ሩሲያ ለዩክሬን ሲዋጉ ተይዘዋል ያለቻቸውን የ72 ዓመት አሜሪካዊ በእስር ቀጣች

ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ሲሳተፉ ተይዘዋል ያለቻቸውን አሜሪካዊ አዛውንት በእስራት ቀጣች። የ72 ዓመቱ ስቴፈን ሁባርድ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት እንደተጀመረ ወደ ኬቭ ቅጥረኛ ወታደር ሆነው ለመዝመት መመዝገባቸው ተገልጿል። ጦርነቱ ከተጀመረ (የካቲት 2022) ከሁለት ወራት በኋላም ከዩክሬን ጦር ጋር ጎን ተሰልፈው ሲጓዙ በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው የተባለው።

የሩሲያ ፍርድ ቤት ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎትም የ72 ዓመቱን አዛውንት በስድስት ዓመት ከ10 ወራት እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ማሳለፉ ተዘግቧል። የሚቺጋን ነዋሪው ሁባርድ በዩክሬን ጦርነት በቅጥረኛ ወታደርነት ሲሳተፉ ተማርከው በእስራት የተቀጡ የመጀመሪያው አሜሪካዊ ሆነዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር፣ ሩሲያ ሁባርድ ህጋዊ ድጋፍ እንዲያገኙ አልፈቀደችም ሲሉ ወቅሰዋል። የእስራት ቅጣት የተላለፈባቸውን የዜጋቸውን ጉዳት በቅርበት ለመከታተል የሚደረገው ጥረት ግን እንደማይቋረጥ ነው ያነሱት።

አሜሪካዊው የ72 ዓመት አዛውንት የቀረበባቸው ክስ እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራት የሚያስቀጣቸው ነበር ተብሏል። ይሁን እንጂ የእድሜያቸው መግፋት ቅጣቱ እንዲቀንስላቸው ማድረጉን ጉዳዩን የያዙ የህግ ባለሙያዎችን በመጥቀስ የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሞስኮ በቁጥጥር ስር የምታውላቸው የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ይህም በአሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት በቁጥጥር ስር የሚገኙ ዜጎቿን ለማስመለስ እንደ ዋነኛ መደራደሪያ ሊያገለግላት እንደሚችል ነው የተገለጸው ሲል አል ዐይን ዘግቧል።

አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You