ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት በተፈጸመው የሩዋንዳ ዘር ፍጅት የሁቱ መንግሥት በነበረው ተሳትፎ ላይ ጥያቄ ያነሱት ፈረንሳዊ-ካሜሩናዊ ጸሐፊ ቻርለስ ኦናና ፓሪስ በሚገኝ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው። በ100 ቀናት ውስጥ ወደ 800 ሺህ የሚጠጉ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች ተገድለዋል።
ኦናና ከአምስት አመት በፊት ባሳተሙት መጽሐፋቸው የሁቱ መንግስት በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ማካሄዱን በእቅድ ፈጽሟል መባሉን “ባለፈው ክፍለ ዘመን ከታዩት ትልቅ ማጭበርበሮች አንዱ” ሲሉ ገልጸውታል። ኦናና የዘር ማጥፋት መፈጸሙን ወይም ደግሞ በተለይም ቱትሲዎች ዒላማ መሆናቸውን ጥያቄ ውስጥ አልከተቱም ሲሉ ጠበቃቸው ኢማኑኤል ፒር አጥብቀው ተናግረዋል።
ፒር ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና አውታር እንደገለጹት ከሆነ “በፖለቲካ ሳይንስ የ10 ዓመታት ጥናት ላይ የተመሰረተ እና የዘር ማጥፋቱ ከመፈጸሙ በፊት፣ በኋላ እና በወቅቱ ምን እንደነበረ ለመረዳት ያለመ” መጽሐፍ ብለዋል። የ60 ዓመቱ ኦናና እና የመጽሐፉ አታሚ የኤዲሽን ደ ቱካን ዲሬክተር ዴሚየን ሴሪየ ከአራት ዓመት በፊት በተመሳሳይ የመጽሐፍ ጉዳይ ተከሰው ነበር።
“በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸመውን ወንጀል በይፋ በመቃወም” በሚል በወቅቱ ክሱን ያቀረቡት መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሰርቪ እና የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ፌዴሬሽን (ኤፍአይዲኤች) ናቸው። የሩዋንዳን የዘር ማጥፋትን ከመካድ ጋር በተያያዘ በፈረንሳይ ፍርድ ቤት የታየ ሁለተኛው ጉዳይ ሆኗል። በፈረንሳይ ሕግ መሰረት ፈረንሳይ በይፋ እውቅና የሰጠችውን የዘር ማጥፋት መካድ ወይም “ማሳነስ” ወንጀል ነው።
ደራሲው ፍርድ ቤት መቆማቸው በተመለከተ “ከሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ጋር በተያያዘ እስካሁን ምንም ሕግ ባለመኖሩ ይህ ታሪካዊ ነው” ሲሉ የሰርቪ ሥራ አስኪያጅ ካሚል ሌሳፍሬ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
“በዋነኛነት ከሆሎኮስት ጋር የተገናኘውን የሕግ ጉዳይ መሰረት እናደርጋለን።” ብለዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እአአ በ 2021 ፈረንሳይ በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ላደረገችው ሚና ሩዋንዳውያን ይቅር እንዲሏቸው ጠይቀዋል። ፈረንሣይ ሊመጣ ስለነበረው የእልቂት ማስጠንቀቂያ እንዳልሰማች እና ለረዥም ጊዜ “እውነታውን ለመመርመር ዝምታን መርጣ ነበር” ቢሉም፤ ሀገራቸው የግድያው ተባባሪ እንዳልነበረች ግን አበክረው ገልጸዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም