ቅዳሜ ታኅሳስ 24 ቀን 1946 ዓ.ም የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አስራ ሦስተኛ ዓመት ቁጥር 37 እትም “ምነው ቢቀር !!” በሚል ርዕስ ተከታዩን ገጠመኝ አስነብቦ ነበር።
ምነው ቢቀር !!
የቤት አመል ገበያ ይወጣል የሚባለው ያባቶች ተረት ሐሰት አይደለም። ታኅሳስ 4 ቀን 1946 ዓ.ም. ከዓለም ገና ወደ አዲስ አበባ በሚመላለሰው አውቶቡስ ላይ ለደረሰበት ባለጉዳይ የሚያሳዝን ለተመልካች የሚያስደንቅ ታሪክ አይቼ በጣም ተገረምኩ።
ታሪኩ እንደሚከተለው ነው። አንድ ወንድና ሴት ዕድሜያቸው ከእኩል ዘመን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ፤ ቀድሞ ያላወቁትን ነገር ለመድረስ ከአውሮፕላን ማረፊያ አጠገብ ተነስተው ወደ ዓለም ገና ለሽርሽር ሄደው ኖሯል። ይሄውም ከአዲስ ዘመን ወጣቶች ጋር ለመወዳደር በማሰብ ከቤታቸው በማለዳ ወጥተው እንደወጣቶቹም ከሽርሽሩ ቦታ ሰበታና ዓለም ገና ውለው ሲመለሱ “ስካር” በሚባለው የመጠጥ ድንጉላ ሲጫወቱ ውለው እየተምነሸነሹ ውበት በተመላው አውቶቡስ ወደቤታቸው ሲመለሱ፤ ወንድየው በሴትዮዋ ላይ ያየው ጥርጥር ኖሮ ፤ ቅናት በሚባለው በዳቢሎስ ቀስት ስለተነደፈ ፤ ሴትየዋን ከቤቱ ሳይደርስ ለመደብደብ ፈልጎ አቃቂ ወንዝ ላይ ሲደርሱ አውቶቡሱ እንዲያቆምለት ለመነ።
ከዚህ ወዲያ ሠራተኞቹ ኮንትሮሉና ሾፌሩ፤ እንዲሁም ገንዘብ ተቀባዩ ሆነው በመልካም ትህትና አውቶቡሱን አቆሙለት። ከዚህ በላይ ሰውዬው ተነሳና ሴትየዋ ያላወቀችበት መስሎት እንውረድ አላት። እሷም ቤታችን እኮ ገና ነው አልደረስንም ትንሽ ከፍ ብለን እንውረድ አለችው። ሰውዬው ግን አይሆንም ተነሽ ደርሰናል አላት። እሷም የተንኮል ምንጭ ኖራ፤ እሺ ይውረዱ ብላ እንደሚወርድ ሰው ብድግ አለችና በዚህ ጊዜ ይህ በስካር ሜዳ እንደ አንበሳ ጥጃ ያለቦታው የሚፈነጨው ሰውዬ እውነት ልትወርድለት የተነሳች መስሎት እየተንገዳገደ በጭንቅ ከአውቶቡሱ ወረደ።
በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ስራዋን አውቃ ኖሮ የቀኑን ጨለማነት አስመስላ እሳቸው ቢወርዱ ቤቴ ገና ነውና እዚህ አልወርድም አዲስ አበባ ነው ስትል ተመልሳ ቁጭ አለችና፤ ሹፌሩን ይልቅስ ሰዓት እንዳያልፍብህ መኪናውን ንዳ አለች። ይህን አነጋገሯን አንድ ሰው ስለሰማ ወራጁ ባሏ መሆኑን ያውቅ ኖሮ እናንተ የሰው ሚስት ይዛችሁ አትሂዱ፤ ይህ የወረደው ሰው ባሏ ነው ሲል ተናገረ። ከዚህ በኋላ ሠራተኞቹ የሰውዬውን ነገር ባለመዝለል፤ አንቺ ሴት ተነሺ ውረጂ እባክሽን፤ እኛ በእናንተ ጭቅጭቅ ሰዓት አለፈብን አሏት። እሷም አልወርድም ብላ ባሏን ካቃቂ በጨለማ ጥላው መጣች። ሠራተኞቹም በዚህ ምክንያት የደምብ ሰዓታቸው ስላለፈባቸው አዝነው ጎዳናቸውን ቀጠሉ።
ከዚህ ወዲያ በአውቶቡሱ ውስጥ በዚች ሴት ምክንያት የተደረገው አስደናቂ ጨዋታ ሽማግሌም ሆነ ወጣት ቀመስ የሆነውን ሁሉ እጅግ የሚያስደስት ነበር። ይልቁንም ለሰርግ በዓል እንደሚደረገው ጨዋታ፤
ተመልካቾች ስሙ ወሬ።
ዓለም ገና ገባች ዛሬ ።
እያሉ ሲጫወቱ መጡ። ከዚህ በኋላ የሴትየዋን መዳረሻ አላየውም። ስለዚህ ምነው ቢቀር ስል በአርእስቱ መነሻ ለማድረግ ያሳሰበኝ ጠባያቸው ሳያኮራቸው ከቤታቸው ወጥተው ካውራ ጎዳና ላይ ሲዘረር ስላየሁ ነው።
ጽጌ ወ. ጸ. (ዘሩፋኤል)
* * *
ቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 1943 ዓ.ም የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አስራ አንደኛ ዓመት ቁጥር 15 እትም፣ ጋሪ ጎታች ፈረስ የባለቤቱ ግርፊያ ቢቀርልኝም ተሳፋሪው በያዘው ዱላ ተጎዳሁ ብሎ ስሞታ አቅርቧል በሚል ተከታዩን ማሳሰቢያ አስነብቦ ነበር።
ማሳሰቢያ
ጅራፍ ቀረልኝ ብዬ እፎይ ብዬ ነበር። እኔም በዚህ ምክንያት አቅሜ በሚፈቅድልኝ መጠን ከመታዘዝና ከማገልገል አልተቆጠብኩም ነበር። ይሁንና አሁን ግን ባለቤቱ ሳይሆን በተራው ደግሞ በትር እየያዘ የሚቀመጠው ተከራዩ ስለሆነ፤ ፖሊሶች በማያውቁት ነገር በተከራዩ በኩል ተጎዳው። ስለዚህ ከፊቱ ባሰብኝ እያለ ጋሪ ጎታቹ ፈረስ ሲጮህ ይሰማልና ይታሰብበት።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 3/2011