በምግብ ሸቀጦች ላይ የሚለጠፈውና የምርቶቹ የአገልግሎት ዘመን የሚገለጽበት አሰራር ግልጽ ያልሆነና ሌላ ድብቅ ዓላማ ያለው ነው የሚል ጥርጣሬ ያደረበት የሜሪላንድ ነዋሪ የሆነ አንድ አሜሪካዊ አሰራሩ ትክክል አለመሆኑን ለማሳየትና ዕውነታውን ለህብረተሰቡ ለማሳወቅ የአገልግሎት ዘመኑ ካለፈበት ድፍን ዓመት የሞላውን እርጎ በመጠጣት በራሱ ላይ ጀብደኛ ሙከራ አካሂዷል።
ምግብ አምራች ኩባንያዎች የምርቶቻ ቸውን የአገልግሎት ዘመን የሚገልጹበት አሰራር ሁሌም ያስገርመው እንደነበር የገለጸው ስኮት ናሽ የተባለው ይህ ግለሰብ በተለይም ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል በጉዳዩ ላይ ደጋግሞ ሲያስብበት ከቆየ በኋላ “ሞክሬ ማረጋገጥ አለብኝ” የሚል ውሳኔ ላይ መድረሱን …ከሰሞኑ አስነብቧል።
የአገልግሎት ዘመኑ በማለፉ መወገድ ሲገባው ፍሪጅ ውስጥ ተረስቶ ዓመት ሙሉ የቆየውን እርጎ ከአትክልት ሾርባ ጋር በመቀላቀል ጭልጥ አድርጎ ጠጥቶታል። ሆኖም እርጎው ምንም እንኳን ጣዕሙ ጥሩ ያልነበረ ቢሆንም ሚስተር ናሽ ላይ ግን ምንም ዓይነት የጤና ችግር አለመፍጠሩን ገልጿል።
“ኩባንያዎች የአገልግሎት ዘመናቸ ውን የሚገልጹበት አሰራር በጣም ግራ የሚያጋባና ሰዎችን የሚያወዣብር ነው። ጊዜው ያለፈበት ማለት ምን ማለት ነው? “እስከ …ቀን ድረስ ቢጠቀሙት ተመራጭ ነው”፣ “እስከ …ቀን ድረስ ሊሸጥ የሚችል”፣ “ለ…የበለጠ ተመራጭ ነው” በማለት ነው የምርቶቻቸውን የአገልግሎት ዘመን የሚገልጹት። ሆኖም ይህ ዓይነቱ አገላለጽ ወጥነት የማይታይበት በመሆኑ በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ መደናገርን ፈጥሯል ብዬ አስባለሁ” ብሏል በአንድ ድረ ገጽ ላይ በጻፈው ጦማር።
ስለሆነም የምርቶች የአገልግሎት ዘመን የሚገለጽበት አሰራር ግልጽነትን በተከተለ መንገድ እንደገና ሊከለስ ይገባል በማለት ኩባንያዎችን ሞግቷል። ከዚህም በተጨማሪ የአገልግሎት ዘመንን የሚገልጹት ቀኖች ከእውነታው ጋር የሚዛመዱ መሆን እንዳለባቸው አሳስቧል።
“አንዳንድ ምርቶችም ከነጭራሹ የአገልግሎት ዘመንን መግለጽ የማያስፈ ልጋቸው ናቸው” የሚለው የሥራ ፈጠራ ባለሙያው ሚስተር ናሽ ለአብነትም በጨው የታሸጉ ምግቦችንና ከአገልግሎት በኋላ ወዲያውኑ የሚጣሉ የህጻናት ንጽህና መጠበቂያ ጨርቆችን ይጠቅሳል። የተመራማሪው ሙከራ እንዲህ ብናካፍላችሁም እናንተ ግን እንዳትሞክሩት አደራችን ይድረሳችሁ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 4/2011
ይበል ካሳ