የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እሥራኤል በኢራን ላይ ልትወስደው ስላቀደችው የአጸፋ ጥቃት መከሩ።
ሁለቱ መሪዎች ለ30 ደቂቃ በስልክ ባደረጉት ምክክር የአጸፋ ጥቃቱ ተገቢነት ላይ መስማማታቸውን ዋይትሐውስ ገልጿል።
እሥራኤል ከባላንጣዋ ኢራን በቅርቡ ለደረሰባት የባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ምን አይነት አጸፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ አልተገለጸም።
ፕሬዚዳንት ባይደን ባለፈው ሳምንት እሥራኤል የኢራን የነዳጅ እና የኒዩክሌር ጣቢያዎች እንዳታጠቃ ጥሪ ማቅረባቸው ቢነገርም ቴል አቪቭ የቴህራንን የኒዩክሌር ጣቢያዎች ዒላማ ልታደርግ እንደምትችል ይጠበቃል።
ተንታኞች እሥራኤል የኢራንን የባላስቲክ ሚሳኤል ማምረቻ ጣቢያዎች እና የአየር መቃወሚያ ሥርዓቶች ልትመታ እንደምትችል መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የእሥራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት “የእኛ (እሥራኤል) ጥቃት እልቂት የሚያስከትል፣ ዒላማውን የሚመታና ከሁሉም በላይ የማይጠበቅ ይሆናል” ማለታቸውን የእሥራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ኢራን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ከእሥራኤል የሚቃጣ የአጸፋ እርምጃ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል ስትል መዛቷ የሚታወስ ነው።
እሥራኤል በሊባኖስ ከሄዝቦላህ ጋር የምታደርገው የምድር ውጊያ እና በቤሩትና ሌሎች ከተሞች የምትፈጽመው የአየር ጥቃትም ባይደን እና ኔታንያሁ ከመከሩባቸው ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።
ፕሬዚዳንት ባይደን በዚሁ ወቅት እስራኤል በሊባኖስ የሚፈጸመው የአየር ጥቃት በንጹሐን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እንዲቀንስ አሳስበዋል ብሏል ዋይትሐውስ ባወጣው መግለጫ።
በተያያዘ ዜና እሥራኤል በቤሩት የምትፈጸመው የአየር ጥቃትና በደቡባዊ ሊባኖስ የሚካሄደው ውጊያ ቀጥሎ ወደ ሶሪያም ተሻግሯል።
የእስራኤል የጦር ጄቶች በሶሪያ በኢራን ድጋፍ ይደረግላቸዋል በተባሉ ቡድኖች እና የሄዝቦላህ አባላት ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን የሀገሪቱ ጦር ገልጿል።
በሶሪያ ቁኔትራ በተባለ አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት የሄዝቦላህ ክንፍ የሆነው “ጎላን ቴረሪስት ኔትወርክ” አባል የሆነውና ለሄዝቦላህ መረጃ የሚያቀብለው አድሃም ጃሁት ተገድሏል ብሏል ጦሩ ባወጣው መግለጫ።
የሶሪያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን በበኩሉ እሥራኤል በሆምስ እና ሃማ ከተሞች አቅራቢያ የተፈጸሙት የአየር ጥቃቶች “መጠነኛ የንብረት ውድመት” ማስከተላቸውን ዘግቧል።
እስራኤል በኢራን ይደገፋሉ የምትላቸው የፍልስጤም፣ የሊባኖስ፣ የሶሪያ፣ የየመን እና የኢራቅ ታጣቂ ኃይሎች የተቀናጀ ጦርነት ከፍተውብኛል ብላ ታምናለች። በጋዛ ከሃማስ ጋር ጦርነት ከጀመረች አንስቶም በሶሪያ እና የመን ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶችን ማድረሷ ይታወሳል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም