ሰሞኑን ወንዶች የሴቶችን በስልጣን ላይ መብዛት ተከትሎ ነገረ ትዝብታቸውን መደርደር ጀምረዋል፡፡ኧረ ወንድ ንቃ ከቤት መውጣት ፈራን ከሚሉ ጥቃቅን ፍራቻ አንስቶ፤ ማርች ስምንት የወንዶች ቀን ሆኖ ይታሰብ እስከሚሉ ትላልቅ መፈክሮች በማኅበራዊ ሚዲያዎች እየፎከሩ ይገኛሉ፡፡
ቅድሚያ ለወንድ በማለት የታክሲ ወረፋ የሚያስቀድሙ ሴቶችም እንዳሉ ከእለት ውሏቸው የሚያጫውቱኝ ወንዶችም አልጠፉም፡፡ የስ ውሃ ላይ የሴት ምስል ስላለ እንዳትገዙት የሚሉ ቅናት ያደረባቸው ወንዶችም እንዲሁ ብዙ ናቸው አሉ፡፡ አንዳንዶችማ በወንዶች ስም የሚጠሩትን ስያሜዎች ሳይቀር ወደ ሴቶች እንዲመጣ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው የሚለው ፌስ ቡክ ደግሞ ለአብነትም ‹‹ወንዶገነትን›› ወደ ‹‹ሴቶገነት›› ‹‹ወንዲራድ›› ትምህርት ቤትን ወደ ‹‹ሴቲራድ›› ‹‹ወንዲማክን›› ወደ ‹‹ሴቲማክ›› ለመቀየር የሚደረገው ሸፍጥ መበራከቱን በየቀኑ ከሚለጠፈው የቧልት ማህደሩ ውስጥ ያስነብበናል፡፡
ከሁሉም የገረመኝ ደግሞ በፊት ተላካፊ የነበሩት ወንዶች አሁን መልሰው እንደ ሴቶች እየተሸኮረመሙ ነው የሚለው ሰሞነኛ ወሬ ነው፡፡ ይህንን አጠናክሮ የነገረኝ አንዱ ቀንደኛ የፌስ ቡክ ደንበኛ አንዷ የሰፈሯን ወንድ ትላከፍና እርሱ ለእህቱ ይናገራል ከዚያም ልጅቷ ለጓደኞቿ ‹‹ለከፈችኝ ብሎ ለታላቅ እህቱ ሊናገር አልሄደም መሰላችሁ፤ እስኪ ምን እንደሚያመጣ አየዋለሁ!›› በማለት ቀድሞ ለወንዶች ተሰጥቶ የነበረውን ብሂል እንደወሰደች እያዘነ ነገረኝ፡፡
‹‹ምን ሴት ብታውቅ በወንድ ያልቅ›› የሚለውን አደገኛ ካንሠር ከሚተርቱት ሰዎች መካከል አንዱ ነበርኩ፡፡ ዛሬ ላይ የሴቶችን የመምራትና የስልጣን ባለቤትነት ስመለከት ንቀታችንን ሶስት አራት እጥፍ የሴቶች ጫንቃ ላይ እያሳረፍን መክረማችን በእጅጉ እያስቆጨኝ ነው፡፡ (ይቅር በሉኝ ሴቶች) ሴቶችን የረሳ፣ ሴቶችን የናቀ፣ ሴቶችን ተሳታፊ ያላደረገ ሥርዓት ይዞ የትም እንደማያደርስም ተገንዝቤአለሁ፡፡
በተረቶቻችን፣ በምሳሌዎቻችንና በጥቅሶቻችን በሰፊው እንደምንረዳው፤ የሴትን የበታችነት አጠንክረው የሚያሰምሩ ኃይለ ቃሎች እንዳሉ ነው፡፡ ነገር ግን የአገራችን ሴቶች የተረቱንና የምሳሌያዊ ንግግሩን ያህል ሳይሆን በሀገራችን የህብረተሰብ አወቃቀር መሰረት ከእናትነት አልፈው ከባድ የአገር ሃላፊነትን ተቀብለው እየሰሩ መሆናቸው አይካድም፡፡ ለዚህም ነው ‹‹በለው በለው ሲል ነው የወንድ አብነቱ ሴትም ትዋጋለች ከረጋ መሬቱ›› የሚል ድንቅ ምሳሌ የሚነገረው፡፡
በራስ መተማመንና ልበ-ሙሉነት የአንድ ህብረተሰብ ዋና ኃይል ነው፡፡ ይህንን ኃይል ለመገንባት ደግሞ ሴቶች ያላቸውን ሚና መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ የጾታ እኩልነትን አታከብርም ብለው የሚከሱ ሰዎች ከሚጠሯቸው ምስክሮች መካከል ‹‹ወንድ ወደ ችሎት ሴት ወደ ማጀት!›› የሚል አባባል ቀዳሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ መስከረም 1 ቀን መቁጠር ስትጀምር ነው ሴቶችንም እኩል አድርጋ የቆጠረችው፡፡ ይህ ቆጠራ እንደመብረቅ ብልጭታ ታይቶ የጠፋ ሳይሆን እንደ ቀትር ፀሐይ የጊዜ አድማስ ያልከለለው ነው፡፡ ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያችን ሴት ልጅን (ንግሥት ማክዳ) የአገር መሪ አድርጋ ስትሾም ያን ጊዜ ሌሎች አገራት የሴትን እኩልነት ቀርቶ ሰውነትን እንኳን አምነው አልተቀበሉም ነበር፡፡
ከማርች ስምንት አንድ ሳምንት ቀድመን በምናከብረው የአድዋ በዓል ከአፄ ምኒልክ ጐን ምንጊዜም ጣይቱ አለች፡፡ እቴጌ ጣይቱ ለአፄ ምኒልክ ባለቤታቸው ብቻ ሳትሆን የባርነት ጨለማን ከአፍሪካ ምድር ያራቁበት ፀሐያቸው ናት፡፡ ንግሥት ዘውዲቱም ብትሆን ለኢትዮጵያ ክብር እንስት ዘውድ ናት፡፡
እኔን የሚያስጨንቀኝ ጉዳይ አሁን ላይ ሴቶቻችን እንደተባለውም በመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊነት ውስጥ መጥተዋል፡፡ ነገር ግን በየሰፈሩ እንደምሰማቸው ቀልዶች ሴትን ከወንድ ጋር ብቻ እንዲፎካከሩ የማድረግ ስራ የጤንነት ምልክት አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም አንድን አካል ሁልጊዜ እንደተፎካካሪና እንደተቀናቃኝ ማሳየት በሂደት ፉክክሩ ወደ መተቻቸት እና ጥላቻ እንዲያዘነብል ያደርገዋልና፡፡
ሴቶችን ሰብስቦ እንዲህና እንዲያ እንድትሆኑ ያደረጓችሁ ወንዶች ቅኝ ስለገዟችሁ ነው እያሉ መለፈፍ ውጤቱ እንደ አገራችን ዘመንኛ ፖለቲካ መከባበር ሳይሆን መጠላላት ነው፡፡ ‹‹… እኩል ያልሆንኸው እገሌ የሚባል ብሔር ሲጨቁንህ፣ ሲበድልህ ስለኖረ ነው›› በሚል ስብከት የተመሠረተ የፖለቲካ ድርጅት ዓላማው በብሔሮቹ መካከል ፍቅርን ማጽናት ሳይሆን እርስ በርስ በማጣላት እርሱ ዳኛ ሆኖ ህልውናውን ማስቀጠል እንደሆነው ማለት ነው፡፡
ሴቶች ከወንዶች ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሳቸው ከሴቶች ጋርም መወዳደር አለባቸው፡፡ ሴቶች እኩል መሆን ያለባቸውም ከሰነፍ ወንዶች ጋር አይደለም ከጀግና ሴቶች ጋርም እንጂ፡፡ በእውነቱ ከሆነ እኛ አገር ውስጥ ባለው ሥርዓተ ጾታ ከሴቶች ይልቅ የተጎዳነው የበላይ የሆንን የሚመስለን ወንዶች ነን፡፡
የማጀቱ መጥፋት እህቶቻችን ወደ ችሎት ለመምጣታቸው ማረጋገጫ መሆን የለበትም፡፡ እህቶቻችን ሴት በመሆናቸው ውኃ መቅዳት፣ ወጥ መሥራት፣ ስፌት መስፋት፣ ፈትል መፍተልና ሌሎች መሰል ጥበባትን መተው አለባቸው የሚልም እምነት የለኝም፡፡(ወንዶችም በዚህ ስራ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው ሳልዘነጋ) ስለዚህ ውድድሩ መሆን ያለበት ወንዶች ከሴቶች ጋር እኩል ለመሆን ነው ወይስ ሴቶች እንደ ወንዶች ለመሆን የሚለው በራሳቸው በሴቶች ሊፈታ ይገባል፡፡
አዲሱ ገረመው