ከአሜሪካ ወደ ቱርክ ሲጓዝ የነበረ የመንገደኞችን አውሮፕላን እያበረረ የነበረ ቱርካዊ ፓይለት በበረራ ላይ ሳለ ታሞ ሕይወቱ አለፈ።
ፓይለቱ ከአሜሪካዋ ሲያትል ወደ ቱርኳ ኢስታንቡል በረራ ላይ በነበረበት ወቅት ነው አየር ላይ ሕይወቱ ያለፈው።
የ59 ዓመቱ ካፒቴን ኢልሺን ፔህሊቫን አውሮፕላኑን እያበረረ በነበረበት ወቅት ራሱን በመሳቱ ሁለተኛው ፓይለት እና ረዳት አብራሪው አውሮፕላኑን መቆጣጠራቸውን የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ በኤክስ ገጻቸው ገልጸዋል።
“በአውሮፕላኑ ውስጥ ለፓይለቱ የመጀመሪያ እርዳታ ቢደረግለትም ሳይሳካ ቀርቷል። የአውሮፕላኑ አብራሪዎች በድንገተኛ ሁኔታ ለማረፍ ጥረት ቢያደርጉም ፓይለቱ በአየር ላይ እያለ ሕይወቱ አልፏል” ሲሉ ያህያ ኡስተን ገልጸዋል።
የቱርኩ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ኤርባስ ኤ 350 አውሮፕላን ኒውዮርክ ላይ እንዲያርፍ የተደረገ ሲሆን፣ ከዚያም መንገደኞቹን ወደ ቱርክ ለማብረር ዕቅድ ተይዞ እንደነበር ቃል አቀባዩ አክለዋል።
የበረራ ቁጥር ቲኬ 204 የሆነው አውሮፕላን ከሲያትል የተነሳው በሀገሬው ሰዓት አቆጣጠር ማክሰኞ ምሽት 1 ሰዓት አካባቢ ነበር።
አብራሪው በካናዳዋ ግዛት ኑናቩት ሕመም ማጋጠሙን ተከትሎ ባልደረቦቹ አውሮፕላኑን ተረክበው ወደ ጆን ኤፍ ኬኔዲ አየር ማረፊያ አቅንተዋል።
አውሮፕላኑ ከሲያትል ከተነሳ ከስምንት ሰዓታት በኋላ በኒውዮርክ አርፏል።
ከአውሮፓውያኑ 2007 ጀምሮ የቱርክ አየር መንገድ አብራሪ የነበረው ኢልሺን ፔህሊቫን መደበኛ የጤና ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን፣ ሥራቸውን ሊያስተጓጉል የሚችል ምንም ዓይነት የጤና እክል እንዳልነበራቸው አየር መንገዱ ገልጿል።
የቱርክ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማኅበር፣ ታትካ ፓይለቱ ለበርካታ ዓመታት የአቪዬሽን ማኅበረሰቡን እንዳገለገለ አስታውሶ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጆቹ እና ለሥራ ባልደረቦቹ መጽናናትን ተመኝቷል።
ፓይለቱ ሕይወቱ ያለፈበት ምክንያትም ሆነ ሕመም እስካሁን አልተገለጸም። አብራሪዎች በየ12 ወሩ መደበኛ የሕክምና ምርመራዎችን የሚያደርጉ ሲሆን፣ ዕድሜያቸው ከ40 በላይ የሆናቸው ፓይለቶች ደግሞ በየስድስት ወሩ የሕክምና የምስክር ወረቀታቸውን ማደስ አለባቸው።
በአውሮፓውያኑ 2015 የአሜሪካ አየር መንገድ ፓይለት ከፊኒክስ ወደ ቦስተን በሌሊት እየበረረ በነበረበት ወቅት ራሱን ስቶ በረራ ላይ ሕይወቱ አልፏል።
የ57 ዓመቱ ፓይለት ራሱን መሳቱን ተከትሎ ሌላኛው አብራሪ አውሮፕላኑን ተረክቦ በሲራከስ ግዛት በድንገተኛ ሁኔታ አርፏል።
በአሁኑ ወቅት በመንገደኞች አውሮፕላን ሁለት አብራሪዎች በአብራሪዎች ከፍል ውስጥ መገኘት አለባቸው።
ሆኖም የአውሮፓ ኅብረት የአቪዬሽን ደኅንነት ኤጀንሲ በበረራ ወቅት አንድ ፓይለት ትልልቅ የመንገደኞች አውሮፕላኖችን በብቸኝነት ለማብረር የሚያስችል ቴክኖሎጂ እየተሠራ ነው ብሏል።
የአውሮፓ ኮክፒት ማኅበር እና ሌሎች የፓይለቶች ማኅበራት በአውሮፕላኖች ውስጥ ያሉ አብራሪዎችን ቁጥር መቀነስ ደኅንነትን አደጋ ላይ ይጥላል በማለት ጅማሮውን ተቃውመዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም