በየትኛውም የዓለም አካባቢ የሚገኝ ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎት ሰላም እና ልማት ነው። ሌላው ሁሉ ከዚህ የሚመነጭ እና ለዚሁ የተገዛ ነው። በተለይም ባለንበት ዘመን የሰው ልጅ ከደረሰበት የአስተሳሰብ ልቀት አኳያ የሰላም እና የልማት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል።
በተለይም በድህነት እና በኋላቀርነት የሚጠቀሱ ሀገራት፤ የሕዝቦቻቸውን የዘመናት ሆነ የእለት ተእለት የሰላም እና ልማት ጥያቄ ለመመለስ ከሁሉም በላይ ለሰላም እና ስለሰላም ያላቸውን አስተሳሰብ ሊመረምሩ፤ ሰላም የሕዝቦቻቸውን ጥያቄ ለመመለስም መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነ በአግባቡ ሊያጤኑት ይገባል።
በእነዚህ ሀገራት የሚገኙ የሕዝብ ጥያቄ አንግበናል የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሆኑ በነጻ አውጪ ስም ጠብመንጃ ያነገቡ ኃይሎች፤ ከፖለቲካ ስልጣን በላይ ሰላምን ትልቅ የፖለቲካ ስኬት አድርገው ሊወስዱት፤ ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት ሊፈጥሩ እንደሚገባ ብዙዎች የሚስማሙበት እውነታ ነው።
አሁን ባለንበት የፖለቲካ – ኢኮኖሚ እሳቤ ፤የጠብመንጃ ትግል ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ከመሆን ባለፈ የሕዝቦችን የሰላም እና የልማት ጥያቄ ለመመለስ እንደማያስችል ተጨባጭ እውነታዎች የሚያመላክቱት ነው፤ “በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት” የተገዛ የፖለቲካ ትግል ለተጨማሪ ጥፋት ሀገር እና ሕዝብን ከመዳረግ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም።
ዘላቂ ሰላም ማምጣት በማያስችል የፖለቲካ እሳቤ የሚከወን ልማት ፣ ቀጣይነት እና ማስተማመኛ የሌለው ነው። ዜጎች በልማት ላይ ያላቸውን ተስፈኝነት በማቀጨጭ ፤ በልማት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በእጣ ፋንታቸው ላይ ጨለምተኛ እንዲሆኑ ፤በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ለበለጠ ድህነት እና ኋላ ቀርነት የሚዳርግ ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን ከመጣንበት ከዚህ የተዛባ የፖለቲካ አስተሳሰብ የተነሳ፤ እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ ከፍለናል፤ እየከፈልንም ነው። ችግሩ አሁን ላለንበት ድህነት እና ኋላ ቀርነት በዋነኛነት የሚጠቀስ ፤ተስፋ ለምናደርጋቸው ብሩህ ቀናቶች ተግዳሮት እየሆነብን ያለ የአስተሳሰብ ስብራት ነው።
ለዚህች ሀገር ብሩህ ተስፋዎች፤ ለሕዝቦቿም የተሻሉ ነገዎች የሚያስብ የትኛውም ኃይል ከሁሉም በላይ የሕዝባዊነቱ መገለጫ የሚሆነው ስለሰላም የሚኖረው አመለካከት እና ከአመለካከቱ የሚመነጨው ድርጊቱ ነው። ከዚህ ውጪ በጠብመንጃ እና ከጠብመንጃ በሚመነጭ ስልጣን ተስፈኛ የሆነ ኃይል ለሕዝባችን ዘላቂ ሰላም እና ልማት ሊያመጣ አይችልም።
እስካሁን እንደ ሀገር የመጣንበት እያንዳንዱ የታሪክ ምእራፍ የሚያስተምረን፤ ከጠብመንጃ አፈሙዝ የመነጨ ስልጣን ሀገርን ከአንድ የጥፋት ታሪክ ወደሌላ የጥፋት ታሪክ በማሸጋገር ሀገር አሁን ያለችበት ድህነት እና ኋላቀርነት ላይ ማድረሱን ፤ በዚህም ማንም ተጠቃሚ አለመሆኑን ነው።
ለዚህ ደግሞ በትንሹ እንደ ሀገር ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የተጓዝንበትን መንገድ መመልከት፤ ምን እንዳተረፍን ማስተዋል ተገቢ ነው። በጠብመንጃ የሚወለደውን ስልጣን የተደረጉ ሙከራዎች የቱን ያህል ትውልዶችን ብቻ ሳይሆን የትውልዶችን ተስፋ እንደተናጠቀን ማየት ተገቢ ነው።
በጠብመንጃ ኃይል ስልጣን መያዝ ብቻ ሳይሆን ጠብመንጃ የወለደውን ስልጣን ለማስጠበቅ ሀገር እንደሀገር የከፈለችውን ዋጋ፤ በዚህ ሂደት ሕዝባችን ሰላማዊ በሚመስል የፖለቲካ ምእራፍ ውስጥ ያሳለፈውን የመከራ እና የግዞት ሕይወት ማጤን ፤ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ ያለውን እና የነበረውን ሀገራዊ የፖለቲካ ስብራት መገንዘብ ፤ ተስፋ ያደርግናቸውን ብሩህ ነገዎች ተጨባጭ ለማድረግ ወሳኝ ነው።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ይህ ሀገራዊ የፖለቲካ ስብራት እያስከፈለን ያለውን ያልተገባ ዋጋ ከሁሉም በላይ የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ የሆነው ሕዝባችን ጊዜ ወስዶ በሰከነ መንፈስ ሊመረምረው ፤ጠብመንጃ የወለደው ሆነ ሊወልደው የሚችለው የፖለቲካ ስልጣን መቼም ቢሆን ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ጥያቄው መልስ ሊያመጣ እንደማይችል ሊረዳው ይገባል፡፡
ከዚህ መረዳት በመነሳትም አሁን ላይ ጠብመንጃ አንስተው የዕለት ተዕለት ሕይወቱን /ዛሬውን ብቻ ሳይሆን ነገዎቹን እያበላሹ ያሉ ኃይሎችን በቃችሁ ሊላቸው እና ባለው አቅም ሁሉ ሊታገላቸው ይገባል። ይህን ማድረግ የራሱን ብቻ ሳይሆን የመጪዎቹን ትውልዶች እጣ ፈንታ የማስተካከል፤ የሀገርን መጪ ዘመን ብሩህ የማድረግ መሠረት ነው!
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም