‹‹በዩኒቨርሲቲው የተደረገ የፕሮግራም መዛባት የለም›› – የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ
የዛሬው የፍረዱኝ አምድ ዝግጅታችን ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ይወስደናል። በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች እና በጤና ሳይንስ ተማሪዎች መካከል የተፈጠረን ውዝግብ ያስመለክተናል።
‹‹በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ድክመት እና በፕሮግራም ያለመመራት ችግር መመረቅ በነበረብን ጊዜ መመረቅ አልቻልንም። ዩኒቨርሲቲው አመራሮች በደል እየፈጸሙብን ነው›› ሲሉ የጤና ሳይንስ ተማሪዎች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድን አቤት ብለዋል።
የምርመራ ቡድኑም የተማሪዎቹን ቅሬታ እና የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ምላሽን ይዟ ቀርቧል።
ከአቤቱታ አቅራቢዎች አንደበት
ለምርመራ ቡድኑ አቤቱታ ያቀረቡት ተማሪዎች በርካታ ቢሆኑም ተፈጸመ የተባለውን ችግር ያሳያሉ ያልናቸውን የተወሰኑ ተማሪዎች አቤቱታ ወስደናል። ተማሪዎቹ ስማቸውም እንዳይጠቀስ ስለጠየቁ ስማቸው አልተገለጸም።
አቤቱታ አቅራቢ – አንድ
አቤቱታ አቅራቢ አንድ እንደገለጸው፤ ወደ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የገባው በ2015ዓ.ም። በዩኒቨርሰቲውም በጤና ፋካሊቲ በፋርማሲ ትምህርት ክፍል ተመደበ። ይሁን እንጂ እሱ እና ጓደኞቹ ትምህርት በጀመሩበት ዓመት የአንድ መንፈቀ ዓመት ትምህርት ብቻ ተምረው ወደ ቤተሰብ እንዲሄዱ ተደረገ። በሌሎች ዩኒቨርሲቲ ተመድበው የነበሩ ጓደኞቻቸው ግን የሶስት መንፈቀ ዓመት ትምህርት መማር ችለው ነበር። ቀጥሎ በነበረው የትምህርት ዘመንም እንዲሁ በአንድ ዓመት መማር የነበረባቸውን ያህል ሳይማሩ ቀሩ።
በዚህም አሁን ላይ ከአቤቱታ አቅራቢው ጋር የ12ኛ ክፍል ፈተና ተፈትነው ወደ ሌላ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ ጓደኞቻቸው አንድ ዓመት ወደኋላ መቅረታቸውን እና ይህም ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ሰፈር ሰዎች በሚመጣ አስተያየት ለከፍተኛ የሥነ ልቦናዊ ጉዳት እና ተጽእኖ መዳረጋቸውን ይናገራል። አሁን ላይ እየሄዱበት ያለውም የትምህርት አሰጣጥ ሌላ አንድ ዓመትን ወደኋላ እንደሚጎትታችው ያስረዳል።
በ2015 ዓ.ም ላይ ዩኒቨርሲቲው ያወጣው የትምህርት መርሃ ግብር “ስኬጁል“ በራሱ ልክ አልነበረም። ለመዘግየታቸው ዋና ምክንያት እሱ ነው። በወቅቱ የወጣው የትምህርት መርሃ ግብር ‹‹ትክክል አይደለም›› ብለው ተማሪዎች ቅሬታ ቢያቀርቡም ሰሚ አለማግኘታቸውን ያስረዳል። አንድ የፋርማሲ ተማሪ አምስት ዓመት መማር ሲገባው ስድስት ዓመት እና ከዚያ በላይ እንዲማር እየተደረገ ነው።
አሁንም የትምህርት አሰጣጡ በመጓተቱ የተነሳ አንድ ተማሪ መመረቅ ካለበት አንድ ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆነ ጊዜ ዘግይቶ ይመረቃል። እሱንም ከዚህ በኋላ በተገቢው መንገድ የትምህርት መርሃ ግብር አውጥተው ማስተማር ከቻሉ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በስኬጁል እንደማይመራ አንዱ ማሳያ ደግሞ ተማሪዎችን ከእረፍት ለትምህርት ጥሪ የሚያደርጉበት ማስታወቂያ ነው። ለምዝገባ ቁርጥ ያለ ቀን ወስነው ተማሪዎችን አይጠሩም። ወደ ዩኒቨርሲቲው ለመድረስ ከ7 መቶ ኪሎ ሜትር እንደሚጓዝ የሚናገረው አቤቱታ አቅራቢ ተማሪ ፤ ዩኒቨርሲቲው ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ወደ ዩኒቨርሲቲ ግቡ በተባለበት ጊዜ እየመጣ መንገድ ላይ እያለ ዩኒቨርሲቲው ምክንያቱ በውል ባልታወቀ አግባብ የመግቢያ ጊዜውን አራዘመ። በዚህም ምክንያት በርካታ ቀናት አዲስ አበባ ላይ አልጋ ተከራይቶ እንዲቆይ ተገደደ። ይህም ላልተገባ ወጪ መዳረጉን ያስረዳል። በየጊዜው የመግቢያ ቀን እያሳወቁ መቀያየር ለወላይታ ዩኒቨርሲቲ አዲስ አይደለም።
ቅሬታ አቅራቢ – ሁለት
ሁለተኛው ቅሬታ አቅራቢው የፋርማሲ ተማሪ ሲሆን ተማሪዎች የሚለማመዱባቸው የላብራቶሪ እቃዎች ብዙ ጊዜ እንደማይሟሉ ይነገራል። በላብራቶሪው ኬሚካሎችም የሉም። ጋዋንም ተበዳድረን ነው የምንለብሰው <<ለምን እንደዚህ ይደረጋል?>> ብለው ሲጠይቁ በየጊዜው ከበጀት ጋር የተያያዘ ችግር እንዳጋጠማቸው ይነገሯቸዋል።
ባለፈው ዓመት ከዚህ ቀደም የነበረው ማኔጅመንት (አመራር) ተቀይሯል። አዲስ ማኔጅመንት (አመራር) ሲመጣ ለውጦች ይኖራሉ ብለው ተስፋ አድርገው እንደነበረ ፤ ነገር ግን ምንም ለውጥ እንደሌለ አሁንም ሁሉም ነገር በነበረት እየቀጠለ መሆኑን ያስረዳሉ።
የህክምና ትምህርት ‹‹ኮርስ›› ብዛት ስላለው ትምህርቱን በተባለው ጊዜ ለመጨረስ ተማሪዎች ክረምቱን ጭምር ዩኒቨርሲቲ መቆየት ነበረባቸው። በኢትዮጵያ የሚገኙ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ያለው ተሞክሮ ይህ ነው። የወላይታ ዩኒቨርሲቲ ግን ተማሪዎችን ግቢ ውስጥ እንዲቆዩ ቢያደርግም ለትምህርቱ መሟላት የነበረባቸው ግብዓቶች ባለመሟላታቸው መማር የነበረባቸው ትምህርት ማግኘት እንዳልቻሉ ያስረዳሉ።
መምህራኖቻቸው እና ‹‹ዲፓርትመንት ሄዶች ››(የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች) በሚችሉት ልክ በስኬጁሉ ለማስተማር ይሞክራሉ። ነገር ግን በመማር ማስተማሩ ሂደት እያገጠሙ ያሉ ችግሮችን ከላይ ያለው አመራር የሚገነዘብ አይመስልም።
በወላይታ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ኦቶና›› ተብሎ በሚጠራው ካምፓስ ተማሪዎች መመረቅ ካለባቸው ጊዜ አንድ ዓመት ተኩል እና ከዚያ በላይ ዘግይተዋል። የሰላም እጦት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች እንኳን ተማሪዎች በጊዜ እንዲገቡና እንዲማሩ ይደረጋል። ወላይታ ላይ ግን ምንም ዓይነት የጸጥታም ሆነ የደህንነት ስጋት ሳይኖር ወጥ የሆነ ስኬጁል በማውጣት ተማሪዎችን እያሰተማሩ አለመሆናቸውንም ያስረዳሉ።
የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ደስ እንዳለው የትምህርት መርሃ ግብር ያወጣል። አንዳንድ ጊዜ በጣም ያፋጥኑት እና ማወቅ ያለባቸውን ሳያውቁ እንዲሄዱ ይደረጋል። በሌላ ጊዜ ደግሞ በጣም ያጓቱትና ወደ ኋላ እንደሚቀሩ ይገልጻሉ።
አስተዳደሩ ለተማሪዎች የመመረቂያ ጊዜ መዘግየት ምንም ትኩረት አይሰጥም፤ በመዘግየት ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን የሚያስቡት ሁሉ አይመስሉም። ሁሉን ነገር እንደ ቀልድ ነው የሚያዩት። የተማሪዎች እዚያ መቆየት እና ዘግይቶ መመረቅ ማግኘት ያለባቸውን እውቀት እንዲያገኙ ቢያስችል መልካም ነበር። ነገር ግን ዝም ብለው ጊዜ እያቃጠሉ መሆናቸውን ይናገራሉ።
እንደ የትምህርት ክፍሉ የሚለያይ ቢሆንም ዋናው ግቢም የሚማሩ ተማሪዎች መመረቅ ከነበረባቸው ጊዜ በአንድ ሴሚስተር ብቻ ነው የሚዘገዩት። በዚህም ዋናው ግቢ ላይ ያሉ ተማሪዎች ከዚህ በፊት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሞክረው ነበር ፤ ግን የሚሰማ አካል ሊገኝ አልቻለም።
ቅሬታ አቅራቢ – ሶስት
በ2012 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲው የገቡ የጤና ተማሪዎች በ2016 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ መመረቅ ሲገባቸው አሁንም በግቢው ይገኛሉ። ይህ የሆነው በዩኒቨርሲቲው ችግር ነው። በ2013 ግቢ ከገቡ ተማሪዎች መካከል መሆኑን የሚናገረው ቅሬታ አቅራቢዋ፤ ሌላ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች 2016 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ተመርቀው ወጥተዋል። እነሱ ግን መቼ እንደሚመረቁ እንኳን እንደማያውቁ ትናገራለች።
በሁሉም ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ የጤና ተማሪዎች በክረምት እየተማሩ እያለ የወላይታ ዩኒቨርሲቲ ግን ወደ ቤተሰብ ለመሄድ የሚሆን የአንድ ቀን ማስጠንቀቂያ እንኳን ሳይነገራቸው በአንድ ቀን ከግቢ እንዲወጡ ተደርጓል። ዩኒቨርሲቲው ሰኔ 18/2016 ዓ.ም ባወጣው ማስታወቂያ ‹‹ ሰኔ 19 ጠዋት በአስቸኳይ ግቢውን ለቃችሁ ውጡ›› የሚል ነበር።
በዚህም ምክንያት ምንም ዝግጅት ያላደረጉት ተማሪዎች ሰኔ 19 ጠዋት ተገደው ከዩኒቨርሲቲው ግቢ እንዲወጡ ተደረገ። በወቅቱ ‹‹እንዴት በአንድ ቀን ውጡ እንባላለን?›› የሚል ጥያቄ አንስተው እንደነበር የሚናገረው አቤቱታ አቅራቢዋ ፤ ‹‹ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መልሰን እንጠራችኋለን›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ትናገራለች።
ይህን ተከትሎ በተለይም ከዩኒቨርሲቲው በበርካታ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቤተሰቦቻቸው የሚገኙ ተማሪዎች ለሁለት ሳምንት ወደ ቤተሰቦቻቸው ከሚሄዱ እዚያው በዩኒቨርሲቲው አካባቢ ለመቆየት በመወሰን ቤት ተከራይተው መጠበቀን መረጡ። ነገር ግን የተባለው ጊዜ ሲደርስ ቢጠይቁም ‹‹ሌላ ሁለት ሳምንት ጠብቁ›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ታስረዳለች።
ይሁን እንጂ አሁንም ከሁለት ሳምንት በኋላ ቢጠይቁም ለጉዳዩ ምላሽ የሚሰጥ አካል አለማግኘታቸውን ትናገራለች። በዚህም ከሶስት ወር በላይ ያለ ትምህርት እንዲቀመጡ መደረጋቸውን ትገልጻለች። ለጤና ተማሪ ይሄን ሁሉ ወር ያለ ትምህርት እንዲያልፍ የሚያደርግ ዩኒቨርሲቲ አለመኖሩንም ታስረዳለች።
አሁን ላይ በሌላ ዩኒቨርሲቲ ከሚማሩ አቻ ጓደኞቻችን ከአንድ ዓመትና ከዚያ በላይ ለሚሆን ጊዜ ወደኋላ መቅረታቸውን ነገር ግን አሁንም ከዚህ የከፋ ችግር እንዳያጋጥማቸው ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ጠቁማለች። ዩኒቨርሲቲው በበርካታ ውስብስብ ችግሮች የተሞላ ነው የምትለው አቤቱታ አቅራቢዋ ፤ ግቢ ውስጥ ያለው የሴቶች ማደሪያ ህንጻ አንድ ብቻ መሆኑን እና በሚኖሩበት ህንጻ ‹‹ዶርም›› ውስጥ ደግሞ ሎከር እንኳን አለመኖሩን ትገልጻለች።
በአንድ ክፍል ውስጥ ስድስት እና ሰባት ተማሪ ሆነው እንደሚኖሩ የምትገልጸው ተማሪዋ፤ ውድ የሆኑ እንደ ላፕ ቶፕ፣ ታብሌት እና የትምህርት ቁሳቁሶችን የሚያስቀምጡበት ቦታ እንደሌላቸው ታስረዳለች። በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ለማስተማር የተዘጋጀ እንደማይመስል አመላክታለች።
በግቢ ውስጥ ተማሪዎች የሚዝናኑባቸው ካፌዎች ሁለት ብቻ ናቸው። አንዱ በዩኒቨርሲቲው የሚታከሙ የውጭ ህሙማን ጭምር የሚጠቀሙበት ነው። ሌላኛው ደግሞ ጥሩ ምግብ የለውም ፤ በዚያ ላይ ገበያ ስለሚበዛ ወረፋ አለው። ለጤና ተማሪ ቆሞ የሚጠብቅበት ጊዜ አይኖረውም።
ይህን ሊረዳ የሚችለው የጤና ተማሪ ብቻ ነው። ‹‹ግቢው ሰፊ ሆኖ እያለ ተጨማሪ ምግብ ቤቶችን ከፍተው ተማሪዎች ሳይንገላቱ አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ እንዴት ማመቻቻት ይከብዳቸዋል?>> ስትል ትጠይቃለች።
ቅሬታ አቅራቢ- አራት
ዩኒቨርሲቲ ሲባል የቅንጦት ስፍራ እንዳልሆነ እናውቃለን የሚለው ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ፤ በግቢው ጂ+6 የሆነ የወንድ ተማሪዎች ማደሪያ መኖሩን ተናግሮ፤ ህንጻው መታጠቢያ ቤት የለውም ይላል። መታጠቢያ ቤቱ ላይ ያለው ውሃ ሲፈስ የህንጻው አሰራር ችግር ስላለበት ህንጻው በውሃ ይጥለቀለቃል።
ከዚህ የተነሳም ‹‹የኢንተርን›› ተማሪዎች ካሉበት ህንጻ በመሄድ እንደሚታጠቡ ያስረዳል። ይህም ሆኖ የተማሪዎችን ችግር መቅረፍ ያልቻለው አመራር በልዩ ሁኔታ ከሚማሩት ተማሪዎች ህንጻ ሄዳችሁ እንዳትታጠቡ የሚል ማስታወቂያ ተለጠፈ።
ይህን ተከትሎ ተማሪዎች በህብረት በመሆን የት ሄደን እንታጠብ? የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን እና በተማሪ ህብረት አማካኝነት ተከራክረው ፈቃድ ማግኘታቸውን ያስረዳሉ። ‹‹በአጠቃላይ አመራሮቹ የሚሰሩትን ሥራ የሚያውቁት አይመስለኝም›› ሲል ይናገራል።
በግቢው የውሃና የመብራት ችግር የለም የሚለው አቤቱታ አቅራቢው ፣ ነገር ግን ውሃው ቢኖርም ወንዶች ህንጻ ላይ ያለው ችግር መቅረፍ አለመቻላቸውን ይገልጻል።
ለተማሪዎች የሚቀርበው ምግብ በየጊዜው ጥራቱ እየቀነሰ ነው። ይሄ ሁሉ ችግር እያለ ግን የተማሪዎች ትኩረት ትምህርቱ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲያልቅላቸው መሆኑን ያስረዳል። አራት ዓመት መማር ያለበት በአራት ዓመት ውስጥ ትምህርቱን መጨረስ አለበት ፤ አምስትም ዓመት መማር ያለበት በአምስት ዓመት ትምህርቱን ተምሮ ማጠናቀቅ እንዳለበት ይገልጻል።
በኮቪድ ወቅት ማለትም የ2012 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲው የገቡ ተማሪዎች እስካሁን አልተመረቁም። በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ተማሪዎች ግን መደረግ ያለበትን ሁሉ አድርገው ለአንድ የጤና ተማሪ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ አስመርቀዋል። ወላይታ ዩኒቨርሲቲ ግን ከተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የኢንጂነሪንግ ተማሪዎችን ብቻ ነው ያስመረቀው።
ለምሳሌ በ2013ዓ.ም ላይ ወደ ዩኒቨርሲቲው የገባ አንድ የጤና ተማሪ አሁን ላይ ቢያንስ አራተኛ ዓመት ሁለተኛ ሴሚስተር ላይ መሆን ነበረበት። ነገር ግን ገና የሶስተኛ ዓመት ሁለተኛ ሴሚስተር ትምህርት እየወሰዱ መሆናቸውን ይናገራል። በዚህ ዓመት ይጨርሱ ቢባል እንኳን ማወቅ የሚገባቸውን ሳያውቁ የሚያልፉ መሆናቸውን አመላክቷል። 2014ዓ.ም ግቢ የገቡ ጤና ተማሪዎች ደግሞ ሶስተኛ ዓመትን መጨረስ ሲኖርባቸው አሁን ላይ ገና ሁለተኛ ዓመትን እየጨረሱ ነው።
‹‹አሁን ከዚህ የከፋ ችግር እንዳይገጥም ምን ማድረግ ይገባል?›› ብለው በክፍል ተወካዮቻችን አማካኝነት ከትምህርት ክፍሉ ኃላፊዎቻችን ጋር መወያየት ቢችሉም የትምህርት ክፍሉ ኃላፊዎችም ‹‹እኛ ምንም ማድረግ አንችልም›› የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ይናገራል።
ተማሪዎች ግቢ ውስጥ በቆዩ ቁጥር ተማሪው ላይ ከሚያደርሰው ጫና ባለፈ መንግሥትንም ላልተፈለገ ወጪ የሚዳርግ ነው። ይህ ደግሞ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የሚበጀተውን በጀት የሚጎዳ ነው። ነገር ግን ይሄንን ታሳቢ አድርጎ በጣም ወሳኝ ለሚባሉ ትምህርቶች ሰፋ ያለ ጊዜ፤ ተጓዳኝ (ማይነር) የሚባሉትን ደግሞ አጠር ያለ ጊዜ ሰጥቶ የትምህርት ክፍለ ጊዜውን ለማስተካከል የሚጥር አንድም አመራር አለመኖሩን ጠቁሟል።
አንድ ተማሪ አንድ ዓመት እና ከዚያ በላይ ወደኋላ ቀርቷል ሲባል የዩኒቨርሲቲው አመራሮች አያውቁም ወይስ ለተማሪዎቻቸው አይጨነቁም ወይስ ችግሩ ከነሱ አቅም በላይ ሆኖ ነው? የሚለውን ማወቅ እንደሚፈልጉ የገለጸው፤ አቤቱታ አቅራቢው እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲፈጠሩ ፕሬዚዳንቱ በዩኒቨርሲቲው እየሆነ ያለውን ታች ድረስ ወርዶ መመልከት እንደነበረበት ይናገራሉ።
ቅሬታ አቅራቢ -አምስት
በ2017 መጨረሻ ላይ መመረቅ የነበረበት። ነገር ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ 2019 አጋማሽ ላይ እንኳን መመረቁን እርግጠኛ አይደለም። ችግሩ ከቤተሰብ እና ከራሳቸው እቅድ ውጭ እያደረጋቸው መሆኑን ያስረዳል። ይህም ለከፋ ‹‹ዲፕሬሽን›› ውስጥ እንዳስገባው ይናገራል። በተመሳሳይ የትምህርት ክፍል ከእርሱ ጋር ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የነበሩ ጓደኞቹ አሁን ላይ ተመርቀው ሥራ ይዘዋል። ይሄንን የተመለከቱ ቤተሰቦቹ አፍ አውጥተው ለምንድነው የማትመረቁት? ተባረህ ወይም ሌላ ችግር ገጥሞህ ከሆነ ንገረን ብለው እንደሚያስጨንቁት ጠቁሟል። በዚህም ተመርቀው ለቤተሰቦቻችን ተስፋ እንሆናለን ብለው ቢያስብም ሃሳቡ ሃሳብ ብቻ ሆኖ መቅረቱን ይናገራል።
ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ልጆቹን እንዴት ሆኖ እንደሚያስተምር ይታወቃል። ተመርቀው እና ሥራ ተቀጥረው ቤተሰብን ማገዝ ባይችሉም እንኳን እራሳቸውን ችለው የቤተሰቦቻቸውን ጫና መቀነስ እንደነበረባቸው ጠቁመዋል። በየጊዜው ይሄ ነው በማይባል ምክንያት የትምህርት ጊዜው ስለሚራዘም መቼ እንደሚያልቅ እንደማያውቁ እና የምርቃት ጊዜያቸውን እንደሚናፍቁም
ተናግሯል።
ግቢ ውስጥ በርካታ ተማሪዎች ተስፋ ቆርጠዋል። በኛ ግቢ (የጤና ተማሪዎች ካምፓስ) ትንሹ ተማሪ ግቢ ውስጥ የሚቆይበት አራት ዓመት ነው። ትልቁ ደግሞ ‹‹ሜድስን›› ሰባት ዓመት ነው። አሁን ግቢ ውስጥ ያሉ የሜድስን ተማሪዎች ከሰባት ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፤ መቼ እንደሚመረቁ አያውቁም።
የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች የተማሪዎችን ችግር የሚረዱ ቢሆንም ጉዳዩን ለበላይ በማሳወቅ መብቶቻቸውን ማስከበር ቢገባቸውም ለበላይ አመራሮች ከማሳወቅ ይልቅ ስለችግሩ ተማሪዎችን ማስረዳትን ነው የሚመርጡት። ለጤና ተማሪ በሳምንት ሁለት ፈተናና አንድ ‹‹ፕረዘንቴሽን›› ግድ ነው። በመሆኑም ችግር ቢገጥማቸው እንኳን ቅሬታ ለማቅረብ ጊዜ እንደሌላቸው ያስረዳሉ።
አሁን ላይ አዲስ ገቢ የጤና ተማሪዎች የሚገቡት ከጤና ካምፓስ ውጭ በዋናው ግቢ ነው። ዋናው ግቢ ደግሞ የኢንጂነሪንግ እና የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች መማሪያ ነው። በመሆኑም አዲስ ገቢ ተማሪዎች ‹‹ከሲኒየር›› የጤና ተማሪዎች ማግኘት የነበረባቸውን እውቀት እና ልምድ አያገኙም።
የመጀመሪያ ዓመት የትምህርት ውጤቱ ቀንሶብኝ ነበር የሚለው አቤቱታ አቅራቢው ፤ እንዴት ማጥናት እንደነበረብን፤ እንዴት እንደምንፈተን፣ እንዴት መዘጋጀት እንደነበረብን የምንጠይቀው ‹‹ሲኒየር›› አልነበረንም። አሁንም ይሄንኑ አሰራር እያስቀጠሉ ነው። ይህም የሆነው ነባር ተማሪዎች ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተመርቀው ግቢውን ባለመልቀቃቸው ነው።
ቅሬታ አቅራቢ -ስድስት
የሰፈሩ ልጅ የሆነው እና 12ኛ ክፍልም አብሮት የተማረው ጓደኛው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኮምፒዩተር ሳይንስ እየተማረ ነው፤ ዘንድሮ ይመረቃል። እየተማረው ባለው ትምህርት ሳይመረቅ ጥሩ ገንዘብ ያገኛል። ምክንያቱም ‹‹ዌብሳይት›› ይፈጥራል፤ ሌላም ከኮምፒዩተር ጋር የተገናኙ ሥራዎችን ይሰራል። ይህ ጓደኛው 12ኛ ክፍልን እንደጨረሱ የጤና ትምህርት ለመግባት ይፈልግ ነበር። ነገር ግን ውጤቱ ሳያስገባው ቀረ። ‹‹አሁን ላይ እኔ ሥራ ልሥራ ብል የሰው ሕይወት ላይ ስለሆነ የምንሰራው ምንም ነገር የለም። ወረቀቴን ሳልይዝ ሥራ የሚቀጥረኝ የለም። ››
በትምህርት ክፍላቸው ትምህርት ተጀምሯል ተብሎ መምህር ቢመደብም ብዙ ጊዜ መምህሩ ወደ ክፍል የሚገባው ትምህርት ተጀመረ ከተባለበት ጊዜ ከወር ከሁለት ወር በኋላ ነው። ‹‹ለምን?›› ብለው ሲጠይቁም፤ ‹‹መምህራን ደሞዝ አልተለቀቀም›› የሚል መልስ እንደሚሰጧቸውም ያስረዳል።
በግቢው ጠንካራ የተማሪ ህብረት የለም የሚለው አቤቱታ አቅራቢው፤ የተማሪዎች ህብረት የተማሪዎችን ችግር አይተው ለተማሪ ከመከራከር ይልቅ ለዩኒቨርሲቲው መወገንን እንደሚመርጡ አመላክቷል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምላሽ
የዝግጅት ክፍሉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማሩ ሂደት ምን እንደሚመስል፤ ተማሪዎች ያነሷቸውን ቅሬታዎች ታውቃላችሁ? ስንል ለዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክስ ጉዳዮች ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አክበር ጭፎ ጥያቄ አቅርበን የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል።
ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራው የሚያከናውነው የትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ /ካሌንደር/ መሰረት አድርጎ ነው። ትምህርት ሚኒስቴር ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በሰጠው የትምህርት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተማሪዎቻቸውን በጊዜው ከጠሩ ዩኒቨርሲቲዎች ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው። በዚህም መሰረት ሁለተኛ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት መደበኛ ተማሪዎች ወደ ግቢ ገብተዋል። ተማሪዎች የተጠሩትም ዩኒቨርሲቲው ለመማር ማስተማሩ ሂደት አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ነው። ተማሪዎች በገቡ ማግስት ወዲያውኑ ትምህርት እንዲጀምሩ ተደርጓል።
የጤና ተማሪዎች ከትምህርት ፕሮግራሙ ጋር በተያያዘ ከአንድ ዓመት ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ትምህርት ተስተጓጉሎብናል ብለው ቅሬታ አቅርበዋል። ለዚህ የዩኒቨርሲቲው ምላሽ ምንድነው? ተብለው የተጠየቁት ዶክተር አክበር፤ የጤና ትምህርት ሲባል በርካታ የትምህርት ክፍሎች አሉትና የትኞቹ ናቸው?። በሚል ጥያቄን በጥያቄ መለሱ። ዝግጅት ክፍሉም ጥያቄውን ግልጽ ለማድረግ ቅሬታ ያነሱት ከሶስተኛ ዓመት ጀምሮ ያሉ የላብራቶሪ፤ የህክምና፤ የፋርማሲ፤ ተማሪዎች ናቸው። ለምሳሌ የሶስተኛ ዓመት ያቀረቡት ቅሬታ ‹‹በዚህ ዓመት አምስተኛ ዓመት መሆን ሲገባን እኛ ግን ያለነው ሶስተኛ ዓመት ላይ ነው።
በዚህም አንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ ጊዜ ተቃጥሎብናል›› የሚል ነው ለዚህ ምላሽዎት ምንድን ነው? ተብለው የተጠየቁት ኃላፊው፤ በዩኒቨርሲቲው የተደረገ የፕሮግራም መዛባት የለም። ባለፈው ዓመት ወደ ግቢው ስንመጣ አዲስ ነበርን። ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነው የመጣነው። ባለፈው ዓመት ጥር አካባቢ ሶስተኛ ዓመት ተማሪዎች ክረምቱን ተምረን ማለፍ አለብን ብለው ያመጡት ሃሳብ ነበር። ይሁን እንጂ ጉዳዩን በተግባር ስናጠና ተማሪዎቹ የ2013 የገቡ ተማሪዎች ናቸው። በትምህርት ፕሮግራሙ ላይ ቅሬታ ያላቸው ተማሪዎች በዚያው ዓ.ም የገቡ ተማሪዎች ናቸው። ሌሎች ተማሪዎቸ ላይ ምንም ቅሬታ የለም።
ነገር ግን እነዚህ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው የገቡት የትምህርት ዓመቱ ሊያልቅ ሲል ነው። በተጨማሪም በኮቪድ.19 ምክንያት ሴሚስተሩን ሳይጨርሱ ወጡ። ከኮቪድ ጋር ተያይዞ የተዛባው የትምህርት ሴሚስተር የሌሎች ባች ተማሪዎቻችን ጭምር ጎድቷል። ነገር ግን 2013 ዓ.ም ላይ የገቡ ተማሪዎችን የበለጠ ጎድቷል። ምክንያቱም ሰኔ መጨረሻ ላይ ገብተው ሴሚስተር ሳይጨርሱ ቶሎ ወጡ።
ፕሮግራሙ ከዚያ ጀምሮ እንደተዛባ እስካሁን መጥቷል። ስለዚህ ከኮቪድ በተያያዘ የመጣው ችግር በሌሎች ተማሪዎች ላይም ጫና አሳድሯል። የበለጠ ጫና ያሳደረው ግን በ2013 ዓ.ም የገቡ ተማሪዎች ላይ ነው። አሁን ግን በአብዛኛው እየተስተካከለ እየመጣ ነው።
ችግሩ በሚቀጥለው ጥር ወር ሙሉ በሙሉ ይስተካከላል። በተጨማሪም ሰኔ ላይ የሚስተካከል አለ፤ በዚያን ጊዜ ውስጥ ወጥ ይሆናል። ተማሪዎች ባነሱት ቅሬታ ላይ በግልጽ ተወያይተን ያለውን ሁኔታ ለተማሪዎች አስረድተን ችግሩ የመጣው ከኮቪድ ጋር በተያያዘ እንደሆነና ፕሮግራሞች ወደ ፊትና ወደ ኋላ ማለታቸውን በተግባር ተማምነን፤ መቼ የመውጫ ፈተና እንደሚፈተኑ በግልጽ አስቀምጠን አልፈናል። ምናልባት ከጤና ተማሪዎች ጋር በተያያዘ ሌላ ችግር ካለ አይተን ችግሩን እንፈታለን።
‹‹ከዚህ በፊት በነበረው የትምህርት ሥርዓት የጤና ተማሪ ሶስት ወር አርፎ አያውቅም። ውጡ ስንባልም ከገቢው የሚሰጠን ምክንያት አሳማኝና ምክንያታዊ አይደለም። ስንጠይቅም ተገቢነት ያለው ምላሽ አይሰጠንም›› ይላሉና ምላሽዎት ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ከመውጣታቸው በፊት ይህን ዓይነት ቅሬታ ማንሳታቸውን አልሰማንም፤ ከሁሉም የትምህርት ክፍሎች ጋር በጋራ ነው የምንሰራውና ከዚህ ጋር በተያያዘ እምናውቀው ቅሬታ የለም።
ከ2013 ዓ.ም ጋር የተያያዘ ከሆነ ቅሬታው ከኮቪድ ጋር በተፈጠረ መዛባት ነው። ከዚያ ውጭ የህክምና እና ሌላ ጤና ተብሎ ተከፍለው በሚማሩ ተማሪዎች ጉዳይ ለትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርበን የጤና ትምህርት በተፈጥሮው ለየት ይላልና 11 ወር የሚማሩበት ሁኔታ አለ። ትምህርት ሚኒስቴር ሰርኩላር በጻፈው ደብዳቤ መሰረት መቆየት ያለባቸው ተማሪዎች ግቢ ቆይተው ክረምቱን ሙሉ ተምረዋል። ይህ ከትምህርት ሚኒስቴር አቅጣጫ ውጭ አለመሄዳቸውን ያስረዳሉ።
የህክምና ተማሪዎችን ውጡ አንልም፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ ትምህርት የሚመራው በፕሮግራም ነው። ስለዚህ ዓመቱን ሙሉ የሚማሩበት ሁኔታ አለ። እስካሁን ድረስ እየተማሩ ያሉ አሉ። ዲፓርትመንቶች በተለየ መንገድ ትምህርት ጨርሰናል ውጡ ያሉበት ሁኔታ ካለ እናጣራለን። ነገር ግን እኔ እስከማውቀው ድረስና በአሰራር የህክምና ተማሪ ውጡ አይባልም።
የጤናና የላብራቶሪ ተማሪዎች ጊዜ ሳይሰጣቸው ውጡ እንደተባሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ነው የወጣነው ይላሉ እና በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ? የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው ዶክተር አክበር፤ ይህን ጉዳይ እናጣራለን። ዋናው ግቢ ከመቶ በላይ ተማሪዎች ሰብሰበን አቅም የሌላቸውን ዶርሚታሪ ሰጥተን እንዲቆዩ አድርገናል። ውጡ ብለን ያስወጣናቸው ተማሪዎች የሉም። ነገር ግን ግልጽ መረጃ አጣርተን ተጨማሪ መረጃ መስጠት እንችላለን።
‹‹የፋርማሲ ተማሪዎች ማየት የነበረብን የላብ ውጤቶች እያየን አይደለም፤ ላብራቶሪውም በቂ ግብዓት የለውም፤ ስንጠይቅ በጀት የለም የሚል ምላሽ እየተሰጠን ነው። ማየት ከነበረብን 12 ኬሚካሎች ሁለቱን ብቻ ነው የምናየው ስለዚህ ተመርቀን ብንወጣም ተወዳዳሪ አንሆንም›› የሚሉ ቅሬታዎች ያነሳሉ። ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ የጤና ተማሪዎች የሚማሩት ‹‹ኦቶና›› የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ባለው አቅም አስፈላጊው የላብራቶሪ ሙከራ እንዲያዩ እያደረገ ነው። ግብዓት ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ነው፤ እናሟላለንም። አንዳንድ ጊዜ ፤ ምናልባትም አልፎ አልፎ መብራት ሊጠፋ ይችላልና ሌላ ቦታ ሄደው የሚሰሩበት ሁኔታ እናመቻቻለን። ነገር ግን ያን ያህል ችግር አለ ብለን መናገር አንችልም። መማሪያው ህክምና የሚሰጥበት ሆስፒታል ነው። ታካሚ ሲበዛ በእቅዳችን መሰረት ላይሄድ ይችላል። ነገር ግን ያን ያክል የጎላ ችግር አይደለም።
ለህክምና ተማሪዎች ያላችሁ ትኩረት ምን ያህል ነው? ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ዶክተር አክበር ሲመልሱ፤ ለጤና ተማሪዎች ከፍተኛ ትኩረት እንሰጣለን። ምክንያቱም ጤና ዘርፉ ላይ የሚሰራው በሰው ሕይወት ላይ ነው። ዩኒቨርሲቲው ለዚህ ትልቅ ቦታ አለው። በጤናው ዘረፍ እያከናወነው ያለው ሥራ ለአካባቢው ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው።
ትልልቅ ባለሙያዎች ያሉበት ዩኒቨርሲቲ ነው። የሰው ፍላጎት ሰፊ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ሁሉንም በአንድ ጊዜ ባናሟላም ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ቅድሚያ በመስጠት ዩኒቨርሲቲው ባለው አቅም ልክ እየሰራ ነው። ስለሆም ለጤና ተማሪዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን አሟልቶ ለማስተማር ጥረት እየተደረገ ነው።
በዚህ ዓመት ለህክምና ትምህርት ምን ያህል በጀት ተመድቦ ምን ያህል ወጪ ተደርጎ የተገዛ ግብዓት አለ? ካለ ቢጠቅሱ? ተብለው የተጠየቁት ኃላፊው በጀት ተመድቦ በሂደት ላይ ነው። ይህ ለህክምና ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በዩኒቨርሲቲው 62 ዓይነት የትምህርት ዓይነቶች አሉ። ለሁሉም እንደ የበጀቱ ግብዓት ለማሟላት ግዥ ሂደት ላይ ነው። የዩኒቨርሲቲው የማስተማሪያ ሆስፒታል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚያስተናግድ ነው። ተማሪዎች ቅሬታ እንዲያቀርቡ የሚያስችል ከባድ ጉዳይ ግን የለም።
ሆስፒታሉ ጠባብ ነው። የማስፋፊያ ሆስፒታል ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ ነው። ሁሉም ተማሪዎች የሚፈልጉት ተሟልቶ ቢማሩ መልካም ነው። ነገር ግን ባለን አቅም እያስተማርን ነው። ከ90 በመቶ በላይ የህክምና ተማሪዎች የመውጫ ፈተናው በማለፍ ወደ ሥራው ዓለም ተቀላቅለዋል። ተምረው የሚመረቁበት ጊዜም ከሌላ ዩኒቨርሲቲ የተለየ አይደለም። በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች የተሻለ ትምህርትና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ዶክተር አክበር ገልጸዋል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ወኪል ወልዴ በበኩላቸው፤ ከአንድ ዓመት በላይ የመመረቂያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ተማሪዎች አለመኖራቸውን ገልጸው፤ ባሳለፍነው ዓመት ክረምት ላይ መመረቅ የነበረባቸው ተማሪዎች የመመረቂያ ጊዜያቸው ወደ ጥር መሸጋገሩን ተናግረዋል።
ጊዜውም የተገፋበት ምክንያት በዩኒቨርሲቲው የሚፈተኑ የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች በመኖራቸው እና በሰላም ሚኒስቴር የሚሰለጥኑ ሰልጣኞች በግቢው ውስጥ ስለነበሩ ነው። በ2012 ዓ.ም የ12ተኛ ክፍል ተፈታኝ መሆን የነበረባቸው ተማሪዎች በኮቪድ ምክንያት አንድ ዓመት ወደኋላ ቀርተዋል። ይሄንን ለማካካስ እንደ ሀገር አግባብነት ባለው አካሄድ እየሄድን ነው። ከትምህርት ሚኒስቴር በመጣው መርሃ ግብር መሰረት የጤና ተማሪ ከሆነ በዓመት ውስጥ 10 ወራት የህክምና ተማሪዎች ደግሞ 11 ወራት ነው የሚማሩት።
የፋርማሲ ተማሪዎች በላብራቶሪ ኬሚካሎች አለመሟላት የተግባር ትምህርት በተገቢው መንገድ መከታተል አልቻልንም ይላሉ ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።
‹‹ለፋርማሲ ተማሪዎች የተገዙ ኬሚካሎችን ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን አንዳንድ ያልተሟሉ ሊኖሩ ይችላሉ። በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲገዙ ጥያቄ አቅርበናል። አንዳንዶቹ ገበያ ላይ ባለመገኘታቸው ሌሎቹ ደግሞ በበጀት መጓደል ያልተሟሉ አሉ። ይህ ሲባል ግን ተግባር ትምህርትን ለመከታትል የሚዳግቱ ግን አይደሉም። ››
በተጨማሪም 170 የሚሆኑ የህክምና ተማሪዎችም በዋናው ግቢ መኖራቸውን ገልጸው፤ ወደ ኮሌጁ መተው የሚማሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የዶርሚተሪ ማስተካከል ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ከመጸዳጃ ቤት እና ከመታጠቢያ ቤት ጋር ተያይዞም በኮሌጁ ውስጥ ሶስት የተማሪ ማደሪያ ህንጻዎች አሉ። ከሶስቱ አንዱ ህንጻ የውሃ ፍሳሽ ችግር አለበት ። ይሄንን ከህንጻ ተቋራጮች ጋር ተነጋግረን በከፊል ዘግተነዋል። የውሃ ፓንፑም ተበላሽቶ ነበር። አሁን ግን ፓንፑን አስተካክለን ውሃ ወደ ህንጻው እንዲወጣ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
የተበላሹ ቁም ሳጥኖችን ‹‹ሎከሮችን›› ለማስጠገን እና የአዳዲስ ግዥ ለመፈጸም ከማኔጅመንት ጋር ንግግር ተደርጓል። የግዥ ሂደቱ ግን በዚህ ቀን ተጠናቆ ለተማሪ ይደርሳል ማለት አይቻልም። ከጋዋን ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት በሂደት ላይ መሆናቸውን እና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለተማሪዎች እንደሚደርስ ገልጸዋል።
በመልካም አስተዳደርና ምርመራ ቡድን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም