ከኖቤል ሽልማቶች ጀርባ ያለው አልፍሬድ ኖቤል

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቂያ ላይ አሜሪካ በጃፓኖቹ ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ከተሞች ላይ ከፈጸመችው የአውቶሚክ ቦምብ ጥቃት በተረፉት ሰዎች የተቋቋመው ኒሆን ሂዳንኪዮ የተባለው ቡድን የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።

በአውሮፓውያኑ 1945 ከተፈጸመው አሰቃቂው ጥቃት 10 ዓመታት በኋላ የተመሠረተው ይህ ቡድን የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች ከዓለም እንዲወገዱ በሚያደርገው ጥረት ነው በኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ የሰላም ሽልማት አሸናፊ የሆነው። በዓለም እጅግ የተከበረው የኖቤል ሽልማት በተለያዩ መስኮች በየዓመቱ በሥራቸው ለተመረጡ ግለሰቦች እና ቡድኖች የሚሰጥ ሲሆን፣ የኖቤል የሰላም ሽልማትም የዚህ አካል ነው።

ለዚህ ሽልማት መጀመር ምክንያት የሆነው ስዊድናዊው የንግድ ባለቤት ኢንጂነር አልፍሬድ ኖቤል ነው። ግለሰቡ ሀብቱን ለዚሁ ሽልማት እንዲሆን አበርክቷል። ግለሰቡ ዝና እና ሐብት ያገኘው ድማሚት የሚባለውን ከባድ ፈንጂ በመፍጠር ነው።

በዚህም ኖቤል የግዙፍ ጦር መሣሪያ ማምረቻ ድርጅት ባለቤት ቢሆንም፣ በመጨረሻም ገንዘቡ ለዓለም ሰላም አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች በሽልማት እንዲሰጥ ወስኗል። እአአ በ1833 በስዊዲን መዲና ስቶክሆልም ውስጥ የተወለደው አልፍሬድ ኖቤል፣ የኢንጂነር ኢማኑኤል ኖቤል እና የአንድሪቴ አህልሴል ልጅ ነው።

አባቱ ኢማኑኤል የፈጠራ ባለቤትነት መብት ያገኘባቸው በርካታ ፈጠራዎች አሉት። አንደኛው ፈጠራው የወታደሮች ቦርሳ ነው። ቦርሳው ውሃ ውስጥ እንደመንሳፈፊያ እና በድካም ጊዜ ደግሞ እንደትራስ ሆኖ ያገለግላል። ነገር ግን ሥራው ሳይሰምርለት ቀርቶ በ 1833 ለኪሳራ በመዳረጉ ከአራት ዓመታት በኋላ አበዳሪዎቹን ሽሽት ከስዊድን ወደ ሩሲያዋ ሴንት ፒተርስበርግ ኮበለለ።

እናቱ አንድሪቴ ቤተሰቡን ለመደገፍ በሚል አምስት ዓመታትን ስቶክሆልም በሚገኝ ግሮሰሪ ውስጥ ለመሥራት ተገደደች። አማኑኤል ኖቤል ሩሲያ ውስጥ መሥራት ጀመረ። ለሩሲያ ጦር መሣሪያ ለማቅረብ በሴንት ፒተርስበርግ ሱቅ ከፈተ። የሩሲያ ባሕር ኃይልም የሚያዘጋጀውን የባሕር ውስጥ ቦምቦቹን እንዲጠቀም አሳምኗል። ቦምቦቹ እአአ ከ1853 እስከ 1856 በተደረገው የክሬሚያ ጦርነት ሴንት ፒተርስበርግን ከብሪታንያ የጦር መርከቦች ለመከላከል ጥቅም ላይ ውለው ነበር።

በዚህ ጊዜ ንግዱ ትርፋማ ሆነለት። እአአ በ1842 ደግሞ የተቀረውን ቤተሰቡን ወደ ሩሲያ ወሰደ። አልፍሬድ እና ወንድሞቹ ሳይንስ እና የቋንቋ ትምህርቶችን በግል አስተማሪዎች ተከታትለዋል። አልፍሬድ የኬሚስትሪ ትምህርቱን እንዲቀጥል በ1850 ወደ ፓሪስ ተላከ። ፓሪስ እያለም ናይትሮግሊሰሪንን የፈጠረውን ጣሊያናዊ ሳይንቲስት አስካኒዮ ሶብሬሮን ተዋወቀ።

ሶብሬሮ ያዘጋጀው ንጥረ ነገር በጣም የሚፈነዳ ፈሳሽ ነበር። ከባሩድ ብዙ እጥፍ የሚበልጥ ነበር። ለሙቀት ወይም ለግፊት ለውጦች ከተጋለጠ ይፈነዳል። ደህንነቱን መጠበቅ ከተቻለ በጣም ትርፋማ ሊሆን እንደሚችል አልፍሬድ ኖቤል አሰበ።

ከክሬሚያ ጦርነት ማብቃት በኋላ በሩሲያ የነበረው ንግድ ሥራው የተቀዛቀዘበት ኢማኑኤል ኖቤል እአአ በ1863 በድጋሚ ከሰረ። ከዚያም ወደ ስቶክሆልም ተመልሶ ከልጁ ከአልፍሬድ ጋር በመሆን ናይትሮግሊሰሪን ላይ ሙከራዎችን ማድረግ ጀመሩ። እአአ በ1864 ኬሚካሉን የተከመቸበት ክፍል ፈንድቶ የአልፍሬድ ወንድም የሆነውን ኤሚልን ጨምሮ ብዙ ሰዎችን ገደለ።

የስቶክሆልም ባለሥልጣናት በከተማው ወሰን ውስጥ የሚደረገውን የንጥረ ነገሩን ሙከራዎች ከለከሉ። አባት እና ልጅ ወርክሾፖቸውን ከስቶክሆልም ውጪ ወደምትገኘው ቪንተርቪከን አዛወሩ። እአአ በ1866 አልፍሬድ ኖቤል ናይትሮግሊሰሪንን ከአሸዋ ጋር በማዋሃድ በቀላሉ እንዳይፈነዳ ማድረግ ቻለ።

ይህም ሊጥ ስለሚመሰል በተለያየ መያዣ ውስጥ ለማስገባት የሚመች ሆነ። በተቦረቦሩ ድንጋዮዎች ውስጥ ሲገቡ ደግሞ በመፈንዳት ድንጋዩን ይበታትኑት ጀመር። አዲሱን ፈንጂ “ዳይናማይት” ብሎ ሰየመው። እአአ በ1867 ደግሞ የፈጠራ ባለቤትነት መብት አገኘበት። ዳይናማይት (ድማሚት) የማዕድን ቁፋሮ፣ የድንጋይ ማውጣት፣ የመንገድ እና የባቡር ሃዲድ ግንባታ ሥራ ላይ ተፈላጊ ሆነ።

እአአ በ1898 በተካሄደው በስፔን-አሜሪካ ጦርነት ወቅት ደግሞ “ዳይናማይት” የተባለ ሽጉጥ ጥቅም ላይ ዋለ። በሕይወት ዘመኑ ወደ 355 የፈጠራ ባለቤትነት ያገኘው አልፍሬድ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ትምህርት የመቀበል ችግር ካለባቸው ተማሪዎች መካከል መማሩን በኢንግሪድ ካርልበርግ የተጻፈው የኖቤል የሕይወት ታሪክ ያስረዳል።

አልፍሬድ ኖቤል እአአ በ1896 ሕይወቱ ሲያልፍ ወደ ጦር መሣሪያ ማምረቻ ድርጅትነት የተቀየረውን ቦፎርስ የተባለውን የስዊድን ብረታ ብረት ኩባንያን ጨምሮ 90 ፋብሪካዎች ከ20 በሚበልጡ የዓለም ሀገራት ነበሩት። ወንድሞቹ ሩሲያ ውስጥ በነበራቸው የነዳጅ ንግድ ላይ ኢንቨስት በማድረግም በሀብት ላይ ሀብት አፍርቷል።

ኖቤል በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ፣ በሕክምና ወይም በፊዚዮሎጂ፣ በሥነ ጽሑፍ እና በሰላም ዘርፎች የሰውን ልጅ ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ ሰዎች ዓመታዊ ሽልማቶችን ለመስጠት ሀብቱን (3 ሚሊዮን ዶላር) አበርክቷል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You