ያረጀ የቅኝግዛት እሳቤ ከመራመድ ወጥቶ ለማሕቀፉ ትግበራ ተባባሪ መሆን ብልህነት ነው!

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ለፍትህ እና ለፍትሐዊነት ካላቸው ዘመን ተሻጋሪ ማህበረሰባዊ እሴት አኳያ፤ በናይል ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ፍትሐዊነት እንዲሰፍን ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ለዚህ አስተሳሰብ ባእድ የሆኑ የቅኝ ግዛት ውሎች በብዙ መስዋእትነት ነጻነቱን የተቀዳጀውን የአሁኑን አፍሪካዊ ትውልድ እንደማይመጥኑ ድ ምጿን ከፍ አ ድርጋ አሰምታለች።

ፍትሐዊነት ዓለም አቀፍ መርህ ተደርጎ በሚወሰድበት አሁናዊው ዓለም፤ እንደሀገር ስለፍትሐዊነት ያሰማቻቸው ድምጾች በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ተገቢውን ጆሮ ሳያገኙ በመቅረታቸው፤ ሀገሪቱ በተለይም የዓባይ ወንዝን በፍትሐዊነት ለማልማት ያደረገችው ጥረት በብዙ ፈተናዎች የታጀበ እንዲሆን አድርጎታል።

የአንድ ሀገር ሆነ ሕዝብ የመልማት ጥያቄ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው በዓለም አቀፍ ህጎችም የተደገፈ ነው። በተለይም ባለንበት ዘመን የመልማት ጥያቄ የበለጸገች ዓለም ለመፍጠር ከሚደረገው ጥረት አኳያ በእጅጉ የሚበረታታ እና ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸረው ነው። ሰብአዊ መብትም ተደርጎ የሚወሰድም ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያም በተለያዩ ወቅቶች ያሏትን የተፈጥሮ ጸጋዎች በመጠቀም ከድህነት እና ከኋላቀርነት ለመውጣት የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች። በተለይም የውሃ ሀብቷን በሁለንተናዊ መልኩ በመጠቀም ሕዝቦቿን ተጠቃሚ ለማድረግ ያደረገቻቸው ጥረቶች ዛሬን በማይመጥኑ የቅኝ ግዛት ውሎች ሲፈተኑ ቆይተዋል።

እነዚህ በናይል ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ቅኝ ገዥዎች ያሠሩዋቸው ውሎች የየትኛውንም አፍሪካዊ ፍላጎት ያላካተቱ፣ከዛ ይልቅ የወቅቱ ቅኝ ገዥ ሀገራትን ጥቅሞች መሰረት ያደረጉ ፣ ከነጻነት በኋላም በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የነበረውን አፍሪካዊ ወንድማማችነትን በመቀጨጭ አለመተማመንን እየፈጠሩ የነበሩ ናቸው።

የተፋሰሱ ሀገራት በነጻነት ትግሉ ወቅት የተፈጠረውን የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ፣ እሳቤው የወለደውን ወንድማማችነት ፣ ከዚህ የሚመነጭ መደጋገፍ እና አብሮ የማደግ መነሳሳት ተጨባጭ እንዳይሆን ትልቅ ተግዳሮት፤ ከዛም አልፎ በተፋሰሱ ሀገራት የመልማት ፍላጎት ላይ ትልቅ ደንቃራ ሆነዋል ።

በተለይም በተለያዩ ወቅቶች ወደ ስልጣን የመጡ የግብጽ መንግሥታት የወንዙን ውሃ ሁሌም የሀገር ውስጥ ፖለቲካ አጀንዳ አድርገው በማቅረብ፤የወንዙን ውሃ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የግጭት እና የአለመተማመን ምንጭ እና የሀገር ውስጥ ፖለቲካ ጊዜ መግዣ ለማድረግ ሰፊ ጥረቶችን ሲያደርጉ፤ ባልተገባ መልኩ በተደጋጋሚ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ለማድረግም ሲሞክሩ ማየት የተለመደ ነው።

በፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር አብሮ ለጋራ ተጠቃሚነት ከመሥራት ይልቅ ፤ ጊዜ ያለፈባቸውን የቅኝ ግዛት ውሎች የሙጥኝ የማለቱ የግብጽ መሪዎች የቀደመ ሆነ አሁናዊ አካሄድ፤ በየትኛውም መንገድ የግብጽን ሕዝብ ከወንዙ ውሃ የተሻለና ዘላቂ ተጠቃሚ አያደርገውም።

መንግሥታቱ እስካሁን እየሄዱበት ያለው የሴራ መንገድም ቢሆን፤ዘመኑን የማይመጥን ፣ዓለም አቀፉን የዲፕሎማሲ መንገድ የተቃረነ ፣ቀናት እየተቆጠሩ ሲሄዱ በአደባባይ ድምጽን ከፍ አድርጎ ለመናገር የሞራል ድፍረት የሚያጎናጽፉ አይደሉም። የግብጽን ሕዝብ በዓለም አቀፍ መድረክ ከማሳነስ ያለፈ ፋይዳም አይኖራቸውም።

በተለይም አሁን ላይ አብዛኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የወንዙን ውሃ ለመጠቀም ፣ የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ህጋዊ ባደረጉበት ወቅት ስለ ቅኝ ግዛት ውሎች ሙግት ለመግጠም መሞከር ፤ የግብጽ መሪዎች ዛሬም ከቅኝ ግዛት አንጎበር እንዳልወጡ የሚያመላክት ነው ።

ዓለም በሁለንተናዊ መልኩ ወደ አንድ መንደርነት እየተጓዘች ባለችበት ፤ለዚህ የሚሆን ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር እየፈጠረች ባለችበት ፤አለመተማመንን እና ጠላትነትን በሚፈጥሩ ጊዜ ያለፈባቸው አስተሳሰቦች የተቃኙ የቅኝ ግዛት ውሎችን የሙጥኝ ማለት ዘመኑን የሚመጥን የፖለቲካ እሳቤ አይደለም።

የግብጽ ፖለቲከኞች ለሕዝባቸው ብሩህ ነገዎች ታማኝ ከሆኑ ፤ታማኝነታቸው ሊመነጭ የሚችለው ዛሬ ላይ ትርጉም አልባ የሆኑ ትርክቶችን ከመደጋገም ወጥተው ፤ከአፍሪካዊ ወንድሞቻቸው ጋር በሰላም እና በፍቅር፤ በመከባበር እና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ማህበራዊ ፣ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነትን ማስፈን ሲችሉ ብቻ ነው ።

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You