ኢትዮጵያን ከጥር 1864 ዓ.ም እስከ መጋቢት 1881 ዓ.ም የመሩት ንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ የተወለዱት ከ186 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (ሐምሌ 5 ቀን 1825 ዓ.ም) ነበር።
አፄ ዮሐንስ ፬ኛ የተንቤንና የእንደርታ ባላባቶች ከነበሩት ወላጆቻቸው ሐምሌ 5 ቀን 1825 ዓ.ም. ማይ በሀ በሚባል ሥፍራ ተወለዱ። ከመንገሣቸው በፊትም ‹‹ርዕሰ መኳንንት ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ›› በመባል ይታወቁ ነበር። በወቅቱም በትግራይ መኳንንት እግር ተተክተው የአካባቢው ገዢ ሆነው ቆይተዋል። በሰሜን በኩል በወደቡ አቅራቢያ መገኘታቸውም ከአውሮፓውያን ቆንሲሎች ጋር ወዳጅነት እየመሰረቱ መጠነኛ የትጥቅ ድጋፍ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። ደጃዝማች ካሳ ምርጫ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት እንደሚሆኑ እርግጠኛ ስለነበሩ ‹‹ደጃዝማች›› ከነበሩበት ግዜ ጀምሮ ራሳቸውን ለውጭ አገራት መንግስታት በደብዳቤ ያስተዋውቁ ነበር።
ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ፣ ከእርሳቸው በፊት የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩትንና አገሪቷን ለሦስት ዓመታት ‹‹የገዙትን›› አፄ ተክለ ጊዮርጊስን ዓድዋ አካባቢ አሳም በሚባል ሥፍራ ላይ ሐምሌ 5 ቀን 1863 ዓ.ም ወግተው ድል ካደረጉ በኋላ፣ ለበዓለ ንግስናቸው የሚያስፈልገውን ሲያደራጁ ቆይተው ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም በእለተ እሁድ በአክሱም ፅዮን ቤተክርስቲያን በጳጳሱ አቡነ አትናቴዎስ እጅ ተቀብተው ‹‹ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ግርማዊ ዮሐንስ ራብዓዊ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ፅዮን ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ነገሡ።
ለሀገራቸውና ለሃይማኖታቸው ባላቸው ቀናኢነት የሚታወቁት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ፣ ከነገሱበት ጊዜ ጀምሮ ንጉሰ ነገስቱ በተቻላቸው መጠን ኢትዮጵያን አንድ የማድረግና በአንድ ማዕከላዊ መንግስት ስር የምትተዳደር አገር እንድትሆን ጥረዋል። የየግዛቱ ንጉሶች እንዳሉ ሆነው እርሳቸው ደግሞ የሁሉም ነገስታት የበላይ ንጉሰ ነገስት ሆነው ለማስተዳደር ጥረት አድርገዋል። ከየአካባቢው መሳፍንት ጋር ሰላም በማውረድና ሀይማኖትን ዋና የፖለቲካ መሳሪያ አድርገው ማዕከላዊውን መንግስት ለማጠናከር ሞክረዋል።
አፄ ዮሐንስ ፬ኛ በተለያዩ አቅጣጫዎች ሀገር ለመውረር ከመጡት ከግብጾች፣ ከቱርኮች፣ ከጣሊያኖችና ከደርቡሾች (መሐዲስቶች) ጋር ያላባራ ጦርነት አድርገው ነፃ ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ያስረከቡ ትጉህ ንጉሥ እንደነበሩ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። በጉራዕ፣ በዶጋሊ፣ በጉንደትና በሌሎች ቦታዎች የተቀዳጇቸው ድሎች ለዚህ ማስረጃዎች ናቸው።
አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ሕይወታቸውን ያጡት ለሀገራቸው ሉዓላዊነት በከፈሉት መስዋዕትነት ነው። መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም ከደርቡሾች ጋር በተደረገው ጦርነት ላይ እንደ ተራ ወታደር መሐል ገብተው ሲዋጉ የዋሉት ንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ጦራቸው ሊያሸንፍ ከጫፍ ደርሶ ሳለ፣ ንጉሰ ነገሥቱ በድንገት ተመትተው በማግሥቱ አረፉ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 3/2011
አንተነህ ቸሬ