የአውስትራሊያው ግዛት ወንጀል የፈፀሙ የ10 ዓመት ታዳጊዎች እንዲታሠሩ አወጀ

የአውስትራሊያዋ ኖርዘርን ቴሪተሪ ግዛት ዕድሜያቸው 10 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሕፃናት ወንጀል ከፈፀሙ ሊታሰሩ ይችላሉ የሚል ሕግ አወጣ። የአውስትራሊያ ግዛቶች ሕፃናት ማረሚያ ቤት የሚገቡበት ዕድሜ ከ10 ወደ 14 ከፍ እንዲያደርጉ ከተባበሩት መንግሥታት ጭምር ጫና እየተደረገባቸው ቆይቷል።

ባለፈው ዓመት የኤንቲ ግዛት ዕድሜውን ወደ 12 ከፍ አድርጎት ነበር። ነገር ግን ነሐሴ ላይ ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ አስተዳደር ወጣቶች ከወንጀል እንዲቆጠቡ በማለት የዕድሜ ጣራውን ወደ 10 ዝቅ አድርጎታል። አዲሱ ሕግ ሕፃናትን ለመጠበቅ የወጣ ነው ሲሉ ባለሥልጣናት ተከራክረዋል። ዶክተሮች፣ የመብት ተሟጋቾች እና የአውስትራሊያ የቀደምት ማኅበረሰብ አባላት ሕጉን ተቃውመውታል።

ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ሕጉ አቦሪጂናል እና ቶሬስ ሰትሬይት አይላንደር የተባሉት ቀደምት ማኅበረሰብ ሕፃናትን የበለጠ የሚጎዳ ነው። ኖርዘርን ቴሪተሪ ግዛት ከሌሎች የአውስትራሊያ ግዛቶች ሲነፃፀር 11 እጥፍ ሕፃናት የሚታሠሩበት ግዛት ሲሆን አብዛኛዎቹ አቦሪጂናል ናቸው።

የአውስትራሊያ ግዛቶች በወጣቶች በሚፈፀሙ ወንጀሎች እየታመሱ ሲሆን በኤንቲ ግዛት አሊስ ስፕሪንግስ በተሰኘችው ከተማ ለወጣቶች ብቻ ሰዓት እላፊ ታውጇል። የግዛቱ ዋና ሚኒስትር ሊያ ፊኖቺያሮ “ሕፃናትን የመጠበቅ እና የማኅበረሰቡን ደኅንነት የማስከበር ግዴታ ስላለብን ነው” ሕጉን ያወጣነው ብለዋል።

አብዛኛዎቹ ሕፃናትና ታዳጊዎች ሰብሮ በመግባት እና ሰዎች ላይ ጉዳት በማድረስ ነው ወንጀል የሚፈፅሙት። ኖርዘርን ቴሪተሪ ግዛት ሕፃናት ጥፋት አጥፍተው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በዋስትና የሚወጡበትን ሕግም ጠበቅ አድርጓል። ነገር ግን አውስትራሊያ ውስጥም በመላው ዓለም የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሕፃናትን ማሰር የበለጠ ወንጀሎች እንዲሠሩ ከማበረታቱም በላይ ጤናቸው፣ ትምህርት እና ሥራ የማግኘት ዕድላቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል።

በመንግሥት የሚተዳደረው ገለልተኛው የአውስትራሊያው ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው ዘገባ አዳዲሶቹ ፖሊሲዎች “ሕዝባዊ” በሆኑ እና “ጠንካራ ሕግ” በማውጣት በሚያምኑ አስተዳደሮች ነው ተግባራዊ የሚደረጉት ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You