የስነ ጽሑፍ ተመራማሪ ፣ መምህር ፣ ገጣሚና ጸሐፊ ተውኔት ደበበ ሰይፉ የተወለደው ከ69 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (ሐምሌ 5 ቀን 1942 ዓ.ም) ነበር።
ልጅነት በሚል ግጥሙ “አይ ያች የዘመን አምባ፣ በብይ ድብደባ፣ በኳስ ጥብጠባ” ሲል የልጅነት ጊዜውን ተመልሶ የሚቃኘው ደበበ፣ በቀድሞ ሲዳማ ክፍለ ሀገር ይርጋለም ከተማ ከእናቱ ከወ/ሮ የማርያም ወርቅ አስፋውና ከአባቱ በጅሮንድ ሰይፉ አንተን ይስጠኝ ተወለደ።
የመጀመሪያ ወንድ ልጅ በመሆኑ በወላጆቹ ዘንድ ልዩ እንክብካቤ ይደረግለት ነበር። ገና ከልጅነቱ ፊደል እጣው የሆነ ጎበዝ ተማሪ ነበር። እናቱ እንደሚናገሩት ዳዊት ለመድገም ምንም ያህል ጊዜ አልወሰደበትም። አባቱ ከቄስ ትምህርት ቤት አውጥተው መደበኛ ትምህርት ቤት ሲያስገቡት ልበ ብሩህነቱን አይተው እዚያው የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሊያደርጉት የነበሩት የኔታ በጣም አዘኑ።
አባቱ አዲስ አበባ ደርሰው ሲመለሱ መጽሐፍትና መፅሔቶችን ገዝተው መምጣታቸው ደበበ ገና ከልጅነቱ ከፍተኛ የንባብ ፍቅር እንዲያድርበት አድርጓል። ደበበ ከልጅነቱ ጀምሮ ከሰው ተገልሎ የመቀመጥ ልማድ ነበረው። ብቻውን ወራጅ ወንዝ እያየ መቀመጥ ያስደስተው ነበር።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በይርጋለም ከተማ ራስ ደስታ ትምህርት ቤት ከተከታተለ በኋላ ቤተሰቦቹ ወደ አዲስ አበባ በመምጣታቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት አጠናቀቀ። ቀጥሎም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ዓመት የቢዝነስ ትምህርት ከተማረ በኋላ በትምህርቱ ባለመደሰቱ “አእምሮን የማይቆነጥጥ ትምህርት” በማለት ወደ አርትስ ፋክልቲ ተዘዋውሮ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል በ1965 ዓ.ም. በስነ ፅሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ። ከአምስት ዓመት በኋላም በዚሁ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪውን በእንግሊዝኛ ስነ ጽሑፍ አራት ነጥብ በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቀቀ። ውጤቱ በውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪውን እንዲቀጥል የሚያስችለው ቢሆንም ሳይቀጥል ቀርቷል። በርካታ የስራ ባልደረቦቹ ትምህርቱን እንዲቀጥል ቢወተውቱትም በጄ አላለም። የሚሰጠው መልስ “መጽሐፌ የዶክተር ደበበ ሰይፉ እንዲባል ነው ? አሁን ያለሁበት ሁኔታ ብዙ ነገር እንድሰራ የሚያደርገኝ ነው” የሚል ነው።
በተማረበት ዩኒቨርሲቲ እስከ 1980 ዓ.ም. ስነጽሑፍ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ ወደ ቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ተዘዋውሮ ማስተማር ቀጠለ። ደበበ በርካታ ወጥ ትርጉም ተውኔቶችን ጽፏል። ከነዚህ ውስጥ እናትና ልጆች ፣ ከባህር የወጣ አሳ ፣ እሷና እሱ ፣ ሳይቋጠር ሲተረተር ፣ የህጻን ሽማግሌ ፣ ክፍተት ፣ ዕድምተኞቹ እና ጋሊልዮ ጋሊሊ ይጠቀሳሉ።
ከ1978 እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ሊቀመንበር ሆኖ ሰርቷል ፤ ማህበሩ የሚያሳትማት “ብሌን” መጽሔት ዋና አዘጋጅም ነበር። በተጨማሪም የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የቦርድ አባል በመሆን አገልግሏል። በምርምር ረገድም በኢትዮጵያ ስነፅሑፍ ላይ በርከት ያሉ ምሁራዊ መጣጥፎችን በአማርኛና በእንግሊዝኛ አበርክቷል። በዚህም ረዳት ፕሮፌሰር ለመባል በቅቷል።
ደበበ በኢትዮጵያ ሬዲዮ አማካሪና ረዳት አዘጋጅ ፣ እንዲሁም ተርጓሚ በመሆን ሰርቷል። ለአማርኛ ቋንቋ እድገት ለማርክሳዊና ለሙያዊ ስነጽሁፍ እሳቤዎች የሚያስፈልጉ ስያሜ ቃላት በመፍጠር ለቋንቋው እድገት የበኩሉን ድርሻ አበርክቷል። “መቼት”፣ “ገጸ ባህርይ” ፣ “ቃለ-ተውኔት” እና “ቧልታይ” ን የመሳሰሉ የሙያ ቃላት የደበበ ፈጠራዎች እንደሆኑ ይነገራል። ዶክተር ፈቃደ አዘዘ “አማርኛን ስለማናውቀው ነው እንጂ ሰፊና ጥልቅ ቋንቋ ነው” የሚል አስተሳሰብ እንደነበረው ይናገራሉ።
ደበበ ፈርጀ ብዙ ዝንባሌዎች ቢኖሩትም በአንባቢያን ዘንድ ይበልጥ የሚታወቀው በገጣሚነቱ ነው። ከፍተኛ የቋንቋ ክህሎትና ምጥቀት የሚንጸባረቅባቸው ግጥሞቹ በበርካታ አንባቢዎች ዘንድ አድናቆትን አትርፈውለታል። በማርክሳዊ አመለካከቱና በጋለ የአገር ፍቅሩ ሳቢያ ግጥሞቹ ባመዛኙ ማህበራዊ ቅኝት አላቸው። ለህዝብ ተቆርቋሪነቱ በበርካታ ግጥሞቹ ውስጥ ተንጸባርቋል። “ሐዘንሽ አመመኝ” እና “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ” በተሰኙ ግጥሞቹ 1966 ዓ.ም. ለተከሰተው ድርቅ መንግስት ያሳየውን ግዴለሽነት በተባ ብዕር በማቅረብ የድርቁን ሰቆቃና ያስከተለውን ውድመት አሳይቷል።
በመፅሐፍ መልክ የታተሙ አራት ሥራዎች አሉት፡- “የትያትር ጥበብ ከጸሐፌ ተውኔቱ አንጻር”፣ “ማርክሲዝምና የቋንቋ ችግሮች”፣ “የብርሃን ፍቅር ቅጽ 1” እና “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ፡ የብርሃን ፍቅር ቅጽ 2”
ከዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ጀምሮ የቅርብ ጓደኛው አቶ ታምራት እጅጉ ስለደበበ ሲናገር “ደበበ ስለ ልጅነት ጊዜዎቹ አውርቶ አይጠግብም ነበር። ስለ ይርጋለምና የልጅነት ዘመኑ ሲያነሳ ብትሰማ ፈዝዘህ ትቀራለህ፤ ስሜቱ ይሞቃል” ይላል። እውነትም “ይርጋለም” በሚለው ግጥሙ ይህ ፍቅሩ ጉልህ ሆኖ ይታያል ፤ “የልጅነቴ ህልም ቀለም ፣ አይኔን የከፈትሽው ጨረር ፣ ወርቃማይቱ ጀምበር” ሲል ያወድሳታል።
ደበበ በህይወቱ መጨረሻ በዙሪያው ባሉ ሰዎች ተበሳጭቶ ከዩኒቨርሲቲ መምህርነት ራሱን አሰናብቶ ቤት ውስጥ መዋል እንደጀመረ ይነገራል። ቆይቶም የመገጣጠሚያ አካላት ያለመታዘዝ ችግር ገጥሞት ታመመ። ለስምንት ዓመታት ያህል ህመሙ ጸንቶበት ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም በ50 ዓመቱ አረፈ። የቀብሩ ስነስርዓት የተፈጸመው በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን ሐውልቱ ላይ “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ” በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ የሚገኘው ተከታዩ ግጥም ተጽፏል፡-
ለምን ሞተ ቢሉ
ንገሩ ለሁሉ ሳትደብቁ ከቶ
ከዘመን ተኳርፎ
ከዘመንተጣልቶ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 3/2011
የትናየት ፈሩ