አዲስ አበባ፡- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ኢትዮጵያ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በሰብዓዊ ልማት ዕድገት ማስመዝገቧን ገለጸ፡፡
ድህነትን ለማጥፋት እና በሀገራት መካከል በዘላቂ ልማት ረገድ ያለውን አለመመ ጣጠን ለመቀነስ ከ170 በላይ በሆኑ ሀገራት የሚሠ ራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የኢትዮጵያን የ2018 የሰብዓዊ ልማት ሪፖርት ትናንት በሂልተን ሆቴል ይፋ አድርጓል፡፡ ሪፖርቱን ያቀረቡት የተባ በሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያ ጀምስ ዋኪአጋ እንዳሉት፤ በሰብዓዊ ልማት መመዘኛ ነጥቦች ከ0.500 በታች በማስመዝገብ በዝቅተኛ የሰብዓዊ ልማት ምድብ ውስጥ ካሉት 40 ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ ብትሆንም ካለፉት አስራ አምስት ዓመታት ወዲህ ግን ጠንካራ ዕድገት ማስመዝገብና ዕድገቱንም ማስቀጠል ችላለች፡፡
እንደ የኢኮኖሚ ባለሙያው ማብራሪያ፤ እ.ኤ.አ. ከ2012/13 ጀምሮ የሰብዓዊ ልማት አመላካች በሁሉም ክልሎች ዕድገት አሳይቷል፡፡ ከትምህርት እና ከገቢ ንዑስ አመላካቾች ጋር ሲነጻጸር ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ ልማት ዕድገት ከፍተኛውን አስተዋጽኦ የሚያበረክተው ጤና ነው፡፡ በሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች የጤና ንዑስ አመላካች ለሰብዓዊ ልማት ደረጃ ዕድገት ዋነኛ ምንጭ ሆኗል፡፡
የትምህርት ስኬ ትም መሻሻል አሳይቷል፡፡ ነገር ግን በጾታ፣ በገጠር እና በከተማ መካከል ያለው ምጣኔ አሁንም ዝቅተኛ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 ዕድሜያቸው 10 ዓመት እና ከዚያ በላይ ከሆነ ልጆች መካከል 32 በመቶ ወንዶች እና 51 በመቶ ሴቶች የትም ህርት ዕድል አያገኙም ነበር፡፡ በተያያዘም በትምህርት ላይ መሆን ከሚገባቸው ወስጥ 1 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቁት፡፡ የትምህርት ወጪ ከፍተኛ ቢሆንም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ውጤታማነቱ አሁንም ዝቅተኛ ነው፡፡
በቀረበው ሪፖርት መሰረት በኢትዮጵያ ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚጠቀሙ በጋብቻ ውስጥ ያሉ ሴቶች ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2000 ከነበረበት 6 በመቶ በ2016 ወደ 35 በመቶ አድጓል፡፡ይህ አሃዝ ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን ከሰሓራ በታች ያሉ ሀገሮች ሳይጨምር 24 በመቶ ላይ ከሚገኘው አህጉራዊ አማካኝ ጋር ሲታይ በመጠኑ ከፍ ያለ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 4 /2011
የትናየት ፈሩ