የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ በዘመናት መካከል በኢትዮጵያዊነቱ ተደራድሮ የማያውቅ ፣ በሀገረ መንግሥት ግንባታውም ሆነ ፤ ሀገረ መንግሥቱን አጽንቶ በማስቀጠል ሂደት ውስጥ ሰፊ አበርክቶ ያለው ሕዝብ ነው ። በታሪክ የኢትዮጵያውያንን እጣ ፈንታ የተጋራ ወደፊትም ቢሆን እጣፈንታው ከኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር የሚጋራ ሕዝብ ነው።
እንደ ሀገር የትናንት ታሪካችን ደማቅ አካል የሆነው የትግራይ ሕዝብ ፤ ከፍ ባለ ሃይማኖታዊ እና ማኅበረሰባዊ ሥነምግባር የሚጠቀስ ፤ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያያዊ ለፍትህ እና ለነጻነት ቀናኢ የሆነ ፤ ለብሔራዊ ክብር ራሱን መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ሁሌም ዝግጁ የሆነ ፤ ለፍቅር እና ከዚህ ለሚመነጭ ወንድማማችነት ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ሕዝብ ነው።
ከሳለፋቸው ብዙ የሰላም እጦት ዓመታት ፤ በነዚህ ዓመታት ከከፈላቸው ተዘርዝረው የማያልቁ አላስፈላጊ ዋጋዎች አኳያ ፤ ሰላም እና ከሰላም የሚመነጭ ሕይወትን ለራሱ ፣ ለሀገሩ እና ለመጪዎቹ ትውልዶች አብዝቶ የሚመኝ ፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት ያለው ሕዝብ ነው ።
ይህ ሕዝብ ማኅበረሰባዊ ማንነቱ ከተገነባበት መንፈሳዊ እና ማህበረሰባዊ እሴቶቹ፤ ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ከተጓዘባቸው የሕይወት ውጣ ውረዶች ካካበተው ተጨባጭ ተሞክሮ አኳያ፤ ከጦርነት እና ከግጭት ተጠቃሚ የሚያደርገው ምንም ነገር ሊኖር እንደማይችል በአግባቡ የተረዳ ነው ።
ይህንን ሕዝብ እናውቀዋለን እንወክለዋለን ፤ የሚሉ ፖለቲከኞች ከሁሉም በፊት ይህንን የሕዝቡን አሁናዊ እውነታ በአግባቡ ሊረዱ ፤ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ከዚህ የማኅበረሰብ ተጨባጭ እውነታ ጋር የተጣጠመ መሆኑን ቆም ብለው በሰከነ መንፈስ ሊያስቡት ይገባል።
ይህ ሕዝብ ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በነጻነት፣ በዴሞክራሲ እና በፍትህ ስም በተካሄደው መራራ ትግል ምን ያህል የትግሉ ተጠቃሚ ነበርኩ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከማንም በላይ ሊናገር የሚችለው ራሱ ነው። በትግሉ ወቅት የከፈለው መስዋእትነት ምን ያህል የነጻነት፣ የዴሞክራሲ እና የፍትህ ጥማቱን አርክቶታል ለሚለውም መልሱ በእጁ ነው።
ከዚህም ባለፈ ከለውጡ ማግስት በፌዴራል መንግሥቱ እና በሕወሓት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት በተቀሰቀሰው ጦርነት የቱን ያህል ዋጋ እንደከፈለ ፣ ምን ያህል ልብ ሰባሪ በሆነ ክስተት ውስጥ እንዳለፈ ፤ ክስተቱ ምን ያህል ሕዝቡን ተጨማሪ የኀዘን ማቅ እንዳለበሰው የአደባባይ ሚስጥር ነው።
የትግራይ ሕዝብ በነጻነት፣ በዴሞክራሲ እና በፍትህ ስም ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎ ፍላጎቶቹን ተጨባጭ ማድረግ አልቻለም ፣ ለምን ለተመሳሳይ የዓላማ ትርክት በየጊዜው መስዋእት ለመክፈል ይገደዳል ፤ መስዋእትነቱ ፍሬ ላለማፍራቱስ ማነው ተጠያቂ የሚሉትን ጥያቄዎች አሁን ላይ ማንሳት ተገቢ ነው።
ሀገርን ጨምሮ የትግራይ እናቶች በብዙ ተስፋ የሚጠብቋቸው የትግራይ ወጣቶች በየወቅቱ በሚፈጠር አለመግባባት ለሞት እና ለስደት የሚዳረጉበት እውነታ ማብቂያው መቼ ነው?፣ ለትናንቱም ሆነ ለዛሬው ጥፋት ተጠያቂ ማነው ፣ ጥያቄው አሁን ላይ ምላሽ የሚፈልግ ፤ የትግራይን ሕዝብ ወደሚፈልገው ሰላም እና መረጋጋት የሚያመጣ ነው።
የትግራይ ሕዝብ እንደ አንድ ትልቅ የታሪክ ባለቤት ሕዝብ ምንድነው እየሆነ ያለው በሚል ቆም ብሎ ሊያስብ ወደሚያስችለው ስክነት ሊመጣ ይገባል ፣ አላስፈላጊ ዋጋ እየከፈለ ካለበት የግጭት አዙሪት ወጥቶ የራሱን ዕጣ ፈንታ በራሱ ወደሚወስንበት የታሪክ ምዕራፍ ሊሸጋገርም ይገባል ።
በተለይም ወጣቱ ትውልድ ካለበት ነባራዊ እውነታ አኳያ የራሱን እና የክልሉን ሕዝብ ዕጣ ፈንታ መወሰን በሚያስችል ዝግጁነት ራሱን ማብቃት፣ ትናንት ለነጻነት፣ ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ሕይወታቸውን የገበሩ ሰማዕታት መስዋእትነት በተጨባጭ ለትግራይ ሕዝብ ምን አተረፈለት ፣ ዛሬስ ያለው እውነታ ምን ያተርፍለታል የሚለውን በአግባቡ ሊመረምር ይገባል።
የጦርነት ከበሮ በተጎሰመ ቁጥር ፣ ሕይወቱን ለመሰዋዕት ከማዘጋጀት በፊት መስዋዕትነቱ በተጨባጭ ለትግራይ ሕዝብ ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል ፣ የተነስ ታጠቅ ጥሪ ከትናንት እንደ ሕዝብ ብዙ መስዋእትነት ካስከፈለው ተመሳሳይ ጥሪ በምን ይለያል ለሚለው ጥያቄም በቅድሚያ ምላሽ ሊያገኝለት ይገባል።
እንደ ትውልድ ካለው የራሱ መሻት/መፈለግ አንጻር ፤ በክልሉ ትናንት ሆነ ዛሬ የሆነው እና እየሆነ ያለው እውነታ ምን ትርጉም አለው? ፤ በሱ እጣ ፈንታ ላይ እየወሰነ ያለው ፤ ለምን እንዲወስን ሆነ ፤ አቅም ስለሌለው ወይስ አማራጭ ስለተነፈገ ? የሚ ለውንም ጉዳይ በአግባቡ ሊመረምረው ይገባል ።
እንደ ትውልድ ፍላጎቱ ምንድነው ? የጦርነት ገድል ወይስ ሰላም እና ከሰላም የሚመነጭ ልማት ፤ ወደ ግጭት የሚወስድ የጥላቻ ትርክት ወይስ በአብሮነት ትርክት የተሻሉ ነገዎችን መፍጠር ወደሚያስችል አዲስ የታሪክ ጅማሬ መምጣት የሚለውንም ጉዳይ አጥርቶ መመለስ ይጠበቅበታል ። ይህን ማድረግ ሲችልም ለራሱም ሆነ ለመጪው ትውልድ መትረፍ ይችላል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም