ሩሲያ የጦር ምርኮኞችን ገድላለች መባሏን ዩክሬን አወገዘች

ሩሲያ የማረከቻቸውን ዘጠኝ የዩክሬን ወታደሮችን ገድላለች መባሏን የዩክሬን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት አወገዘ። ድርጅቱ የሩሲያ ኃይሎች በድንበር አካባቢ በሚገኝው ከርስክ ክልል የማረኳቸው የዩክሬን ወታደሮች ላይ ግድያ ፈጽሟል ብሏል።

የድርጅቱ ኃላፊ ዲሚትሮ ሉቢኔትስ ሩሲያ “ሁሉንም የጦርነት ሕጎች እና አሠራሮች” ጥሳለች ሲሉ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ለቀይ መስቀል ቅሬታቸውን መጻፋቸውን ተናግረዋል።

ኃላፊውን ይህንን ያሉት የዩክሬን የጦርነት ውሎዎችን የሚተነትነው ድረገጽ፣ ዲፕስቴት የሰው አልባ አውሮፕላን ኦፕሬተሮች ናቸው ያላቸውን ወታደሮች አስክሬን በድሮን በተቀረጸ ቪዲዮ ማውጣቱን ተከትሎ ነው። የሩሲያ ባለሥልጣናት ስለቀረበባቸው ክስ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

ዩክሬን ባልተጠበቀ ሁኔታ የሩሲያን ድንበር ዘልቃ በመግባት ከፈጸመችው ወረራ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን በድንበር አካባቢ እንዳሰማራች ይታመናል።

በዲፕስቴት ድረ ገጽ በታተሙ ምስሎች ላይ የውስጥ ሱሪ ብቻ ያደረጉት የዩክሬን ወታደሮች አስከሬኖች በሆዳቸው በኩል ተንጋለው ይታያሉ። አስከሬናቸው የታየበት ስፍራ የእርሻ ቦታ ነው የተባለ ሲሆን ቢቢሲ እነዚህን ምስሎች በተናጠል ማረጋገጥ አልቻለም። ድረገጹ የገለፀው እነዚህ የዩክሬን ወታደሮች በሩሲያ ኃይሎች መገደላቸውን ነው።

“እነዚህ ተግባራት ሳይቀጡ መታለፍ የለባቸውም። ጠላት ሙሉ ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲህ አይነት ወንጀሎችን ችላ ሊል አይገባም” ሲሉ ዲሚትሮ በቴሌግራም ገጻቸው አስፍረዋል።

ዩክሬን በጄኔቫ ስምምነት መሠረት የጦር ወንጀል የሆነውን ምርኮኞችን በመግደል ሩሲያን በተደጋጋሚ ስትወነጅላት ይሰማል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት የዩክሬን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሩሲያ ኃይል 93 የዩክሬን የጦር ምርኮኞችን ገድሏል የሚል ሪፖርት አቅርቦ ነበር።

በምሥራቃዊ ዶኔትስክ ክልል በተፈጸመው የ16 የጦር ምርኮኞች ግድያ ላይ ምርመራ መክፈቱን አክሎ ገልጿል። ሩሲያ ወታደሮቿ በዩክሬን ጦርነት የጦር ወንጀል ፈጽመዋል መባሏን አትቀበልም ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም

Recommended For You