ኢትዮጵያን ጨምሮ ቡና አብቃይ የአፍሪካ ሀገሮች 25 እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። በአመት ከ600 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ቡና በማምረት የቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ቀዳሚ ናት።
የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ባለው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድርሻም ‹አረንጓዴው ወርቅ› የሚል ስያሜ እንደተሰጠው አይዘነጋም። በአሁኑ ወቅት ለውጭ ገበያ የተመረተ ቡና መጋዘን ማጣበቡ የዘርፉን ተዋናዮች ቁጭት ብቻ ሳይሆን አጣብቂኝ ውስጥም ከቷቸዋል።
የኦሮሚያ ግብርና ተፈጥሮ ሀብት እና የቡናና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድሳኒ አሚን እንደገለጹት ለውጭ የሚቀርብ የአንድ ቶን ቡና ዋጋ ለሀገር ውስጥ ከሚቀርበው ተመሳሳይ መጠን ጋር በዋጋ ሲነጻጸር በ370 ዶላር ዝቅተኛ ነው። ችግሩ ቢኖርም በብዛትም በጥራትም እንዲመረት በመንግሥት በኩል የስልጠና እንዲሁም በቡና ላይ የሚካሄድ ምርምር እንዲጠናከር አስፈላጊው ድጋፍ አልተቋረጠም ይላሉ።
በአምስት መቶ ሄክታርና ከዚያ በላይ በሆነ መሬት ላይ የሚያመርቱ አርሶ አደሮችም በግላቸው የውጭ ገበያ አፈላልገው እንዲያቀርቡ በቡናና ሻይ ባለስልጣን ፈቃድ የመስጠት ሥራ ተጀምሯል። መንግሥት እንዲህ የተለያዩ አማራጮች ከማፈላለግ ጎን ለጎን ከአርሶአደሩና ከላኪው ጋር ሲመክር ቢቆይም ለሀገር ውስጥ የሚቀርበው ለውጭ ከሚቀርበው በዋጋ የተሻለ መሆኑ ችግሩን አሳሳቢ ማድረጉን አቶ መሐመድሳኒ ይናገራሉ።
ችግሩ የሁሉም አፍሪካ ሀገራት ቢሆንም የሌሎቹን የባሰ የሚያደርገው የሀገር ውስጥ የቡና ፍጆታቸው ዝቅተኛ መሆኑ ነው። ቡና የሚጠጣ ማህበረሰብ ባለማፍራታቸው ምርታቸው ይወድቃል። ኢትዮጵያ ቡና የሚጠጣ ማህበረሰብ ያላት በመሆኗ ተጠቃሚነቷ ከፍተኛ እንደሆነ ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። አፍሪካውያን የጋራ ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት ምክክር ጀምረዋል። ምክክራቸውንም በአዲስአበባ ከተማ ሰሞኑን በቶጎ ሎሜ ላይ ደግሞ ቀደም ሲል አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እዳስረዱት የእርስበርስ የገበያ ትስስርን በማጠናከር የቡና ግብይትን በማሳደግ እንዲሁም አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው የመፍታት ባህልን ለማዳበር ዓላማ ያደረገ ምክክር ሲሆን፣እያንዳንዱ ሀገር በተለይም በሀገር ውስጥ ያለውን የቡና ፍጆታ ጠንካራና ደካማ ተሞክሮ ለይቶ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ነው። አምስት መቶ ሺ ዶላር በጀት ተመድቦለት የሁለት አመት ፕሮጀክት ስልጠናና የምርምር ፕሮግራም ተቀርጾ ስራ ጀምሯል ።
ዶክተር አዱኛ እንዳሉት በሀገር ውስጥ የቡና ፍጆታ ኢትዮጵያ የተሻለ ተሞክሮ አላት። ኬንያም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በማሳተፍ ስለቡና ጥቅም የማህበረሰብ ግንዛቤ በማሳደግ ባከናወነችው ተግባር የተጠቃሚውን ቁጥር ከሁለት በመቶ ወደ አምስት በመቶ ለማሳደግ ችላለች። በአፍሪካ በደረጃ መልካም ተሞክሮ ያላቸው ቢጠቀሱም እንደሴራሊዮን ባሉ ሀገራት ቡና የመጠጣት ባህል የሌላቸውና ቢጠጡም የተዘጋጀ ገዝተው የሚጠቀሙ ደግሞ ጥቂት አይደሉም። ይህም በዓለም ላይ የቡና ዋጋ ሲወድቅ የተመረተው ምርት እንዲባክን አድርጓል።
በሚቀጥሉት ሁለት አመታት በፕሮጀክቱ በተገኘው ድጋፍ የህክምናና የተለያዩ ባለሙያዎችን በማሳተፍ ግንዛቤ የማስጨበጫ ትምህርት፣ ጥራት ያለው የቡና አመራረት ዘዴ፣ በአፈላልና በማቀነባበር ዙሪያ ስልጠና እንደሚሰጥ እና የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግ ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ቡና ፍጆታ ልምዷን በማካፈል የተሻለ ዕድል ይኖራታል። የገበያ ዕድሏን ወደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማስፋትም ያግዛታል ብለዋል። በፕሮጀክቱ ድጋፍም በባለስልጣኑ ግቢ ውስጥ ስለቡና አፈላል ስልጠና የሚሰጥበት ማዕከል እንደሚቋቋም ጠቁመዋል።
በዓለም ላይ ለቡና ዋጋ መውደቅ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ቡና አቀነባብሮ ወይም እሴት ጨምሮ ማቅረብ ለአፍሪካውያን ከችግሮቹ ውስጥ አንዱ እንደሆነ የሚጠቁሙት ዶክተር አዱኛ ጥሬ ቡና ለገበያ ማቅረብ በገዥው የሚወሰን በመሆኑ ማትረፍ እንደማይቻልና ለአብነትም ሩዋንዳ 99 በመቶ ጥሬ ቡና ለገበያ አቅርባ አንድ ከመቶ እንኳን ጥቅም እንደማታገኝ አስረድተዋል። ብዙ ምርት መቅረብና የጥራት ጉድለትም ለዋጋው መውረድ መንስኤዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ችግሮችን ለመፍታት ከተወሰዱት እርምጃዎችም የቡና ጥራትና ግብይት አዋጅ ማጽደቅ አንዱ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር አዱኛ አዋጁ በ2009 ዓ.ም የጸደቀ ሲሆን፣ በተያዘው በጀት አመት ደግሞ ደንብና መመሪያ ወጥቷል።
አዋጁ ከያዛቸው ዋና ዋናዎቹ ለሀገር ውስጥና ለውጭ አገር ምን አይነት ቡና መቅረብ እንዳለበት፣ ጥራትና እሴት ጨምሮ ማቅረብ ስለሚቻልበት ሁኔታ ጥቂቶቹ ናቸው። ስምንት አማራጮችን ያስቀመጠው አዋጁ ረጅም የግዥ ሰንሰለት ለመቀነስ ከማገዙ በተጨማሪ አርሶ አደሩ በማሳው ላይ እንዳለ ግብይት የሚፈጽምበትንና በቀጥታም ለውጭ እንዲያቀርብ ዕድል ያመቻቻል።
የማምረት አቅምን ለማሳደግ የንቅናቄ መድረኮች እንደሚከናወኑና ከ50ሺ ሄክታር በላይ አሮጌ ቡናዎችን በአዲስ የመተካት እንዲሁም በሽታ መከላከል የሚችሉ የተሻለ ዝርያ ያላቸውን የቡና ችግኞች የመትከል ሥራ ለማከናወን እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። በአቅራቢና ላኪ መካከል እንዲሁም ከቅሸባ ጋር ተያይዞ የሚቀርበውን ቅሬታ ለማስቀረትም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ግብረሐይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።
ላለፉት 27 አመታት በቡና ሥራ፣ ለስምንት አመታት ደግሞ ኢንተርአፍሪካ ኮፊ በተባለ ድርጅት ውስጥ የአፍሪካ ቡና ምርምር ዋና ዳይሬክተር ሆነው የሰሩትና በምርምርም ዘርፉን በማገዝ ላይ የሚገኙት ዶክተር ባዬታ በላቸው አፍሪካውያን የጀመሩት እንቅስቃሴ ለዘርፉ ተስፋ ሰጭ እንደሆነ ይናገራሉ።
በዘርፉ በቆዩባቸው ጊዜያቶች በኢትጵያ ሰፊ የምርምር ሥራ ሲሰራ መቆየቱን፣ ጠንካራ የምርምር ማዕከላት መኖራቸውንና በተከናወኑት የምርምር ሥራዎችም 40 ምርጥ ዝርያዎችን ማበርከት መቻሉን አስረድተዋል።
ቡና መኖሪያው ጫካ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ባዬታ የጫካው መመናመን ዘርፉን እየጎዳው መሆኑንና በዚህ ላይ ተከታታይ ሥራ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል። የምርምር ሥራዎች በበጀት ካልተደገፉ ምርምር ብቻውን ውጤት አይሆንም ብለዋል። የገንዘብ እጥረቱ በምርምር የተዳቀለ የቡና ዝርያን ለመተግበር ማነቆ መሆኑንም ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2011
ለምለም መንግሥቱ