የኬንያ ሴናተሮች ምክትል ፕሬዚደንቱ ሪጋቲ ጋሻጉዋን ለሕክምና ሆስፒታል ሳሉ ከሥልጣን አሰናብተዋቸዋል። የምክትል ፕሬዚደንቱ ጠበቃ እንዳሉት ጋሻግዋ ሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ተገኝተው ከሥልጣን የተነሱበትን ምክንያት ማዳመጥ ያልቻሉት ሆስፒታል በመግባታቸው ነው።
በድራማ የታጀበ በተባለለት ቀን ነው ጋሻግዋ ባልተገኙበት ከመንበራቸው የተነሱት። ምክትል ፕሬዚደንቱ ከሰዓት በኋላ በሴኔቱ ተገኝተው ራሳቸውን ይከላከላሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ጋሻግዋ የቀረቡባቸውን 11 ክሶች በፍፁም አልፈፀምኩም ሲሉ ያስተባብላሉ።
በኬንያውያን ዘንድ ሪጊ ጂ በተሰኘ ቅፅል ስማቸው የሚታወቁት ምክትሉ ደረታቸው ላይ በተሰማቸው ሕመም ምክንያት ካረን በተባለው ሆስፒታል ሕክምና እያገኙ ስለሆነ ቀኑ ይራዘም ሲሉ ጠበቃቸው ጠይቀው ነበር። ነገር ግን ሴናተሮቹ የፍርድ ሒደታቸው እሳቸው ባልተገኙበት እንዲካሄድ ወስነዋል። የጋሻግዋ ጠበቆች ይህን ውሳኔ በመቃወም ምክር ቤቱን ለቀው ወጥተዋል።
ጋሻግዋ ከፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ ጋር ያላቸው ግንኙነት መሻከር ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት እስከ ቅዳሜ ድረስ አንታገስም ማለታቸው ምክትል ፕሬዚደንቱን ከሥልጣን ለማባረር ምን ያህል ቆርጠው እንደተነሱ ያመላከተ ሆኗል።
ባለፈው ሳምንት አብላጫው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ብሔራዊው ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝደንቱን ለማባረር ድምፃቸውን ሰጥተዋል። ከዚህ ሒደት ቀጥሎ ነው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ክርክር በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ማድረግ የነበረባቸው።
ማውንት ኬንያ ከተባለው ማዕከላዊው የሀገሪቱ ክፍል የመጡት ምክትል ፕሬዚደንቱ በሀብት የናጠጡ ነጋዴ ናቸው። ጋሻግዋ ከሥልጣን መባረራቸውን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ይህ “ፖለቲካዊ ግድያ” ነው ብለዋል።
ሐሙስ ምሽት ከ67 የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት ሁለት ሶስተኛው ምክትል ፕሬዚደንቱ በቀረበባቸው ክስ ምክንያት ከሥልጣን መወገድ አለባቸው ሲሉ ድምፃቸውን ሰጥተዋል። ምክር ቤቱ እንደሚለው ምክትል ፕሬዚደንቱ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል በአምስቱ ጥፋተኛ ናቸው። በብሔር መካከል ክፍፍል መፍጠር እና ሲሾሙ የገቡት ቃል አለማክበር ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል ናቸው።
ጋሻግዋ ሙስናን ጨምሮ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ማድረግ የሚሉ ክሶች ቀርበውባቸው የነበረ ቢሆንም ነፃ ወጥተዋል። ዊሊያም ሩቶ እና ጋሻግዋ ወደ ሥልጣን ከመጡ ሁለት ዓመታት አስቆጥረዋል። ነገር ግን ከወራት በፊት ነው አለመግባባት ውስጥ መግባታቸው የተሰማው።
ባለፈው ሰኔ ጋሻግዋ የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ በኬንያ ግብርን ምክንያት በማድረግ ተነስቶ ስለነበረው ተቃውሞ ለፕሬዚደንቱ ተገቢ መግለጫ አልሰጡም ሲሉ መውቀሳቸው ይታወሳል። ይህ ድርጊታቸው ፕሬዚደንቱን እንደመናቅ ተደርጎ ተቆጥሮባቸዋል።
በኬንያ የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ፕሬዚደንት ሩቶ ሊተገብሩት የነበረውን ግብር ማንሳታቸው አይዘነጋም። አልፎም የካቢኔ አባላቱን ሙሉ በሙሉ አባረው አዳዲስ ሚኒስትሮች ቀጥረዋል። ሩቶ የምክትላቸውን ከሥልጣን መነሳት በተመለከተ እስካሁን ያሉት ነገር የለም ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም