ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የዓለም ሀገራት በሮቦቲክ ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ ናቸው:: በዚህ የሮቦቲክ ቴክኖሎጂ ላይ በርካታ ተግባሮች እየተከናወኑ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሮቦቲክ ኦሊምፒያድ ውድድር ይካሄዳል፤ ይህ ውድድር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2004 የተጀመረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ጨምሮ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት በውድድር ሲሳተፉ አይስተዋልም:: ዘንድሮ ግን ኢትዮጵያ ጨምሮ ሦስት የአፍሪካ ሀገራት የመሳተፍ እድሉን አግኝተዋል::
በዚህ ውድድር ለመሳተፍ ይቻል ዘንድ በሀገሪቱ በሚንቀሳቀሱና ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ፣ አርትና ሂሳብ ላይ አተኩረው በሚሰሩት ስቲም ማዕከላት አማካይነት በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል:: ባለፈው ሳምንትም በዓለም አቀፍ ውድድር ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፈውን የሮቦቲክ የፈጠራ ውጤት ቡድን ለመለየት የሚያስችል የውድድር መርሃ ግብር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተካሄዷል::
ዶክተር ስሜነው ቀስቅስ የስቲም ፓውር ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ናቸው:: እሳቸው እንደሚሉት፤ ስቲም ፓውር በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተዘጋጀ ነው:: በውድድሩ ለሚሳተፉ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በሚገኙ 40 የስቲም ፓውር ማዕከላት ተማሪዎች ላለፉት ሁለት ወራት ስልጠናዎች ወስደዋል፤ በዚህም ለዓለም አቀፉ ሮቦት ኦሎምፒያድ የሚመረጠው አሸናፊ ተለይቷል::
ከ600 በላይ የሚሆኑ ከሁለተኛ ደረጃና ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ተማሪዎች በማዕከላቱ ሲሰለጥኑ የቆዩ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ የሰሯቸውን ሮቦቶች በእዚህ መድረክ አቅርበዋል:: መድረኩ ሮቦቶቹ የሰውን ፣ የአካባቢን እና የማህበረሰብን ችግር የመፍታት አቅማቸውን መነሻ በማድረግ ተገምግመው በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጡ ዳኞች አማካኝነት ተገምግመው በኅዳር ወር በቱርክ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክለው ተሳታፊ ተለይቶበታል::
በፕሮጀክቶቹ ሁለት ወይም ሦስት እና ከዚያ በላይ ተማሪዎች ተሳትፈዋል:: ውድድሩ ከተለያዩ ተቋማት 37 የሚሆኑ የሮቦቲክስ ቴክኖሎጂዎች ቀርበውበታል:: ስልጠናው በ40 ማዕከላት የተሰጠ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሁሉም ውድድሩ ላይ መሳተፍ አልቻሉም:: እነዚህ 37 ፕሮጀክቶች ከአዲስ አበባና ከሁሉም ክልሎች የመጡ ናቸው::
ዶክተር ስሜነው እንዳብራሩት፤ ስቲም ፓውር በኢትዮጵያ 65 ማዕከላት አሉት፤ በእነዚህ ማዕከላት በሮቦቲክስ፣ በኤሌክትሮኒክስ፣ በኮምፒዩተር ሳይንስ፣ በሌሎችም መሰረታዊ ሳይንስ በሚባሉት በሂሳብ፣ በፊዚክስና በሌሎችም ዘርፎች ሰልጠናዎች ይሰጣሉ:: ሰልጠናውን ያገኙ ተማሪዎችም በሚቀጥለው ወር በሀገር አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘጠነኛ ጊዜ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የሳይንስና ኢንጂነሪንግ መድረክ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ:: የዘንድሮ ፕሮግራም ቀደም ካሉት ስምንት ፕሮግራሞች ለየት ባለ መልኩ ሮቦቲክስ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው::
ከቀረቡት ፕሮጀክቶች ያሸነፈው አንድ ፕሮጀክት ብቻ ኢትዮጵያን ወክሎ ቱርክ በሚካሄደው ውድድር ላይ ይሳተፋል የሚሉት ዶክተር ስሜነው፤ ዓለም አቀፉ የሮቦት ኦሎምፒክ በውድድሩ ላይ እንዲሳተፉ እድሉን ከሰጣቸው አራት የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነች ይገልጻሉ::
‹‹ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር የምትሳተፈው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፤ እንድትመረጥ ካደረጓት ምክንያቶች መካከል እንደ ሀገር ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ትምህርት ዙሪያ ስቲም ፓውር ባከናወነው ተግባር ነው:: ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በእነዚህ መስኮች መሥራት ከጀመረ 15 ዓመታትን አስቆጥሯል:: በእ.ኤ.አ 2020 ጀምሮ ለሌሎች ሀገራት የእኛ ሀገር ተሞክሮ ማጋራት ጀምረናል:: ደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳ የመሳሰሉ 33 የአፍሪካ ሀገራት አድርሰናል:: ስቲም ፓውር ሮቦቲክስ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት ከጀመረ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል:: የሮቦቲክስ ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ለማድረስ ግን እድሉ አልነበረም:: ይህም የሆነበት አቅም ሳይኖር ቀርቶ ሳይሆን የፋይናንስና የሎጂስቲክ የመሳሳሉ ችግሮች ስለነበሩ ነው:: አሁን ከዓለም አቀፍ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ ስለተደረገ ኢትዮጵያን ወክሎ በውድድሩ ላይ መሳተፍ ተችሏል›› ይላሉ ::
እሳቸው እንደሚሉት፤ እያንዳንዱ ስቲም ማዕከል የሰልጠናቸውን ተማሪዎች በተናጠልና በቡድን በማድረግ በሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ የተለያየ የአካባቢዎች ችግሮችን መፍታት የሚችሉ ፕሮጀክቶችን እንዲሰሩ አቅጣጫ ተሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል:: የመመዘኛ መስፈርቱን አሟልተው ለመጨረሻው የደረሱት ፕሮጀክቶች እያንዳንዳቸው የሦስት ደቂቃ ቪዲዮ ሰርተው ለዳኞች እንዲልኩ ተደርጓል:: ከተላኩት ቪዲዮች መካከል ለዓለም መድረክ ሊመጥኑ የሚችሉት ፕሮጀክቶች ተመርጠው ለውድድር ቀርበዋል::
ከተሰሩት ሮቦቶች አንዳንዶቹ በግብርና ዘርፍ ሌሎቹ ደግሞ በጤና ዘርፍ እንዲሁም ደንገተኛ አደጋ ሲከሰት ሰው የማይደርስባቸው ቦታዎች ድረስ ደርሰው ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ናቸው:: እነዚህ ደግሞ የዕለት ተዕለት ኑሮአችን ላይ የራሳቸው ሚና አላቸው:: ከዚህ ባለፈ በቀጣይ በሰው ሠራሽ አስተውሎትና ሌሎች የቴክኖሎጂ ግኝቶች ሥራ መሠረት ይሆናሉ:: በሌላ በኩልም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው የ5ሚሊዮን ኮደሮች ስልጠናም አንዱ መሠረት ሊሆን ይችላል::
ለተማሪዎቹ የተሰጠው ሰልጠና ከስልጠናም አልፎ መተግበር ላይ የደረሰ እንደመሆኑ በዕለት ተዕለት ሕይወታችንን ላይ የራሱ ዐሻራ ይኖረዋል ያሉት ዶክተር ስሜነው፣ በቀጣይም በትክክል የአካባቢን ችግር በተለያየ ዘርፍ የሚፈታና የሚተገበር ከሆነ በብዛት ተመርቶ ወደ ገበያ እንዲገባና ወደ ሀብት ፈጠራ እንዲሄድ ለማድረግ ታቅዷል::
ከእነዚህ 37 ፕሮጀክቶች ውስጥ አሸናፊው ኢትዮጵያን ወክሎ ወደ ውጭ ሀገር ይሄድ እንጂ ሁሉም አሸናፊዎች ናቸው ያሉት ዶክተር ስሜነው ፤ ‹‹ስቲም ፓውር ፍብሪኬሽን ላብራቶሪና የተሟሉ ማሽኖች ያሉት በመሆኑ በቴክኒክና በፋይናንስ ድጋፍ ተደርጎላቸው ለገበያ እስኪቀርቡ ድረስ ክትትልና ድጋፍ ይደርግላቸዋል›› ሲሉ ገልጸዋል::
በውድድሩ ተማሪ በረከት አሰፋና ጓደኞቹ ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል ‹‹አዳብቴብል ሮቦት›› የተሰኘ የፈጠራ ሥራ ይዘው ቀርበዋል:: ሮቦቱ በተለያዩ ዘርፍ በግብርና ፣ጤና ፣ በኢንዱስትሪ የተለያዩ ሥራዎች መሥራት የሚያግዝ እንደሆነም ተናግረዋል:: እነ ተማሪ በረከት ማዕከሉ ከተቀላቀሉ ሁለት ዓመታት እንደሆናቸው ተማሪ በረከት ይናገራል፤ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የፈጠራ ክህሎትና አቅም ያላቸው ተማሪዎችን አሰባሰቦ ለአንድ ዓመት ያህል ስልጠናዎች (በሀርድዌር፣ ሶፍትዌር፣ የተለያዩ የሮቦቲክስ እና ሲሰተሞችን በተመለከተ) መውሰዳቸውን ይናገራል::
እነ ተማሪ በረከት ‹‹አዳብቴብል›› የተሰኘውን ሮቦት ለአምስት ሆነው ሰርተው ነው ለውድድር ያቀረቡት:: ሮቦቱን ለመሥራት ያነሳሳቸው እንደ አፍሪካ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የሚደረገው አስተዋጽኦ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ነው:: ይህን አስተዋጽኦ ሊጨመሩ የሚችሉ ነገሮች መኖር እንዳለባቸው በማመን ወደዚህ ሮቦት መሥራት ገብተዋል::
ተማሪ በረከት እንደሚለው፤ ሮቦቷ ከወዳደቁ ቁሶች የተሰራች ናት:: 3ዲ ዲዛይን በመጠቀም ለሮቦቷ የሚያስፈልጉ ቁሶችም እዚሁ ነው የተሰሩት:: በአጠቃላይ ሮቦቷ የተሰራባቸው ቁሳቁስ በሀገር ውስጥ በቀላሉ የሚገኙ እንደመሆናቸው መጠን ዋጋቸውም በጣም ዝቅተኛ ነው:: ሮቦቷ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ስላለት በራሷ ውሳኔዎች ዋና ዋና ሥራዎችን ትሰራለች፤ ኃይል ቆጣቢም ናት:: ከሰባት በላይ በሚሆኑ ዘርፎች ላይ አገልግሎት መስጠት የምትችልና የተለያዩ ሮቦቶች ሊሰሩ የሚችሉትን በአንድ ላይ አድርጋ መሥራት ትችላለች::
‹‹ሮቦቷ ያለ ማቋረጥ ዓመቱን ሙሉ መሥራት ትችላለች›› የሚለው ተማሪ በረከት፤ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላትም ይገልጻል:: አንደኛ በኢንዱስትሪው ላይ ያለውን የሰው ኃይል እጥረት ለመሙላት ትረዳለች:: ለሥራው የሚያስፈልገውን የኃይል መጠንም በጣም ትቀንሳለች:: ሁለተኛ በራሷ ኃይል ቻርጅ እያደረገች ተመልሳ ሥራዋን መቀጠል ትችላለች:: በሦስተኛነት በኢንዱስትሪዎች የሚሰጧትን ማንኛቸውንም ዓይነት ሥራዎችም መከናወን ትችላለች::
ተማሪ በረከት ሃሳብ ብዙ ነገሮች ለማከናወን የምታስችለው ሮቦት ተከታታይ ማሻሻያ እንደሚደረግባት ተናግሯል:: ይህ ሲሆን ሮቦቷ በኢትዮጵያ ሆነ በአፍሪካ ደረጃ በማኑፋክቸሪንግ ወይም በግብርና ዘርፍ የተለያዩ አስተዋጽኦ እንድታበረከት ማድረግ እንደሚቻል ጠቁሟል:: ሮቦቷ የተሰራችበትን መንገድ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ክፍት በማድረግም ሮቦቷን በተለያዩ መንገዶች እያሻሻሉ እንዲጠቀሙ ለማድረግ መታሰቡንም ተናግሯል:: ይቺኛዋን ሮቦት ከኢንቪስትሮች ጋር በመነጋገር ሊጨመሩ የሚችሉ አዳዲስ ነገሮች በመጨመር ለተለያዩ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ተግባራዊ እንድትሆን አቅደው እንደሚሰሩም ይገልጻል::
ሌላኛው የውድድሩ ተሳታፊ እነ ተማሪ መሀናየም ተሻገር እና ጓደኞቿ ናቸው፤ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል የመጡ ናቸው:: እነሱም የሚወዳደሩበትን ፕሮጀክት ይዘው ቀርበዋል:: ማዕከሉን ከሁለት ዓመት በፊት የተቀላቀሉት እነ ተማሪ መሀናየም፣ ማዕከሉን ከመቀላቀላቸው በፊት ያላቸው ውስን እውቀት ነበር፤ ይህንንም በስልጠና በማሳደግ የሮቦት ቴክኖሎጂ መሥራት ችለዋል::
ለአካባቢና ለአጠቃቀም ምቹ የሆነች፣ ቆሻሻ የምትሰበሰብና የምታሰወግድ ሮቦት ሰርተው ነው ለውድድሩ የቀረቡት:: የፈጠራ ሥራውን ለመሥራት ያነሳሳቸው ቆሻሻ የሚሰበሰብበትና የሚወገድበት ሂደት ለማዘመን ማሰብ ነው:: አሁን ባለው የሀገሪቱ አሰራር ቆሻሻን ለማንሳት ጥቅም ላይ የሚውለው የሰው ጉልበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን የኢትዮጵያ ችግር ብቻ ያልሆነና ዓለም አቀፍ የሆነን ችግር ለመፍታት የሚችል ሮቦት መሥራታቸውን ይገልጻሉ::
የእነ ተማሪ መሀናየም ቡድን ሦስት አባላትን ያቀፈ ነው:: ሮቦቱን ለመሥራት ሶፍትዌር እና ሀርድ ዌር ቴክኖሎጂዎችን መሥራታቸውን ይናገራሉ:: ከሶፍትዌር መካከል የራሳቸው ዌብ ሳይት እና አንድሮይድ መተግበሪያ ሰርተዋል:: ሮቦቷን እንደ አስፈላጊነቱ በስልክ ማዘዝ የሚያስችል ኤም አይቲ የተሰኘ መተግበሪያም እንዲሁ ሰርተዋል:: በሀርድ ዌር በኩልም ብዙ ቁሳቁስ በመጠቀም ነው ሮቦቷን የሰሩት:: አሁን ሮቦቷ በሰው ሳይሆን ራሷን በራሷ መመራት የምትችል መሆኗንም ተማሪ መሀናየም ትገልጻለች::
ተማሪ መሀናየም እንደምትለው፤ ሮቦቷ በባትሪ የምትሰራ ሲሆን፤ ወደፊት ግን ሶላር ኢነርጂን መጠቀም እንድትችል ለማድረግ ታቅዷል:: ማሻሻል እንድትችል ተደርጋ ዲዛይን የተደረገች ናት:: አሁን በፕሮቶታይፕ ደረጃ ትሰራ እንጂ ወደፊት ድጋፍ ማግኘት ከተቻለ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ተግባራዊ መሆን እንድትችል ተደርጋ መሥራት ትችላለች::
ቆሻሻዎች የምትሰበስብ ብቻ አይደለችም፤ የተሰበሰበውን ቆሻሻ በየዓይነቱ በመለየት ማስቀመጥ ትችላለች:: ይቺ ሮቦት ተግባር ላይ ስትውል ቆሻሻ የመሰብሰቡን ሥራ ሙሉ በሙሉ በራሷ ያለ ምንም የሰው ኃይል ማከናወን ትችላለች:: ለሠራተኞች ስጋት ልትሆን ብትችልም፣ ለእዚህም መፍትሔ ይዛ መጥታለች:: ፕሮጀክቱ ለእነዚህ ሰዎች ስልጠና በመስጠት ሁለት ዓይነት የሥራ ዘርፎች አዘጋጅቶላቸዋል:: አንደኛው ሮቦቲክ ዘርፍ ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የሚወገዱ ቆሻሻዎችን እንደገና ጥቅም ላይ በማዋል ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ነው::
ተማሪ ሀናንኤል ማስረሻ እና ጓደኞቿ ከቢሾፍቱ ፎቃ ስቲም ማዕከል በውድድሩ ላይ የተሳተፉ ናቸው:: በውድድሩም አግሪ ቴክ ሮቦት የተሰኘ የአፈር ጤንነት የሚመረምር የሮቦት ቴክኖሎጂ ይዘው ቀርበዋል:: ተማሪ ሀናንኤል እንደምትለው፤ በማዕከሉ ለሦስት ወራት ስልጠና ወስደዋል:: እነሱን ይህን ለመሥራት ያነሳሳቸው በአካባቢያቸው ያለውን ችግር በመመልከት በተለይ ግብርና ዘርፍ ላይ አተኩረው ለመሥራት በመፈለጋቸው ነው:: ለእጽዋት የተለያዩ የኢንዱስትሪ ውጤት የሆኑ ማዳበሪያዎችን ከመጠቀም ይልቅ አፈርን በመንከባከብ ተፈጥሯዊ የሆኑ እንደ ፍግ የመሳሳሉ ነገሮችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነት ለመጨመር በማሰብ ነው::
ሮቦቷ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላት ሲሆን፣ የአፈር ጤንነት በመለካት ማረጋገጥ ትችላለች:: አፈሩ ጤናማ ሆኖ ከተገኘ በነበረበት እንዲቀጥል ታደርጋለች:: አፈሩ ጤናማ ካልሆነ ግን በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገባቸው ተግባራትን በመዘርዘር ታመለክታለች:: የአፈሩን እርጥበት በመለካትም እርጥበቱ ከ50 በመቶ በታች ከሆነ መተግበሪያ ላይ እንዲታይ ታደርጋለች:: መተግበሪያው ሰው ሠራሽ አስተውሎት የተገጠመለት ስለሆነ ሊወሰድ የሚገባውን ርምጃ ወዲያውኑ በማሳወቅ ምላሽ እንዲሰጥ እንደምታደርግ ትገልጻለች::
ይቺ ሮቦት በፕሮቶታይፕ ደረጃ ስለተሰራች የምትሰራው በባትሪ ነው፤ በቀጣይ ሶላር ኢነርጂን መጠቀም እንድትችል ይደረጋል የምትለው ተማሪ ሀናንኤል፤ ሶላር ኢነርጂን በመጠቀም አካባቢን በመንከባከብ፣ የአየርና የአፈር ብክለት እንዳይኖር በማድረግ የሰው ልጆች ጤና እንዲጠብቅ ለማድረግ ታስችላለች ትላለች:: በቀጣይ የአፈር ጤንነት ከመጠበቅ ባለፈ የሙቀት መጠን መለካትና ውሃ ማጠጣት እንድትችልና በመስኖ ላይ እንድትሰራ ተደርጎ እንደምትሻሻል ትናገራለች።
በውድድሩ መጨረሻም ከተለያዩ ስቲም ማዕከላት የተወጣጡ 37 ፕሮጀክቶች መካከል በኮተቤ ስቲም ማዕከል አማካኝነት ለውድድር የቀረበው ‹‹አዳብቴብል ሮቦት›› አንደኛ በመውጣቱ በዓለም አቀፍ መድረኩ ኢትዮጵያን ወክሎ እንዲሳተፍ ተመርጧል::
ዓለም አቀፉ የሮቦቲክ ሮቦት ኦሎምፒያድ ውድድር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2004 የተጀመረ መሆኑን መረጃዎች ጠቁመዋል:: የዘንድሮው /የ2024/ ውድድር እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከኅዳር 28 እስከ 30 በቱርክ ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ ከ80 ሀገራት በላይ እንደሚሳተፉ መረጃዎች ያመላክታሉ::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም