ከአንድ ማኅበረሰብ ተጠቃሽ ከሆኑ እሴቶች ውስጥ ጥሩ የሠራን ማበረታታት፣ መሸለም፤ ችግር ያለባቸውን መገሰጽ እና ለተግባሩ ተጠያቂ ማድረግ የተለመደ ነው። በዚህ እና ተመሳሳይነት ባላቸው የሞራል እሴቶች ትውልዶችን ኮትኩቶ ማሳደግ የአንድ ማኅበረሰብ ትልቁ ኃላፊነት ነው። ማኅበረሰባዊ መረጋጋት ከመፍጠር ባለፈ፤ የትኛውም ትውልድ በኃላፊነት መንፈስ ለራሱም ሆነ ለመጪዎች ትውልድ የተሻለ ሥራ ሠርቶ እንዲያልፉ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው።
እንደዚህ አይነት የሞራል እሴቶች በተለይም ሃይማኖታዊ ማንነት ባለበት ማኅበረሰብ ውስጥ ከፍ ያለ ትኩረት ያላቸው፤ በማኅበረሰቡ ቀጣይ ሕልውና/ዕጣ ፈንታ ላይ ከሚኖራቸው አዎንታዊ አስተዋፅዖ አኳያም በማኅበረሰቡ ውስጥ ባሉ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ አስተምህሮዎች ውስጥ ሰፊ ስፍራ የሚሰጣቸው ናቸው።
እነዚህ ማኅበራዊ እሴቶች ከማኅበረሰቡ አልፈው እንደሀገር ማንነት ባለው ማኅበረሰብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ የኃላፊነት መንፈስ እንዲሰርጽ በማድረግ፣ ስለ ራሱ፣ ቤተሰቡ፣ ማኅበረሰቡ እና ሀገር ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ በመፍጠር ሂደት ውስጥ የሚኖረው አስተዋፅዖ መተኪያ የሌለው ነው ።
ቀጣይነት ያለው በሥነ ምግባር የተገራ ትውልድ በመፍጠር፤ በሁለንተናዊ መልኩ የተረጋጋ ሀገር መገንባት፤ በዚህም የዜጎችን ማኅበራዊ ደኅንነት አስተማማኝ ማድረግ የሚያስችል ነው። ለሕግ እና ለሥርዓት ተገዢ የሆነ ትውልድ በማፍራትም ሠላም እና ልማት የሰፈነበት ሀገር በመፍጠር የሚኖረው አስተዋፅዖ የፍጻሜው መጀመሪያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ዓለም አሁን ላይ የደረሰችበት ሥልጣኔም ሆነ ሥልጣኔው የተገዛበት አስተሳሰብ፤ ከነዚሁ የትናንት የሞራል እሴቶች የተቀዳ፤ ዘመኑን በሚሸከም የተሐድሶ እሳቤ የተቃኘ ነው። ከሁሉም በላይ ለሕግ እና ለሥርዓት የተገዛ ትውልድን በመፍጠር ላይ ያተኮረ፤ ለራሱ፣ ለሚኖርበት ማኅበረሰብ እና ለሀገሩ በኃላፊነት መንፈስ የሚንቀሳቀስ፤ በዚህም የመንፈስ እርካታ የሚሰማው ትውልድ መፍጠር ነው ።
ከመሠልጠን ባለፈ የሠለጠነ ሀገር በመፍጠር የተሳካላቸው ሀገራት፤ የሥልጣኔያቸው ትልቁ ምስጢር ቀጣይነት ባለው መንገድ ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ መፍጠራቸው፤ ይህንን የሚያስቀጥል ጠንካራ ተቋማዊ አቅም መገንባታቸው ነው። ትውልዶች በዕለት ተዕለት የሕይወት መስተጋብራቸው ውስጥ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ የሚያስችል ማኅበረሰባዊ ስብዕና መፍጠራቸው ነው።
ሀገራችን አብዝቶ እንደሚነገረው እና እንደሚሰማው የሃይማኖት/የሃይማኖተኞች ሀገር ከመሆኗ አኳያ፤ አብዛኞቹ መንፈሳዊ እና ከዚሁ የሚቀዱት ማኅበራዊ እና ባሕላዊ እሴቶቻችን፣ በማኅበረሰብ ውስጥ የሞራል እሳቤዎች ገዝፈው እንዲወጡ የሚያስችሉ፤ ከራሱ አልፎ ስለሌላው ወንድሙ ሆኖ ስለ ሀገር በኃላፊነት መንፈስ የሚንቀሳቀስ ትውልድ የማፍራት አቅም እንዳላቸው ይታመናል ።
ይህም ሆኖ ግን በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው እውነታ ከዚህ በብዙ መልኩ በተቃርኖ የሚታይ ነው። በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየሆነ ያለው፤ በትውልዶች መካከል በነበረው የሞራል እሴት ቅብብሎሽ ትልቅ ክፍተት መፈጠሩን በተጨባጭ የሚያመላክት ነው። ግለኝነት እና ራስ ወዳድነት፤ ሕገወጥነት እና አናርኪነት በስፋት የሚስተዋልበት ነው።
የሀገርን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚጎዱ፤ የሕዝባችንን የእለት ተእለት ሕይወት የሚፈታተኑ ሕገወጥ ተግባሮች የሕጋዊነት ያህል በአደባባይ አቅም አግኝተው፤ ሀገር ለከፋ አደጋ፤ ሕዝብም ውስብስብ ለሆኑ ችግሮች ዳርገዋል። ከዚህ ችግር ለመውጣት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ቢቀጥሉም፤ ከችግሮቹ ጥልቀት እና ስፋት አኳያ ዛሬም ፈተና እንደሆኑ ነው ።
ከነዚህ ችግሮች ውስጥ በዋንኛነት የሚጠቀሰው በነጋዴው ማኅበረሰብ በስፋት የሚታየው ግብር በአግባቡ አለመክፈል ነው ። ችግሩ በዋንኛነት ለሕግ እና ለሕጋዊ ሥርዓት ካለመገዛት፣ ከተበላሸ የሞራል ስብዕና የሚመነጭ፤ ከዛም ባለፈ እንደ ሀገር ዘመናዊ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት ማበጀት ካለመቻላችን የሚነሳ ነው።
በርግጥ ካለን የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ግንባታ እና በብዙ የሞራል አስተምህሮዎች ውስጥ እንደማለፋችን ግብርን በኃላፊነት የመክፈል ጉዳይ ብዙ የሚያነጋግረን አዲስ ሀገራዊ አጀንዳ አይደለም። አብሮን ዘመናት ያስቆጠረ፣ ለሀገረ መንግሥቱ እስከ ዛሬ መቆየት እና መጽናት አቅም የሆነ ጉዳይ ነውና። ዛሬ ላይ ቆመን ለምናልማት የነገይቱ የበለጸገች ኢትዮጵያም መሠረት የሚሆን ነው።
የበለጸገች ሀገር የመፍጠሩ እውነታ ከምንም በላይ ኃላፊነት የሚሰማው እና ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት መነቃቃት ያለው ትውልድ መፍጠር ስንችል እንደሆነ ይታመናል። አሁን ካለንበት ተጨባጭ እውነታ አኳያ ችግሩን ለመሻገር የወላጆችን፣ የማኅበረሰቡን እና የመንግሥትን የተቀናጀ ሥራ ይፈልጋል፤ ጊዜ ልፋት እና ድካምንም ይጠይቃል።
ይህም ሆኖ ግን ያለውን ሀገራዊ እውነታ ግምት ውስጥ በማስገባት በግብር አሰባሰብ ሂደት ኃላፊነታቸው ለመወጣት ጥረት ለሚያደርጉ ዜጎች እና ተቋማት በአደባባይ እውቅና መስጠት ከተበላሸ አሠራር ለመውጣት እንደ አንድ ስትራቴጂክ አቅም ተደርጎ የሚወሰድ፤ ግብር ከፋይ ዜጎች የሚጠበቅባቸውን በተሻለ የኃላፊነት መንፈስ እንዲወጡ መነቃቃት የሚፈጥር ነው!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም