የሚያደርጋቸው ገፊ ምክንያቶች፤ ዋነኞቹ የእናትና አባት መለያየት፤ ከቤተሰብ ግጭት ጋር ተያይዞ እና ከኑሮ ሁኔታ አንጻር ነው። በዚህ ረገድ በአካባቢዎቹ ድህነት ቅነሳ ላይ መሥራት ያስፈልጋል።
ሌላው ክልሎቹ ሕገ ወጥ ፍልሰት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ፤ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሥራት ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ክልሎች የበለጠ መረጃ ለማግኘት እና ያለውን ችግር ለመቅረፍ ጥናት ቢያደርጉ እና ጉዳዩ ላይ ቢሰሩ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።
ድሬዳዋ ከተማ የሚቀሩበት ምክንያት ከቤታቸው ሲወጡ ይዘው የወጡትን ብር ሲጨርሱ እንዴት ባዶ እጅ ወደ ቤተሰብ እመለሳለሁ ብሎ የመፍራት ነገር በመፈጠሩ ነው። ይዘውት የመጡትን ብር ደላላው ይቀበልና የመሻገሩ ጉዳይ ሳይሳካ ሲቀር ወደ ጎዳና የሚወጡበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ሌላው ምክንያት የድሬዳዋ ማህበረሰብ እንግዳ ተቀባይነት እና አየሩም ምቹ ነው። አየሩ ስለማይከለክለው አንድ ሰው በረንዳ ላይ ሊተኛ ይችላል። ሰው የመረዳዳት ባሕሉ በጣም ከፍ ያለ ስለሆነ ሰው እዛ ከሄደ አይመለስም። ነገር ግን አሁን ላይ ከአቅም በላይ ሆኗል፤ ፍሰቱ የድሬዳዋ ሕዝብ ፍሰት አይደለም። ወደ ጁቡቲ ለመሻገር ከሌሎች ክልሎች የሚመጡ ሕዝቦች ፍሰት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ፍልሰተኞቹ በስፋት የሚመጡት ከየትኛው የሀገሪቱ አካባቢ ነው?
አቶ አብዱረህማን፡- ኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሀረርጌ እና ምዕራብ ሀረርጌ፤ ከአርሲ አካባቢ ነው። ሌላው ከደቡብ ክልልም ይመጣሉ። ከአማራ ክልል ደግሞ ከወሎ አካባቢ እንዲሁም ከትግራይ ክልል አካባቢም የሚመጡ አሉ።
ከዚህ በፊት ትግራይ ክልል እና አማራ ክልል ያሉ ሰዎች በመተማ በኩል ነበር የሚወጡት። አሁን ግን እዛ አካባቢ ችግር ስላለ፤ ለዛ ነው ጫናው የበረታው። ስለዚህ ክልሎች በቅንጅት ሰፋፊ ሥራ እንዲሰሩ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡- ከአካባቢው የሚወጡት በራሳቸው ተነሳሽነት ነው? ወይስ ግፊት የሚያሳደርባቸው አካል አለ?
አቶ አብዱረህማን፡- በብዛት ደላሎች ናቸው የሚያመጧቸው፤ እናሻግራችኋለን በሚል ብራቸውን ከተቀበሉ በኋላ የሚቀሩበት ሁኔታ ይፈጠራል። እነዚህን ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመረ ሥራ አለ። በዚህ ረገድ የተቋቋመ ኮሚቴ አለ በእነዚህ በኩል የቁጥጥር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል።
ሌላው ፍልሰተኞቹ ከቤታቸው የሚወጡት በአካባቢያቸው ያለ ሰው ውጭ ሀገር ሄዷል በሚል መረጃ ሳይኖራቸው የሚወጡበት ሁኔታ ነው። በስፋት ግን ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ናቸው እንዲወጡ የሚያደርጓቸው።
አዲስ ዘመን፡- ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ፍልሰተኞቹ በሚኖሩበት አካባቢ ያሉ ናቸው? ወይስ ፍልሰተኞቹ ድሬዳዋ በጥቆማ ነው የሚመጡ?
አቶ አብዱረህማን፡– ከመካከለኛው ምሥራቅ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ፤ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ የራሳቸው ሰንሰለት አላቸው። በሚዲያም እንደሚታየው መንግሥት በእነዚህ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ ርምጃ ወስዷል፤ ግን አሁንም ይቀራል።
አንዱ ሲቀጣ ሌላኞቹ በየጊዜው አሰራራቸውን እየቀየሩ ስለሚሰሩ ችግሩን ለማጥፋት አዳጋች ያደርጋል። ስለዚህ አሁንም በጥናት በመለየት ርምጃ የመውሰድ ሥራ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ድንበር ለመሻገር ወደ ከተማው መጥተው የሚቀሩትን ወደመጡበት አካባቢ የመመለስ ሁኔታው ምን ይመስላል?
አቶ አብዱረህማን፡- በየጊዜ ወደመጡበት አካባቢ እንመልሳለን፤ ነገር ግን የቅንጅት ሥራ ይፈልጋል። ጉዳዩን ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም አንስተናል። አሁን ላይ ትንሽ ክልሎች ካጋጠማቸው የጥሬ በጀት እጥረት ጋር እና ካሉበት ሁኔታ ጋር ተያይዞ ተግዳሮቶች አሉ። ነገር ግን ችግሩን ለመፍታት ሰፊ ሥራ ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡- በጉዳዩ ላይ እንደ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ አብዱረህማን፡- እኛ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ እንደ ከተማ አስተዳደር ሰፋፊ ሥራዎችን ጀምረናል። ስለዚህ በቀጣይ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በጥናት የተደገፈ ሥራ እንሰራለን የሚል ሃሳብ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በጉዳዩ ላይ ለክልሎቹ፣ ለፍልሰተኞች እና ሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት የሚያስተላልፉት መልዕክት ይኖርዎ ይሆን?
አቶ አብዱረህማን፡- እንደ ሀገር ጠንካራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሥራዎችን በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል። በግንዛቤው ረገድም ሀገር አቀፍ ሚዲያዎችን በመጠቀም መሥራት የግድ ይላል የሚል ሃሳብ አለኝ። በተጨማሪም በድሬዳዋ ከተማ የጨመረውን የሕገ ወጥ ፍልሰተኞች ቁጥር ለመቀነስ ክልሎች በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል የሚልም አስተያየት አለኝ።
አዲስ ዘመን- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ እናመሰግናለን።
አቶ አብዱረህማን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም