ዳራ
እንደምን ሰነበታችሁ አንባቢዎቻችን? እንኳን በጤና ተገናኘን! የዛሬው ጉዳያችን ከሰሞኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባጸደቀው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ የማሻሻያ አዋጅ ዙሪያ ያጠነጠነ ይሆናል።
በኢትዮጵያ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥን በተመለከተ “በሕዝብ እንደራሴዎች” የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀት የጀመረው ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ነው።በወቅቱ ንግድን ለማዘመንና የተሳለጠ የማድረግ ዓላማን ሰንቀው ከተጣሉ መሰረቶች ውስጥ አንዱ የንግድ ሥራን የመመዝገብና ፈቃድንም በመስጠት እንዲከናወን ማድረግ ነበር።(በእርግጥ ከዚያ ቀደም ብሎም ቢሆን የንግድ ብድር፣ የንግድ ኪሳራ እንዲሁም የኩባንያ ሕጎችም በሥራ ላይ እንደነበሩ ያስታውሳል)፡፡
በወቅቱ የንግድና የኢንዱስትሪ ሥራዎችን ለማስመዝገብ (አዋጅ ቁጥር 184/1954)፤ የኢንዱስትሪ ፈቃድን ለማግኘት (አዋጅ ቁጥር 292/1963) እና የውጭ አገር ንግድ (አዋጅ ቁጥር 293/1963) እንዲሁም የተለያዩ የንግድና ኢንዱስትሪ ምዝገባና ፈቃድን የተመለከቱ ደንቦች በሥራ ላይ ውለዋል።እስካሁንም ድረስ በሥራ ላይ ያለው የንግድ ሕግ የወጣውም በ1952 ዓ.ም. ነበር።
በወታደራዊ አገዛዝ ዘመን ደግሞ በአጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴው የተቀየደበት ወቅት እንደነበር አይዘነጋም።በወቅቱም ደርግ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥን በተመለከተ የአገር ውስጥ ንግድ ሥራ መቆጣጠሪያ አዋጅ (ቁጥር 335/1979) እና ደንብ (ቁጥር 109/1979) እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፈቃድ ደንብ (ቁጥር 8/1982) አውጥቷል።
በደርግ ውድቀት ማግስት አገራችን የነጻ ገበያ የኢኮኖሚ መስመር መከተሏን መነሻ በማድረግ ከዚያ ቀደም በሥራ ላይ የነበሩት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥን የተመለከቱ ሕግጋት በሙሉ በአዋጅ ተሻሩ።ለዚህም ምክንያቶች ከነበሩት ውስጥ ቀዳሚው የንግድ ሥራ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጡ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚውን ለማራመድ በሚያስችል መልኩ መመራት አለበት የሚለው ነበር።በመሆኑም የንግዱን ማህበረሰብ ከምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙትን መሰናክሎች ለማስወገድ ያለመ የመጀመሪያው አዋጅ በ1989 ዓ.ም. አዋጅ ቁጥር 67/1989 ሆኖ ጸደቀ።
ከዘጠኝ ዓመታት የትግበራ ጊዜ በኋላ ደግሞ በአዋጁ አፈጻጸም ወቅት ችግር የታየባቸውን ድንጋጌዎች ለማሻሻል በሚል አዋጅ ቁጥር 328/1995 በስራ ላይ ዋለ።ብዙም ሳይቆይ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በተለይም የንግድ ማህበራትን የምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ለማሳለጥ በሚል በድጋሚ የማሻሻያ አዋጅ (ቁጥር 376/1996) ጸደቀ።በ2002 ዓ.ም ደግሞ ከዚያ ቀደም የወጡትን አዋጆች የሻረ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ (ቁጥር 686/2002) ወጥቶ ሲተገበር ቆይቷል።
እነዚህ ሁሉ አዋጆችና ደንቦች በስራ ላይ በዋሉባቸው ጊዜያት በነጻ ገበያ የኢኮኖሚ እሳቤ መሰረት የአገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ የተሻለ እንዲሆን የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸው አሌ የሚባል አይደለም።የንግዱ ዘርፍ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ቁልፍ ሚና ከያዙ የምጣኔ ሃብት ዘርፎች ውስጥ አንዱ እንዲሆን ካስቻሉት ምክንያቶችም ውስጥ አንዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ነው።
ያም ሆኖ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጡ ከዘመናዊነት፣ ከቅልጥፍናና ፍትሃዊነት እንዲሁም ከመረጃ አያያዝ ውስንነቶች አንጻር የንግዱን ማህበረሰብ ለምሬት የዳረጉ ችግሮች ነበሩበት።በዚሁ መነሻነት ታዲያ መንግሥት የሕግና የአሰራር ክፍተቶችን በመድፈን እርካታን ለማሳደግ በሚል የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የመረጃ አያያዝን ማዘመን ላይ ያተኮረ ሌላ የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅ በ2008 ዓ.ም. አጽድቆ በሥራ ላይ አውሏል፡፡
ይሁንና የአገልግሎት አሰጣጡን በማሳለጥ ዘርፉን ወደፊት ያስጉዛል የተባለው ይህ አዋጅ ምንም እንኳን በብዙ መልኩ ከቀደሙት አዋጆች የተሻለ ቢሆንም ሳይውል ሳያድር ወደ ንግድ ሥራ ለመቀላቀል ለሚፈልጉም ሆነ በዘርፉ ውስጥ ላሉት ተዋንያን ማነቆ የፈጠረ ነው በሚል ከሚሰነዘር የሰላ ትችት ሊያመልጥ አልቻለም።በዚሁ መነሻ በቅርቡ በአገሪቱ የተፈጠረውን ሁለንተናዊ ለዉጥ ተከትሎ አላስፈላጊ ሕጎችን ለማስወገድና ለማሻሻል እየተወሰደ ባለው ርምጃ ይህም አዋጅ በለስ ቀንቶት ለመሻሻል በቅቷል።የማሻሻያ አዋጁም ሰኔ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ጸድቋል።
የማሻሻያ አዋጁ ምን አዲስ ነገር ይዟል?
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አፋኝ፣ አሳሪ፣ አግላይ፣ ቢሮክራሲን የሚያንዛዙ እና መሰል አሉታዊ ተጽዕኖ የፈጠሩ የህግና የአሰራር ማዕቀፎች በባለሙያዎችና በሚመለከታቸው ባለድርሻዎች እየተመከረባቸው የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።ዘንድሮ የመሻሻል ዕድል ከገጠማቸው ሕጎች ውስጥ ደግሞ አንዱ የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 ነው።
እርግጥ ነው ይህ አዋጅ የቀደመውን አዋጅ ሙሉ በሙሉ በመሻር በንግድ ስርዓቱ ላይ ማነቆ ሆነው የነበሩ ድንጋጌዎችን በማስወገድና በአንጻሩ ስርዓቱን የሚያቀላጥፉ አዳዲስ ሃሳቦችን በማካተት ነበር ብቅ ያለው።ይሁንና ባለፉት ሶስት የአዋጁ የትግበራ ዓመታት ሕጉ ለንግዱ ማሕበረሰብ ማነቆን የፈጠሩ ድንጋጌዎችን ያካተተ እና ጥቂት የማይባሉ ክፍተቶችም ያሉበት ሆኖ ተገኝተዋል።በውጤቱም የንግድ ሥራ ለመጀመርና ጀምሮም በማከናወን ሒደት ውስጥ የንግዱ ማሕበረሰብ እንዲያሟላቸው የሚጠየቁ መስፈርቶች ለምልልስና ለእንግልት የሚዳርጉ በመሆናቸው ኢትዮጵያን ለትችት የዳረገ ሆኗል።
በዚሁ መነሻም የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን ቀልጣፋ፣ ቀላል፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ዘመናዊ እና ተደራሽ እንዲሁም ለንግድ ሥራ ምቹ ለማድረግ በሚል አዋጁ ሊሻሻል ችሏል።የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤትም አዋጁን በሚያሻሽልበት ወቅት በአገራችን በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ውስጥ የሚታዩ ማነቆዎችን ማስወገድና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ሀገሪቱ ለንግድና ንግድ ሥርዓት ምቹ እንድትሆን ማድረግ የማሻሻያው ተቀዳሚ ምክንያት መሆኑን አብራርቷል።
ከማሻሻያዎቹ ውስጥ አንዱ የንግድ ምዝገባ ፈቃድ አገልግሎቶችን የኢንፎርሜሽን መገናኛ ቴክኖሎጂ አውታሮችን በመጠቀም ተገልጋዮች በአካል ሳይቀርቡ እንዲያገኙ የሚያስችሉ አሠራሮችን እና ሥርዓትን በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲዘረጋ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን (የክልል ቢሮዎችን) የሚያስገድድ አዲስ ድንጋጌ እንዲካተት መደረጉ ነው።ይህም መረጃን በቀላሉ ለደንበኞች ተደራሽ ለማድረግና የአገልግሎት አሰጣጡንም ለማዘመን የሚጠቅም በመሆኑ ለንግድ ስርዓቱ መልካም አዲስ ነገር ነው።
በእስካሁኑ አሰራር የንግድ ማህበራትን ለማስመዝገብ መስራቾች ወይም አባላት የመመስረቻ ጽሁፎቻቸውንና የመተዳደሪያ ደንቦቻቸውን በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ አረጋግጠውና አስጸድቀው የማቅረብ ግዴታ አለባቸው።ከዚህም በላይ ሰነዶቹን አረጋግጠው የሚያቀርቡት መዝጋቢው አካል ለሰነዶች ማረጋገጫ መስሪያ ቤት በሚልካቸው የመመስረቻ ጽሁፍና የመተዳደሪያ ደንብ ናሙናዎች መሰረት ብቻ ነው።ይህ አሰራር ተገልጋዩን ከአንድ ቢሮ ወደ ሌላው የሚያመላልስ በመሆኑ እንግልትንና መሰናክልን የፈጠረ በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ ሲያማርር ቆይቷል።
ከዚህ መነሻ እንግልትን በማስቀረት ቀላልና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አዲስ ስርዓት በአዋጁ ማሻሻያ ላይ እንዲካተት ተደርጓል።በዚሁ መሰረት የንግድ ማህበራት መመስረቻ ጽሁፎችና መተዳደሪያ ደንቦች እንዲሁም ማሻሻያዎችና ለውጦቻቸው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ አካላት ውስጥ በሚቋቋሙ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ውስጥ የሰነዶች ኤጀንሲ ሙያተኛውን በመመደብ እንዲያረጋግጥ የሚያስገድድ ድንጋጌ ተቀምጧል።ይህ ብቻ ሳይሆን በሚቋቋሙት የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች ውስጥ የገቢዎች ሚኒስቴርም የራሱን ሙያተኛ በመመደብ የግብር ከፋዩ መለያ ቁጥር እዛው እንዲሰጥ ያደርጋል።
የንግድ ሥራ ለመጀመር ብርቱ ጋሬጣ ከነበሩት የምዝገባ መስፈርቶች ውስጥ አንዱ የንግድ ማህበራት ሲቋቋሙ በጋዜጣ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረጉ የሚያስገድደው አሰራር ነበር።በጋዜጣ ማሳወጅ በአዋጅ ቁጥር 67/1989 እና በ1952ቱ የንግድ ሕግ አንዱ የምዝገባ መስፈርት ነበር።ይሁንና መስፈርቱ ለንግድ ሥራ መሰናክል መሆኑ ታምኖበት በአዋጅ ቁጥር 686/2002 እንዲሻር ተደርጓል።ከዚያ በኋላ በሚያስገርም ሁኔታ በስራ ላይ ባለው አዋጅ በድጋሚ መስፈርት ሆኖ በመምጣቱ በንግድ ምዝገባ ላይ እንቅፋት ሆኖ ዳግም ብቅ አለ።ነገር ግን በአሁኑ ማሻሻያ መስፈርቱ ሙሉ በሙሉ የተወገደ በመሆኑ ህግ አውጭው የሰራውን “ስህተት” አርሞታል።በተሻረው ድንጋጌ ምትክም የግለሰብ ወይም የንግድ ማህበራት ሲመሰረቱ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በራሱ የኢንፎርሜሽን መገናኛ ቴክኖሎጂ አውታሮችን በመጠቀም የተመዝጋቢዎቹን የምዝገባና ፈቃድ መረጃዎችን ይፋ እንዲያደርግ የሚያስገድድ አንቀጽ ተካቷል።
ማንኛውም የንግድ ማህበር ምዝገባ ለውጥ ወይም ማሻሻያ በሰነዶች ኤጀንሲ ከተረጋገጠ በኋላ ነጋዴዎች በ60 ቀናት ውስጥ ማስመዝገብ እንዳለባቸው ሕጉ የሚያስገድድ መሆኑ እንቅፋትን ፈጥሮ ቆይቷል።ይሁንና የቀን ገደብ ማስቀመጡ የንግድ ሥራን ለማሳለጥ እንቅፋት ከመሆን ውጭ አላስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ለውጡ ወይም ማሻሻያው በንግድ ሕጉ መሰረት እስከተከናወነ ድረስ ነጋዴዎች በቻሉ ጊዜ እንዲያስመዘግቡት የሚፈቅድ አሰራር ተዘርግቷል።
አንድ ነጋዴ ወይም የንግድ ማህበር በንግድ መዝገብ ውስጥ ከሰፈረ (ከተመዘገበ) በኋላ የንግዱን ዓለም ለመቀላቀል የንግድ ሥራ ፈቃድ በእጁ ማስገባት አለበት።ይሁንና ነጋዴው ተመዝግቦ የንግድ ፈቃድ ሳያወጣ ለአንድ ዓመት ከቆየ ምዝገባው እንደሚሰረዝበት አዋጁ ደንግጓል።ሕጉ በዚህም ሳይበቃው የንግድ ፍቃዱ የተሰረዘበት ነጋዴ በንግድ ምዝገባው ሌላ ተጨማሪ ንግድ ፍቃድ ያላወጣበት ከሆነ የንግድ ምዝገባውም እንደሚሰረዝ አስቀምጧል።ይህ ለንግድ ሥራ የቱን ያክል መሰናክል እንደሆነ መናገር ጉንጭ ማልፋት ይሆናል።ከዚህ መነሻ የማሻሻያ አዋጁ ሁለቱንም ቆላፊ ድንጋጌዎች ሙሉ በሙሉ በመሰረዝ የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አሰጣጥ ሂደቱን የተሳለጠ እንዲሆን ስርዓት አበጅቷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአዋጁ መሰረት የንግድ ምዝገባ የሚሰረዘው ነጋዴው የንግድ ሥራውን በማናቸውም ምክንያት የተወ ከሆነ፤ ንግዱን መነገድ እንደማይችል አስተዳደራዊ ርምጃ ሲወሰድበት ወይም በፍርድ ቤት ሲወሰንበት፤ ሃሰተኛ መረጃ ወይም ሰነድ አቅርቦ የተመዘገበ ከሆነ ነው።የንግድ ማህበራት ስረዛ የሚጸናው የስረዛው ማስታወቂያ በአመልካቹ በራሱ ወጪ በጋዜጣ ታትሞ ከወጣ ከአንድ ወር በኋላ ሲሆን፤ የግለሰብ ነጋዴዎች ስረዛ ደግሞ በጋዜጣ ማስነገር ሳያስፈልግ ስረዛው በመዝገብ ከሰፈረበት ጊዜ ጀምሮ ነው።ነገር ግን በተለይም የጋዜጣ ማሳወጅ መስፈርቱ የንግድ ማህበራትን ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ በመሆኑ በማሻሻያው ቀሪ ተደርጓል።በምትኩም የንግድ ማህበር ምዝገባ ስረዛ የሚፀናው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር (ቢሮ) የኢንፎርሜሽን መገናኛ ቴክኖሎጂ አውታርን ተጠቅሞ ካሣወቀበት ከአንድ ወር በኋላ እንዲሆን ተደርጓል።
አንድ ነጋዴ የንግድ ፈቃድ ካወጣ በኋላ ፈቃዱን በየጊዜው ማሳደስ አለበት።አንዳንዶች በነጻ ገበያ ውስጥ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ ከማውጣት ባለፈ እንዲያሳድሱት ሊገደዱ አይገባም ብለው ሲሞግቱ ይስተዋላል።ይሁንና ሕጋዊ፣ ፍትሐዊ፣ የሕዝብ ደህንነትና ጤና የተረጋገጠበት እንዲሁም ግብር በአግባቡ የሚሰበሰብበት የንግድ ስርዓት መስፈኑ ከሚረጋግጥባቸው መንገዶች አንዱ የንግድ ፈቃድ እድሳት ነው።በዚሁ መሰረትም አዋጁ የንግድ ፈቃድ እድሳት የሚከናወንባቸውን ስነ ስርዓቶች በዝርዝር አስቀምጧል።
የንግድ ፈቃድ ከማይታደስባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የንግድ ማህበራት በንግድ ምዝገባ ወቅት ካስመዘገቡት ካፒታል ሶስት አራተኛውን የበሉ ከሆነ (ከከሰሩ) ነው።ይሁንና ማህበሩ ከኪሳራው ሃምሳ በመቶውን አባላቱ ወደ ድርጅቱ ሂሳብ ገቢ የማድረጋቸውን ቃለ ጉባዔ ከሰነዶች ማረጋገጫ እና ከባንክ ሰነድ ካቀረቡ ፍቃዳቸውን ማደስ ይችላሉ።ያም ሆኖ ማህበራቱ በንግዱ ውስጥ እንዲሰነብቱና እንዲያገግሙ እድል ለመስጠት በሚል ድንጋጌው ተሻሽሏል። በዚሁም መሰረት ማህበራቱ ካስመዘገቡት ካፒታል ሶስት አራተኛውንና ከዚያ በላይ ከከሰሩ ከኪሳራው ሃምሳ በመቶ የሚለው ቀርቶ ካፒታላቸውን ከአንድ አራተኛ በላይ እንዲሆን በማድረግ ፈቃዳቸውን ማሳደስ እንዲችሉ ተፈቅዶላቸዋል።
የንግድ ፈቃድ የሚታደሰው በየዓመቱ ነው።ይኸውም በየበጀት ዓመቱ ከሐምሌ 1 እስከ ታህሳስ 30 ወይም ካስመዘገበው የበጀት ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ ነው።ነገር ግን በዚህ የፈቃድ ማሳደሻ ጊዜ ውስጥ ያላሳደሰ ነጋዴ ከጥር 1 እስከ ሰኔ 30 ላለው ጊዜ ከፈቃድ ማሳደሻው በተጨማሪ ፈቃድ ማሳደሱ ለዘገየበት ለጥር ወር ብቻ 2ሺ 500 ብር እና ለሚቀጥለው ለእያንዳንዱ ወር 1ሺ 500 ብር ቅጣት በመክፈል ፈቃዱን እንደሚያሳድስ አዋጁ ይደነግጋል።
በዚህ መሰረት ከቅጣት ጋር በማሳደሻ ጊዜ ውስጥ ያልታደሰ ፍቃድ ይሰረዛል።ፈቃዱ የተሰረዘበት ነጋዴም ፈቃዱን በወቅቱ ላለማሳደሱ ያቀረበው ምክንያት ተቀባይነት ካገኘ ቅጣቱን በመክፈል ፍቃዱ ከተሰረዘበት እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የተሰረዘውን እንደገና ማውጣት ይችላል።ይህ የፍቃድ ማደስና የቅጣት ሂደት የቱን ያክል የተወሳሰበና የተንዛዛ መሆኑን መገመት አያዳግትም።ነጋዴውንም ለእንግልትና ለሮሮ የዳረጉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም ወልዷል።የሆነው ሆኖ በቅጣት የማደሻ ጊዜ ውስጥ ያላሳደሰ ነጋዴ የማንንም ፈቃድና ተቀባይነት ማግኘት ሳያስፈልገው በቅጣት የማደሻ ጊዜው ከተጠናቀቀበት ቀን ጀምሮ ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 2ዐ ሺ ብር በመክፈል ማደስ እንዲችል ተሻሽሎ ተደንግጓል።
ነገር ግን በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አብዛኞቹ ነጋዴዎች በአነስተኛ ካፒታል የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው የ20 ሺ ብር ቅጣቱ በካፒታል ልዩነት ልክ ቢቀመጥ መልካም ነበር።ከዚህ ጋር ተያይዞ የወንጀል ቅጣቶችን በሚደነግገው የአዋጁ ክፍል የፀና የንግድ ሥራ ፈቃድ ሳይኖረው ወይም በንግድ ሥራ ፈቃዱ እንዲሰራ ከተፈቀደለት የንግድ ሥራ ውጭ ሲሰራ የተገኘ ማንኛውም ነጋዴ የንግድ ሥራ ሲያካሂድባቸው የነበሩ የንግድ ዕቃዎች እና አገልግሎት መስጫ እና ማምረቻ መሣሪያዎች መወረሳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከ15ዐሺ እስከ 3ዐዐሺ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ከ7 እስከ 15 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ ያስቀምጣል።ነገር ግን ይህ አንቀጽ አልተሻሻለም።የአሁኑ ማሻሻያ የንግዱን ስርዓት ለማሳለጥ ያለሙ ለውጦችን ከማድረጉ አንጻር በተመሳሳይ መልኩ ይህ ከባድ የእስራትና የገንዘብ መቀጮ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ የንግድ መስመር በማስገባት ላይ ብቻ ባለመ እና አነስተኛ የንግድ አቅም ያላቸውን ነጋዴዎች ባገናዘበ መልኩ ማሻሻያ ሊደረግ ይገባ ነበር።
የንግድ ስም በንግድ ስርዓት ቁልፍ ሚና ካላቸው መሰረታዊ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው።ከዚሁ መነሻ ማንኛውም ነጋዴ የንግድ ምዝገባ በሚያደርግበትና የንግድ ሥራ ፈቃድ በሚያወጣበት ቦታ የንግድ ሥሙን እንዲያስመዘግብ አዋጁ ያስገድዳል።ያም ሆኖ የንግድ ስም እንዲሁ በዘፈቀደ ወይም ነጋዴው ልቡ ያሻው ስለሆነ ብቻ የሚሰጥና የሚመዘገብ እንዳልሆነ ልብ ይሏል።እናም የንግድ ስም እንዳይመዘገብ የሚያደርጉ ምክንያቶች በሕጉ መዘርዘራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል።
በአዋጁ የንግድ ሥም እንዳይመዘገብ የሚያደርጉ ምክንያቶች ናቸው ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ፓርላማው በአሁኑ የህግ ማሻሻያው አንዱን ሰርዞታል።ይህም እንዲመዘገብ የተጠየቀው የንግድ ስም ታዋቂነትን ያተረፈ ሰው ስምን ያካተተ ሲሆንና ስሙን ለመጠቀምም የጽሁፍ ፈቃድ ያልቀረበ ሲሆን የሚለው ነው።ይህ ድንጋጌ በንግድ ምዝገባ ስርዓት ውስጥ መካተቱ “ታዋቂ” በሚል ለተገለጸውና አሻሚ ትርጉም ለሚኖረው ሰው ሞራላዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የማይሰጥ ከመሆኑም በላይ በንግድ ስርዓቱም ውስጥ መሰናክል ከመፍጠር ውጭ ፋይዳ የሌለው በመሆኑ መሰረዙ ይበል የሚያሰኝ ነው።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ሀምሌ 3/2011
ከገብረክርስቶስ