ከ801 ሺህ በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በዘንድሮው ዓመት ከ801 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ተገለጸ። በዚህም 16 ሺህ የሚሆኑ እናቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተጠቁሟል።

6ኛው “የሚላን የከተማ የምግብ ፖሊሲ ስምምነት” ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፣ ጤናማ እና ፍትሐዊ ዓለምን ለመገንባት የተቀናጀ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ የትምህርት ቤት የምግብ ፕሮግራሞች ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። በዚህ ረገድ አዲስ አበባ የተሻለ ተሞክሮ እንዳላት ጠቁመዋል።

በከተማዋ በዘንድሮው ዓመት ከ801 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ መሆናቸውንና 16 ሺህ የሚሆኑ እናቶች የሥራ ዕድል እንዳገኙ አስታውቀዋል።

አዲስ አበባ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራምን ለሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ማቅረቧን የገለጹት ምክትል ከንቲባው፤ በዚህም ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ምግብ በትምህርት ቤቶች በማግኘት ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉና ጤናቸው እንዲጠበቅ መደረጉን ገልጸዋል።

እያንዳንዱ ልጅ ለማደግና ለመማር የሚያስፈልገውን የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ የትምህርት ቤት ምግብ ፕሮግራሞች አስፈላጊ መሆናቸውንም አመላክተዋል።

ምክትል ከንቲባው፤ የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብሩ በመላ ሀገሪቱ ከሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሕጻናትን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል። ይህ ጅምር ከፌዴራል መንግሥት በተለይም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠንካራ ድጋፍ ማግኘቱን ጠቁመዋል።

አዲስ አበባ ፈር ቀዳጅ ከተማ በመሆኗ የዚህ ፕሮግራም ስኬት በሀገር ውስጥ በማሳየቷ ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች አርዓያ ሆናለችም ነው ያሉት።

በማኅበረሰብ ምገባ ፕሮግራም ደግሞ ከ36 ሺህ በላይ አረጋውያን እንዲሁም ነዋሪዎች በምግባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል። እነዚህ መርሐ ግብሮች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ ብቻ ሳይሆን ጤናማ እና ዘላቂ የአመጋገብ ልማዶችን በማስተዋወቅ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌሴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የሚላን የከተማ ምግብ ፖሊሲ ስምምነትን እ.ኤ.አ በ2021 አባል በመሆን መቀላቀሏን ጠቅሰው፤ በምገባ ፕሮግራሙ ያላትን ጠንካራ አቋም አድንቀዋል።

የአዲስ አበባ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ለከተማዋ ኩራት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ከተሞችም አርዓያ መሆኑን ተናግረዋል።

ፎረሙም የተሳካ የትምህርት ቤት ምገባ ሥራዎችን ለማሳየት፣ እንዲሁም ሁሉም ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ከተሞች ያላቸውን ሚና የሚያጐላ መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ከ40 በላይ የሚሆኑ የከተማ ተወካዮች፤ አንዲሁም ከጣሊያኗ ሚላን ከተማ ፖሊሲውን የሚመሩ አካላት ተገኝተዋል።

እ.ኤ.አ በ2015 የተቋቋመውና 233 ከተሞችን በአባልነት ያቀፈው የሚላን የከተማ ምግብ ፖሊሲ ስምምነት በከተሞች ውስጥ ዘላቂ የምግብ ሥርዓት አተገባበርን ለማስተዋወቅ አልሞ እየተሠራ ያለ ነው።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You