የሀገራችን ኢኮኖሚ ምሰሶ ተደርጎ የሚወሰደው የግብርናው ዘርፍ ዘመኑን በሚመጥን ፖሊሲ ፣ ቴክኖሎጂ እና የአሰራር ሥርዓት ባለመዘመኑ ምክንያት ሀገሪቱ ዘርፉን ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል ሰፊ የተፈጥሮ እና ሰፊ የሰው ኃይል ቢኖራትም በምግብ እህል ራሷን መቻል አቅቷት ለዘመናት ለተረጂነት ተጋልጣ ቆይታለች።
በየወቅቱ እያሻቀበ ከሚሄደው የሕዝብ ቁጥር ጋር ተዳምሮ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ችግሩን የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል። በዚህም ዜጎች በብዙ ትጋት እና ልፋት የሚያመርቱት የግብርና ምርት ከእጅ ወደአፍ ከመሆን ሊሻገር እና ከተረጂነት የተላቀቀ ሕይወት ሊመሩ አልቻሉም።
ከዚህ ይልቅ በየአስር ዓመቱ በሚፈጠሩ የድርቅ አደጋዎች ለከፋ አደጋ እንዲጋለጡ ፣እጃቸውን አጣምረው ምጽዋት እንዲጠብቁ ሲያደርጋቸው ኖሯል። ይህም በራሱ ብሔራዊ ክብራችንን በማሳነስ አንገት እንድንደፋ አድርጎናል። ዛሬም የብሔራዊ ክብራችን ጥላ ሆኖ እየተከተለን ነው።
ኋላቀር በሆነ መንገድ የሚመረተው ምርትም ቢሆን ፤በተመሳሳይ መልኩ ኋላቀር በሆነው የምርት መሰብሰብ ሂደት የመባከኑ እውነታ አጠቃላይ የሆነው የሀገሪቱ የግብርና ዘርፍ ሁለንተናዊ በሆነ ተሀድሶ ውስጥ እንዲያልፍ አስገድዶታል። ዘርፉ ጠንካራ በሆነ ፖሊሲ እና ከፖሊሲ የሚመነጭ የቴክኖሎጂ እና የአሠራር ሥርዓት ሊመራ እንደሚገባ አመላካች ሆኗል።
እንደሀገር በግብርናው ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ የምርምር ተቋማት ፈጥረን ወደ ሥራ ከገባን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ታሪክ ባለቤት ብንሆንም፤ የምርምር ተቋማትን ለዘርፉ ዋነኛ ስትራቴጂክ አቅም አድርገን ከመጠቀም ጋር በተያያዘ በነበረው ውስንነት ምክንያት ውጤታማ መሆን ሳንችል ቀርተናል።
ብዙ የግብርና የምርምር ተቋማት እና ተመራማሪዎች እያሉን፤ በተለያዩ ወቅቶች የነበሩ መንግሥታት ለግብርናው ዘርፍ ከቋንቋ ባለፈ ዘርፉን ሊለውጥ የሚችል የፖሊሲ ትኩረት ባለመስጠታቸው ከሀገሪቱ አምራች ዜጋ ከ80 በመቶ የሚሆነው በግብርና ዘርፍ ተሰማርቶ በምግብ እህል ራሳችንን ያልቻልንበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ይህንን መሠረታዊ ችግር ለመፍታት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ዘርፉን ዋነኛ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ምሰሶ አድርጎ በመውሰድ፤ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያመጣበት የፖሊሲ አቅጣጫ ተቀርጾለት ወደ ሥራ ተገብቷል፤ ያሉንን አቅሞች አቀናጅቶ በመጠቀም በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚያስችል ሥራም ከተጀመረ ውሎ አድሯል።
ከዚህም ውስጥ አንዱ ዘርፉን በቴክኖሎጂ እና በአሠራር ሥርዓት የማዘመን ተግባር አንዱ ነው። በዚህም ትራክተሮችን እና ኮምባይነሮችን ፣ ማዳበሪያ፣ምርጥ ዘር እና ጸረ- አረም ኬሚካሎችን በስፋት እና በወቅቱ ወደ አርሶ አደሩ በማድረስ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በመንግሥት በኩል የሚታየው መነቃቃት ከፍ ያለ ነው።
አርሶ አደሩም ቢሆን አቅሞቹን እያቀናጀ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ራሱን ለማገዝ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ፤በዘርፉ የአስተሳሰብ ተሀድሶ መኖሩን የሚያሳይ፤ እንደሀገር በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል የምናደርገው ሀገራዊ ጥረት አንድ እርምጃ ወደፊት መጓዙን የሚያመላክት እና የሚበረታታ ነው።
ከዚህ አኳያ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በኩታ ገጠም እርሻ ፤ በበጋ የመስኖ የስንዴ እርሻ እና በሩዝ ምርት እየተመዘገበ ያለው ስኬት፤እንደሀገር በግብርናው ዘርፍ ያለንን እምቅ አቅም ወደ አደባባይ ይዞ የወጣ፤አርሶ አደሩ በቂ ድጋፍ ካገኘ ምርታማነትን በማሳደግ ከራሱ ተርፎ ለሀገር የሚተርፍ አቅም እንዳለው በተጨባጭ ያሳየ ነው።
ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ መሬቶችን ለማስፋት፤ የውሃ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም እየተደረገ ያለው ጥረት እና እየተመዘገበ ያለው ውጤት ፤በሁሉም ዘንድ ተገቢውን ግንዛቤ ካገኘ ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት አቀናጅታ በዘርፉ ውጤታማ የምትሆንበት፤ ከተመጽዋችነት ወጥታ በዘርፉ የዓለምን ገበያ የምትቀላቀልበት ቀን ሩቅ አይሆንም።
ወቅቱ አርሶ አደር በሁለንተናዊ መልኩ የግብርና ባለሙያዎችን እና የመንግሥትን ድጋፍ በስፋት የሚፈልግበት የሽግግር ወቅት ከመሆኑ አንፃር፤ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በተለይም በምርት መሰብሰብ ወቅት የሚፈጠረውን ብክነት ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ በቂ ዝግጅት ከወዲሁ ማድረግ ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም