በህንድ ቢዛሬ ከተማ ነዋሪ የሆነው የ20 አመቱ ወጣት ሞሃመድ ፉርቃን ድንገት ይታመምና ወላጆቹ በአቅራቢያው በሚገኝ አንድ የግል ሆስፒታል ይወስዱታል። ወላጆቹ ጥሩ ህክምና እንዲያገኝ ነበር ወደ ሆስፒታሉ የወሰዱት። ልጃቸው ቶሎ እንዲድንላቸውም ያላቸውን ጥሪት አሟጠዋል። የወጣቱ ወላጆች እንዳሰቡት ስለልጃቸው መልካም ሳይሆን የጤና መሻሻል እንዳልታየበት ነው ከሀኪሙ የሰሙት። ልጃቸው በህይወት እንዲተርፍላቸው በእነርሱ በኩል የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል።
ልጃቸው እንዲድን ያደረጉት የገንዘብ ወጭና ጉጉታቸው ከፍተኛ የነበሩት የፉርቃን ወላጆች ጥረታቸው ወደ ሀዘን ተለወጠ። የፉርቃን ህይወት አለፈ። ቤተሰቡ በመሪር ሀዘን ልቡ ተሰበረ፣ ዘመድ አዝማድም ተሰባስቦ እየተላቀሰ ሲያረፍድ ዋለ። የቀብሩን ስነሥርዓት ለማከናወንም የፉርቃን አስክሬን ወደ መኖሪያቤቱ ተወሰደ።
የፉርቃን አስክሬን በመኖሪያቤቱ ውስጥ ጸሎትና ስንብት እየተደረገለት ሳለ ግን አንድ ግርምት የሚፈጥር ነገር ተከሰተ። ሁሉም ቤተሰብ የፉርቃንን አስክሬን በመሰናበት ላይ እያለ የሞሃመድ ፉርቃን ታላቅ ወንድም ከሌሎቹ ሀዘንተኞች በተለየ የወድሙን አስክሬን አተኩሮ ይመለከት ነበር። አይኑን ማመን እስኪቸገር ድረስ ያልጠበቀው ነገር ተመለከተ። ‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም› እንደሚለው የሀገሬ ሰው አይነት ነበር የተፈጠረው ነገር። የወንድሙ አስክሬን ከንፈሮቹ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ተመለከተ። አስክሬኑን ተጠግቶ ትኩር ብሎ ተመለከተ። ያየው ነገር እውነት ነበር።
የሞሃመድ ፉርቃን ታላቅ ወንድም ባየው ነገር ተደናገጠ። ለቀብር የተዘጋጀ ሬሳ ነፍስ ይዘራል ብሎ ማን ያምናል። ሰውነቱ ተብረከረከ። እጅግ ከመደንገጡ የተነሳ መናገር ተሳነው። ስሜቱን ተቋቁሞ ያየውንና የሆነውን ሁሉ ለቤተሰቡና ለሀዘንተኛው ነገራቸው። በሀዘን ውስጥ የነበረው ሰው ሁሉ ተደናገጠ። ነገሩን ለማረጋገጥም ወደ አስክሬኑ በመጠጋት ተመለከተ። እውነትም የፉርቃን ከንፈሮች እየተንቀሳቀሱ ነበር። ባዩት ነገር ተገረሙ። አንዳንዶችም ተደናገጡ። ግራም ተጋባ። ቤተሰቡም በዚህ ባልተለመደ ነገር መደነቅ ብቻ ሳይሆን ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ መታየት እንዳለበትም ወስኖ ለምርመራ ወደ ሆስፒታሉ ተወሰደ። ወደ ሆስፒታሉ የተወሰደው አስክሬን ወይንስ የታመመ ሰው? ግራ የሚያጋባ ክስተት ነበር በወጣቱና በቤተሰቡ ላይ የተፈጠረው። ቤተሰቡ ቀደም ሲል የልጃቸውን መሞት ወደ ነገራቸው ሆስፒታል ሳይሆን ሌላ ሆስፒታል ነበር ለምርመራ የወሰዱት። ቀደም ሲል ህክምናውን የተከታተለበትን ሆስፒታል ስለተጠራጠሩት ነበር ሌላ ጋር የወሰዱት።
ቤተሰቡ የሆነውን ለማረጋገጥ ለምርመራ የሞሃመድ ፉርቃን አስከሬንን ወደ ራም ማናሆር ሆስፒታል ይዘው ቢሄዱም ቀጥሎ የሚሆነው ነገርም አስጨንቋቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የምርመራውን ውጤት ለማየት ጓጉተዋል። ቤተሰቡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በመጨረሻም አስደሳች ዜና ነበር የሰሙት።ፉርቃን በህይወት መኖሩን ሀኪም ለቤተሰቡ ሲያረጋግጥላቸው በወቅቱ የተደበላለቀ ስሜት ነበር በቤተሰቡ ላይ የተፈጠረው።
የሞሃመድ ፉርቃን ታላቅ ወንድም ለሪፖርተርስ እንደገለጸው ‹‹በወንድሜ መሞት በጣም ነበር ያዘንኩትና ያለቀስኩት። በአስክሬን ሽኝት ወቅት ነበር ወድሜን ለመጨረሻ ጊዜ ስሰናበተው ከንፈሮቹ ሲንቀሳቀሱ ያየሁትና ባየሁትም ነገር የተገረምኩት። በወቅቱ አይኔን ማመን ሁሉ አቅቶኝ ነበር። ያየሁትን ለሀዘንተኞች ስነግራቸው እነርሱም እንደእኔ ነበር የተደናገጡት። ሁሉም ካየ በኋላ ለምርመራ ሆስፒታል እንዲሄድ ውሳኔ ላይ ደረሰ›› በማለት ነበር የነበረውን ሁኔታ ያስረዳው። ለምርመራ የወሰድንበት ሆስፒታል ሀኪም በህይወት መኖሩንና የኦክሲጂን እርዳታ እያደረጉለት እንደሆነ ሲነግሩት ማመን እንዳልቻለና ሞቷል ብሎ ሲያለቅስ የነበረው ወንድሙ በህይወት መኖሩ ሲነገረው የነበረውን ስሜት መገመት እንደሚቻል በደስታ ስሜት ውስጥ ሆኖ ነበር የተናገረው።
የሞሃመድ ፉርቃንን በህይወት መኖር ያረጋገጡት ሀኪም ለሪፖርተርስ እንደገለጹት ‹‹ሞቷል ተብሎ ለቀብር የተዘጋጀው አስክሬን ሆስፒታል በደረሰ በህክምና ማረጋገጥ እንደተቻለው የልብ ምቱም የደም ዝውውሩም ይሰራ ነበር። በመጀመሪያም የትንፋሽ እጥረቱን ለማስተካከል እርዳታ ተደርጎለታል።
ጉድ ያሰኘው ይህ ክስተትም ሞሃመድ ፉርቃን መጀመሪያ የታከመበት ሆስፒታል በጥርጣሬ እንዲታይና ለትችትም ዳርጎታል። የአካባቢው ባለስልጣናትም በቀድሞው ሆስፒታል ላይ ክስ እንዲመሰረትበትና የሚሰጠው ህክምናም በምርመራ እንዲጣራ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ያለበቂ ማረጋገጫ ያልሞተ ሰው ሞቷል በማለቱ እየተብጠለጠለ የሚገኘው ሆስፒታል በበኩሉ ታማሚው በሆስፒታሉ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ክትትልና ድጋፍ እንደተደረገለት ገልጿል። ሳይሞት ሞቷል መባሉ ግን የመመርመሪያ መሳሪያው ብልሽት እንደሆነና ይህም ሊያጋጥም እንደሚችል ነው የተናገረው።እንዲህ ናት ሙያ በመሳሪያ ማሳበብ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 4/2011
ኢያሱ መሰለ