በዩናይትድ ስቴትስ የምርጫ ዕለት በኢስላሚክ ስቴት ቡድን ስም ጥቃት ለማድረስ አቅዶ ነበር ያለውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሀገሪቱ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።ተጠርጣሪው ናስር አህመድ ታውሄዲ የሚባል የ27 ዓመት የአፍጋኒስታን ዜጋ ሲሆን፤ በኦክላሆማ ነዋሪ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ተናግሯል።
“ተከሳሹ በአይኤስ አነሳሽነት፣ በምርጫ ቀን፣ በሀገራችን ላይ የኃይል ጥቃት ለመፈጸም አሲሯል” ሲሉ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክሪስቶፈር ሬይ ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ግለሰቡ የጦር መሳሪያዎችን ለማጠራቀም እየሞከረ መሆኑን ኤፍቢአይ ገልጾ፤ የቤተሰቡን ንብረት በመሸጥ እነሱን ወደ ሌላ ሀገር ለማዛወር እርምጃ ወስዷል ብሏል።
ታውሄዲ ለውጭ ሀገር አሸባሪ ድርጅት ድጋፍ ወይም
ግብአት በመስጠት፣ ለማቅረብ በመሞከር፣ የጦር መሳሪያ እና ጥይቶችን ለመግዛት በመሞከር ወንጀል ወይም የሽብር ድርጊት ለመፈጸም በማሴር ነው የተከሰሰው። ኤፍቢአይ እንዳለው ከሆነ ታውሄዲ ስሙ ከማይታወቅ ተባባሪ ዘመዱ ጋር ይሠራ ነበር። ተባባሪው ወጣት እና የአፍጋኒስታን ዜጋ መሆኑም ተገልጿል።
በሕግ አስከባሪ አካላት በተገኙ የጉግል መዛግብት ላይ ተመስርተው ባገኙት ማስረጃም የኢስላሚክ ስቴት ፕሮፓጋንዳዎችን በኢንተርኔት እየተከታተለና እና ለአይኤስ ደጋፊ ሆኖ ለሚሠራው የበጎ አድራጎት ድርጅት ገንዘብ በመለገስ ተከሷል።
“አይኤስአይኤስ እና ደጋፊዎቹ በአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ላይ የሚያደርሱትን ቀጣይነት ያለው ስጋት መዋጋት
እንቀጥላለን። የአሜሪካን ሕዝብ ለማሸበር የሚሞክሩ ግለሰቦችን ለይተን እንመረምራለን። እንዲሁም ለሕግ እናቀርባለን” ሲሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሜሪክ ጋርላንድ ተናግረዋል።
ታውሄዲ ዋይት ሃውስን እና የዋሽንግተን ሃውልትን የሚያሳዩ በዋሽንግተን የሚገኙ የስለላ ካሜራዎችን በተመለከተ ጥናት ማድረጉን የፌዴራል መርማሪዎች ገልጸዋል። በተጨማሪም የላላ የመሣሪያ ሕግ ያላቸውን ግዛቶች በተመለከተም ጥናት አድርጓል። ታውሄዲ ጥቃቱን ለመፈጸም ኤኬ-47 ጠመንጃዎችን ለመጠቀም ፈልጎ ነበር ሲሉ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
መስከረም 26 እሱ እና ተባባሪው የጦር መሳሪያዎችን እና ጥይቶቹን ለመግዛት ለኤፍቢአይ በድብቅ ከሚሠሩና የመሣሪያ ነጋዴዎች መስለው ከቀረቡት ግለሰቦች ጋር ተገናኝተዋል። መሣሪያውን ከገዙ በኋላም ታውሄዲ እና ተባባሪው በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ከታሰረ በኋላ በተደረገ ምርመራ ታውሄዲ በምርጫ ቀን “በርካታ ሰዎች በተሰበሰቡበት” ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ለመፈጸም ማቀዱን እና ይህንንም በመፈጸም ለመሞት መዘጋጀቱን ለኤፍቢአይ አረጋግጧል ተብሏል። ታውሄዲ እአአ መስከረም 2021 በልዩ የስደተኛ ቪዛ ከባለቤቱ እና ከልጀቹ ጋር አሜሪካ ገብቷል። በተያዘበት ጊዜም በኦክላሆማ ሲቲ ይኖር እንደነበረም ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም