ዜና ትንታኔ
የናይል ወንዝ የትብብር ማሕቀፍ ባሳለፍነው ሳምንት ከእሁድ ጥቅምት ሦስት ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ እንደገባ ይፋ መደረጉ ይታወሳል። ስምምነቱ ከ11ዱ የተፋሰሱ ሀገራት መካከል ስድስቱ ሀገራት መፈረማቸውን ተከትሎም ነው ወደ ሥራ መግባቱ የታወቀው፡፡
በተለይ በስድስተኝነት ስምምነቱን ያጸደቀችው ደቡብ ሱዳን በስምምነቱ ውስጥ መካተቷ በናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ውስጥ ያለው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ሦስት አስርት ዓመታት ገደማ የፈጀው ይህ ስምምነት የማርቀቅ፣ የድርድርና የማፅደቅ ሂደት ባሳለፍነው ሳምንት መቋጫውን ያገኘ ሲሆን፤ በውስጡም 45 አንቀጾች የያዘ የያዘ እንዲሁም ለተግባራዊነቱ ከ11ዱ ሀገራት ስድስቱ እንዲፈርሙ መርህ የሚያስቀምጥ ነው፡፡
ስምምነቱ መጽደቁ እ.አ.አ በ1929 እና 1959 በግብጽና ሱዳን መካከል የተደረገው የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት የሚቀለብስ፣ ቀጣናዊ ትብብርን የሚያጠናክርና የውሃ ሀብት አስተዳደርን በተመለከተ ሚዛናዊ አካሄድ እንዲኖር እንደሚያደርግም ይጠበቃል፡፡
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ወደ ተግባር መግባቱ በዓባይ ውሃ ኢትዮጵያ ላይ የሚቀርቡ ምክንያት አልባ ክሶችን የሚያስቀር ስለመሆኑም የተደበቀ እውነት አይደለም፡፡
ስምምነቱ መጽደቁ የቀጣናው የውሃ ፖለቲካ ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ይኖረዋል? ያለውስ ፋይዳ ምንድነው? ስምምነቱ እንዲጸድቅስ የኢትዮጵያ ሚና ምን ነበር? እንዲሁም በስምምነቱ ያልተካተቱ ሀገራት ለማሕቀፉ ተፈጻሚነት የሚቋቋመው ኮምሽን ላይ እክል ሊፈጥሩ የሚችሉበት ሁኔታ አለ ወይ? ሲል ኢፕድ የዘርፉ ምሁራንን አነጋግሯል።
የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ተመራማሪና የህዳሴው ግድብ ተደራዳሪ ቡድን የሕግ አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ እንደሚሉት፤ ስምምነቱ የተፋሰሱ ሀገራት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል እንዲሁም የቀጣናውን ልማትና ትብብር የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ስምምነቱ መጽደቁ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሥራ ውጤት የሚያሳይ ነው የሚሉት አምባሳደር ኢብራሂም፤ በተለይ ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን እንድታጸድቀው ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች ይላሉ፡፡
ከውሃ ፖለቲካው አንጻርም አስተማማኝ የሆነ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት መብት ያረጋገጠ፣ ሱዳንና ግብጾች እየሄዱበት የነበረው መንገድ ትክክል አለመሆኑ በተግባር ያሳየ ነውም ባይ ናቸው፡፡
እንደ አምባሳደር ኢብራሂም ገለጻ፤ በስምምነቱ መሠረት ስድስት ሀገራት ካጸደቁት ሕጋዊ ሆኖ በሥራ ላይ መዋል ይጀምራል፡፡ ስምምነቱን ያላጸደቁ ሀገራት ለትብብር ማሕቀፉ በሚቋቋመው ኮሚሽን የሥራ መሠናክል የሚሆኑበት አግባብ የለም፡፡
አምባሳደር ኢብራሂም እንደሚሉት፤ እ.ኤ.አ በ1959 ሱዳንና ግብጽ ባደረጉት ስምምነት መሠረት ግብጽ 55 ነጥብ አምስት ቢሊዮን እንዲሁም ሱዳን ደግሞ 18 ነጥብ አምስት ቢለዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ በዓመት እንዲያገኙ የሚደነግግ መሆኑን አስታውሰው፤ ይህም በሌላ አነጋገር የሚሄደው ውሃ ሁሉ ሱዳንና ግብጽ ብቻ እንዲጠቀሙ የሚያዝ እና ሌሎቹ ሀገራት ውሃ የማግኘት መብታቸውን የሚነፍግ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
በቅርቡ ጸድቆ ወደ ትግበራ የገባው የናይል ወንዝ የትብብር ማሕቀፍም ይህንን የበላይ ተጠቃሚነት የሚያስቀርና የቅኝ ግዛት ውሎቹን ከጥቅም ውጪ የሚደርግ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
የጋራ ተጠቃሚነት እንዲኖር ለማድረግ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥና በላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ሕጋዊ ጥያቄ ለማቅረብ በስምምነቱ ውስጥ መካተት ግድ በመሆኑ የናይል ወንዝ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ከማንም በላይ ተጠቃሚ የሚያደርገው የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ነው ያሉት ደግሞ የውሃ ሀብት ባለሙያ እና የቀድሞ የህዳሴው ግድብ ተደራዳሪ ፈቅአህመድ ነጋሽ ናቸው፡፡
ስምምነቱ ውሃ አጠቃቀም ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን የውሃ ጥበቃና እንክብካቤ፣ ቁጥጥር፣ የውሃ አስተዳደርን የተመለከተ፣ ውሃን በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም ተጨማሪ የውሃ ሀብት ማፈላለግ የሚያግዝ መሆኑንም ነው የሚገልጹት፡፡
በማሕቀፉ ውስጥ ያልተካተቱ ሌሎች ሀገራት የውሃ አጠቃቀም መረጃ እንዲኖራቸው፣ የሀብት ክፍፍሉ ላይም ውሳኔ ሰጪ ለመሆን እንዲሁም በቀጣናው የትብብር ልማት ላይ ተጠቃሚ ለመሆን ስምምነቱን ማጽደቅ ይኖርባቸዋል የሚሉት ባለሙያው፤ አለበለዚያ በጀርባቸው የሚወሰነው ውሳኔ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው የሚችል መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
ባለሙያው እንደሚሉት፤ ስምምነቱን ያልፈረሙ ሀገራት መች ይቀበሉታል የሚል እንጂ አይቀበሉትም የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረው፤ በተለይ ኮሚሽኑ ጠንካራ ኃላፊነት ተሰጥቶት ትላልቅ ውሳኔዎች የሚያሳልፍ ከሆነ ረጅም ጊዜ የማይፈጅ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ ፈቅአህመድ ገለጻ፤ ስምምነቱ በሀገራት መካከል የሚነሱ የተለያዩ የልማት ጫናና ስጋት ለመቀነስ፣የራስን የልማት ወሰን በትክክል ለማወቅ፣ የተለያዩ ድጋፎች ለማግኘት፣ ለልማቶቹ ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ከለላ ለማግኘት እንዲሁም ከውሃውም ባሻገር ትብብሮችን የማጠናከር እድሎች ይኖሩታል፡፡
ድርድሩ ገና አላለቀም፤ ለቀሪው ድርድር ከወዲሁ መዘጋጀትና ኮሚሽኑም ጠንካራና ፍትሐዊ እንዲሆን የአሰራር ሥርዓቱም እንዲዘምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ፡፡
ስምምነቱ የቅኝ ግዛት ውሎች እንዲወገዱ አስገዳጅና ከዓለም ሕግጋት ጋር የተጣጣመ ስለሆነ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቀላሉ እንዲቀበለው ያደርጋል ይላሉ፡፡
ስምምነቱን ያጸደቁ ሀገራት ስምምነቱን ለማስፈጸም የሚቋቋመው ኮሚሽን ውጤት እንዲያስገኝና ከሚሰነዘሩት የተለያዩ ሴራዎች ለመውጣትም ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡
በዚህም ተባለ በዚያ ግን በጥቅሙ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያከናወነችው ዲፕሎማሲያዊ ሥራ እና የቀጣናውን ሀገራት በትብብር ማሕቀፍ እንዲስማሙ የምታደርገው ጥረት ውጤታማ ሆኗል። በቀጣይም ይህን ዲፕሎማሲያዊ ጥረትና አቅም አጠናክሮ መቀጠሉ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይገባል።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም