አውሮፕላን አብራሪው የመንገደኞች አውሮፕላን በማብረር ላይ እያለ ህይወቱ አለፈ

አውሮፕላን አብራሪው የመንገደኞች አውሮፕላን በማብረር ላይ እያለ ህይወቱ አለፈ።የ59 ዓመቱ ካፒቴን ኢሴሂነ ፔህሊቫን ንብረትነቱ የቱርክ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን አብራሪ ነበር። ይህ አብራሪ ከአሜሪካዋ ሲያትል ወደ ኢስታንቡል በመብረር ላይ እያለ ህመም ከተሰማው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ህይወቱ እንዳለፈ ተዘግቧል።

እንደ ዘገባው ከሆነ በበረራ ላይ የነበረው አውሮፕላን ረዳት አብራሪው ኃላፊነት በመውሰድ በመንገደኞች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረጉን የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።ቃል አቀባዩ ያህያ ኡስተን እንዳሉት፤ “ለካፒቴኑ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ለማድረግ የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን ተከትሎ ረዳት አብራሪው ወዲውኑ በድንገት በረራውን በማቋረጥ አውሮፕላኑን ወደ መሬት ለማሳረፍ እየሞከረ እያለ ህይወቱ አልፏል” ብለዋል።

ኤርባስ ኤ350 አውሮፕላኑ በኒዮርክ በድንገት ካረፈ በኋላ መንገደኞችን በመጫን ወደ ኢታንቡል የተጀመረው በረራ እንደቀጠለም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።አውሮፕላን አብራሪው ከፈረንጆቹ 2007 ጀምሮ የቱርክ አየር መንገድ አውሮፕላኖችን ሲያበር ነበር የተባለ ሲሆን፤ በየጊዜው የጤና ምርመራም ሲያደርግ ነበር ተብሏል።

እስካሁን ለአብራሪው ህይወት ማለፍ ምክንያት ምን እንደሆነ ይፋ አልተደረገም። አየር መንገዱ እድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ ለሆኑ አብራሪዎች በየ 6 ወሩ የጤና ምርመራ ማስረጃ እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ ሕግ አለው። ከዚህ በፊት በፈረንጆቹ 2015 ላይ የአሜሪካ አየር መንገድ አብራሪ ከአሜሪካ ፎኒክስ ወደ ቦስተን በመብረር ላይ እያለ የ57 ዓመቱ አብራሪ በድንገት ህይወቱ አልፎ አውሮፕላኑም እንዲያርፍ ተደርጎ እንደነበር አል ዐይን ዘግቧል።

አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You