የቡናው ዘርፍ ውጤታማ አፈጻጸም – ከልማት እስከ ውጭ ገበያ መላክ

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በሻይ፣ በቡናና ቅመማቅመም ምርቶች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ ከልማት ጀምሮ እስከ ለውጭ ገበያ /ኤክስፖርት/ ማቅረብና ገበያ ማስፋፋት ድረስ ትርጉም ያለው ሥራ እየሰራ ይገኛል:: በተለይም የእሴት ሰንሰለቱን በመከተል ልማቱ እንዲጨምርና ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ የገበያ መዳረሻዎች እንዲሰፉና የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ እንዲያድግ በብዙ እየተጋ ስለመሆኑ እያስመዘገበ ያለው ውጤት ይመስክራል::

ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ከተመረቱ በኋላ ጥራታቸውን ጠብቀው ለገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ በኩልም በትኩረት ይሰራል:: ለእዚህም የምርት ጥራትን በማስጠበቅና ብክነትን በመከላከል ምርቱ በተሻለ መልኩ ለገበያ እንዲቀርብና የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኝ ይደረጋል:: ከዚህ ጋር በተያያዘ በእሴት ጭመራ ላይም በትጋት በመስራት ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ቡና ምርት ማሳደግና ከቡናው የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማሳደግ ተችሏል:: የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት የአገር ውስጥ ገበያውን ጨምሮ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ምርት በማሳደግ የኢትዮጵያን ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ በማስተዋወቅ ሰፋፊ ሥራዎችን ተሰርተዋል::

ባለስልጣኑ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በዋናነት ከሰራቸው መካከል ግብይቱን አንቀው የያዙና ልማቱ ውስጥ የሚገኙ እንዲሁም ግብይት ውስጥ ያሉና ልማቱ እንዳይስፋፋ ያደረጉ ችግሮችን ነቅሶ ማውጣት አንዱ ነው:: ለዚህም የ15 ዓመት ስትራቴጂ በማዘጋጀት በዋናነት ስድስት የተለያዩ ምሰሶዎችን ለይቶ ልማትና ግብይቱን የማሳደግ ሥራ ሰርቷል:: ምርትና ምርታማነት ከፍ እንዲል፣ የምርት ጥራት እንዲጨምርና ዘርፉ በምርምር እንዲደገፍ፣ የእሴት ሰንሰለቱን በማሳጠርና በምርቱ ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ እንዲሁም ገበያን የማስፋፋት ሥራ በስፋት እንደሰራና አሁንም እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባላስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶክተር) በተለይ ለኢፕድ ሰሞኑን አስታውቀዋል::

ባለስልጣኑ ባደረገው ሪፎርም በተለይም የቡናው ዘርፉ ከዓመት ዓመት የተሻለ ውጤትና ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ይጠቅሳሉ:: ወደ ውጭ የሚላኩ የቡና፣ የሻይና የቅመማ ቅመም ምርቶች በመጠን እየጨመሩ፣ ከእነዚህ ምርቶች የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝትም በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ በ2016 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ 300ሺ ቶን ቡና ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች:: ይህ ውጤትና ስኬት የተመዘገበው በብዙ ጥረትና በሪፎርም ሥራ ነው:: ውጤትና ስኬቱ የተገኘውም የተለያዩ ተግባሮች መከናወናቸውን ተከትሎ ነው:: አንደኛውና ቀዳሚው ሥራም የገበያ ሰንሰለቱን ማሳጠር ነው:: አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን ለአቅራቢዎች እንዲሁም አቅራቢዎች ለላኪዎች ማቅረብ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ነው::

ይህም በመሀል የሚባክነውን ምርት እንዲሁም ይታይ የነበረውን የምርት ጥራት ጉድለት መቀነስ አስችሏል:: ከዚህ በተጨማሪም ምርቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአርሶ አደሩ በቀጥታ ላኪው ዘንድ መድረስ የሚችልበት አሰራር ተዘርግቷል::

አንድ ቡና ላኪ ኮንትራት ሲፈራረም በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ኮንትራቱን መፈጸም አለበት:: ይህ በ90 ቀናት ውስጥ ተፈጻሚ ካልሆነ ጊዜው ያልፍበታል:: ስለዚህ ይህ ኮንትራት ጊዜው እንዳያልፍበት ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ቡና አቅራቢውን እና ላኪውን በማስተሳሰር በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ቡና ለውጭ ገበያ መላክ እንዲችል ተደርጓል:: በዚህም የጊዜ ገደቡን ማሳጠርና የምርት ጥራትና መጠን እንዲጨምር በር መክፈት ተችሏል::

ሪፎርሙ ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ ከ180 እስከ 190 ሺ ቶን ቡና ብቻ ለውጭ ገበያ ይላክ እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰው፣ የሚላከው ቡና 200 ሺ ቶን እንኳ መግባት እንዳልተቻለ ተናግረዋል:: ባለስልጣኑ ተግባራዊ ባደረገው ሪፎርም ምክንያት በአሁኑ ወቅት እስከ 300 ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን አስታውቀዋል:: በአጭር ጊዜ ውስጥ መቶ ሺ ቶን የተጣራ ቅሽር ቡና ለውጭ ገበያ በሚላከው ቡና ላይ መጨመር ተችሏል ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህም ዘርፉ የእሴት ሰንሰለቱን በማሳጠር ያስመዘገበው ትልቅ ስኬትና ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል::

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ሌላው ኢትዮጵያ እንደ አገር ለገበያ የምታቀርባቸው የቡና አይነቶች ሁለት አይነት ናቸው:: እነሱም ኮሜርሻል እና ስፔሻሊቲ ቡና ይባላሉ:: ኮሜርሻል የሚባሉ ቡናዎች በመጠን ከፍ ያሉ፣ ነገር ግን በጥራት ዝቅ ያሉ ናቸው:: እነዚህ ቡናዎች በዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋቸው ዝቅ ያለና እንደ ሌሎች ሸቀጦች የሚታዩና በጨረታ የሚሸጡ ናቸው:: ይህ ቡና በጨረታ በሚሸጥበት ጊዜ ዋጋው ከብራዚል ቡና የሚወርድበትና ከዛም በላይ ከፍ የሚልበት ጊዜ አለ:: ይሁንና በአብዛኛው ከብራዚል ቡና በታች የሚሸጥበት አጋጣሚ አለ:: ስለዚህ ቡናን በኮሜርሻል ደረጃ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተወዳዳሪ አያደርግም::

ሁለተኛው የቡና አይነት ስፔሻሊቲ ቡና ሲሆን፤ ይህ የቡና አይነት በመጠን አነስ፣ በጥራት ከፍ ያለና የተሻለ ዋጋ ሊያስገኝ የሚችል የቡና አይነት ነው:: ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት አንድ ቶን ኮሜርሻል ቡና 2800 ዶላር ይሸጥ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተመሳሳይ ደግሞ አንድ ቶን ስፔሻሊቲ ቡና 5500 ዶላርና ከዛ በላይ ይሸጥ እንደነበር ገልጸዋል፤ የስፔሻሊቲ ቡና ዋጋ የኮሜሪሻሉን በእጥፍ ይበልጥ እንደነበር አስታውሰዋል::

ዋና ዳይሬክተሩ የኮሜርሻሉን መጠን በመቀነስ የስፔሻሊቲ ቡናን መጠን ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ መሰራቱንና በዚህም ውጤት ማምጣት እንደተቻለ አስታውቀዋል:: የዛሬ ሶስት ዓመት የኮሜርሻል ቡና መጠን በመቶኛ ሲታይ 70 በመቶውን ይሸፍን እንደነበር አስታውሰው፣ የስፔሻሊቲ ቡና መጠን ደግሞ 30 በመቶ እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል:: ዛሬ ላይ ግን የስፔሻሊቲ ቡናን ከፍ በማድረግ 60 በመቶ ማድረስ እንደተቻለና የኮሜርሻሉን ደግሞ ወደ 40 በመቶ ማውረድ መቻሉን ገልጸዋል::

የዛሬ ሶስት ዓመት የተገኘው ገቢም 700 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ጠቅሰው፣ ዛሬ ላይ ገቢው አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ገልጸዋል:: ይህም የቡና ጥራትና መጠንን ከማሳደግ ባለፈ ገቢውን ጭምር በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን እንደሚያሳይ አስታውቀዋል:: የጥራት ደረጃቸውን ከፍ በማድረግ ለዓለም ገበያ የተላከው የቡና አይነት አገሪቷ ከቡና ምርት የተሻለ ገቢ ማግኘት እንድትችል አስችሏታል ብለዋል::

የእሴት ሰንሰለት በማሳጠር እንዲሁም የጥራት ደረጃን በማሳደግ የተመዘገበው ውጤት ከፍ ያለ ስለመሆኑ ያነሱት ዋና ዳይሬከተሩ፤ ባለስልጣኑ ዘርፉን ለማሳደግና የውጭ ምንዛሪ ግኙቱን የተሻለ ለማድረግ ከሰራቸው የሪፎርም ሥራዎች መካከል በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች የኢትዮጵያ ቡናን በስፋት ለማስተዋወቅ የተከናወነው ተግባር ይገኝበታል ብለዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ስሙን ይዞ ከሌላ ቡና ጋር ሳይቀላቀል መሸጥ እንዲችል በመደረጉ ብሔራዊ ቡና በሚል ተዘጋጅቶ ገበያ ውስጥ መግባት ችሏል:: የኢትዮጵያ ቡና ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ገብቶ በራሱ ስም መሸጥ መቻሉ በራሱ አገሪቷ ከዘርፉ የተሻለ ገቢ እንድታገኝ አድርጓል::

ምርትና ምርታማነትን የማሳደጉን ስራ በምርምር እንዲደገፍ ማድረግ እንደተቻለ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለእዚህም ከምርምር ተቋማት ጋር መስራት መቻሉን ገልጸዋል:: የትኛው ዝርያ የትኛው ቦታ ላይ ውጤታማ ይሆናል በሚል በምርምር ዘርፍ በተከናወነው ተግባር ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል::

ለዚህም ሲባል የዛሬ ሶስትና አራት ዓመታት የተተከሉ ቡናዎች ባለፈው ዓመት ወደ ምርት መግባታቸውን ጠቅሰው፣ ዘንድሮ ደግሞ በስፋት ወደ ምርት እንደሚገቡ ጠቁመዋል:: የምርት መጠኑም ከዚህ ቀደም ከነበረበት ስድስት መቶ ሺ ሜትሪክ ቶን ወደ ዘጠኝ መቶ ሺ ሜትሪክ ቶን ከፍ ማለት መቻሉን ጠቅሰው፣ ዘንድሮ ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የቡና ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል::

ከምርምር ሥራው ጋር ተያይዞ ያረጁ ቡናዎችን በስፋት ማንሳት እንደተቻለና አዳዲስ ዝርያዎች ወደ ልማት እንዲገቡ መደረጉን የጠቀሱ ዋና ዳይሬክተሩ፤ የእነዚህ ሁሉ ሥራዎች ድምር ውጤት በ2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ቡና በስፋትና በጥራት ወደ ዓለም ገበያ እንዲገባና የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ተናግረዋል:: በ2017 በጀት ዓመት ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ውጤታማ መሆን የሚቻልበት ሰፊ ዕድል እንዳለም አመላክተዋል::

የኢትጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ለ2017 በጀት ዓመት ጥራት ያለውና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን የሚችል ቡና በከፍተኛ መጠን የመላክ ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል:: በ2016 በጀት ዓመት ሶስት መቶ ሺ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በመላክ ከተመዘገበው ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ከፍ በማድረግ፣ በ2017 በጀት ዓመት 326 /ሶስት መቶ ሃያ ስድስት/ ሺ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ባለስልጣኑ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል::

ባለፉት ሁለት ወራት ማለትም በሐምሌ እና ነሐሴ 56 ሺ ቶን ቡና በመላክ 260 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ባለስልጣኑ አቅዶ፣ 83 ሺ ቶን ቡና ወደ ውጭ ገበያ መላክ መቻሉንም ገልጸዋል፤ ከዚህም ከእቅዱ በላይ 380 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን አመልክተዋል:: ይህም ከዕቅድ አንጻር ሲታይ በመጠን ከ30 ሺ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ ገበያ መላክ የተቻለ መሆኑን አብራርተዋል:: ይህ በሁለት ወራት ውስጥ ከዕቅድ በላይ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑንም አመልክተዋል:: በቀጣዮቹ ወራት አሁን በተመዘገበው ውጤት ልክ ማስመዝገብ ከተቻለ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ማሳካት የሚከብድ አይደለም ብለዋል::

በአሁኑ ወቅትም የመስከረም ወር ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት እየቀሩት 22 ሺ ቶን ቡና ወደ ውጭ ገበያ በመላክ 90 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት እንደተቻለ ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀው፣ አሁን የተመዘገበው ውጤት ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በምርት መጠንም ሆነ በገቢ መጠን ሰፊ ልዩነት የተመዘገበበት መሆኑንም አብራርተዋል::

የገበያ መዳረሻዎችን አስመልክቶ ዋና ዳይሬክተሩ ሲያስረዱ እንዳመለከቱት፤ ኢትዮጵያ ቡናን ለአምስት ትላልቅ አገራት በስፋት ታቀርባለች:: ሀገራቱም አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ቤልጅየም፣ ጀርመንና ሳዑዲ አረቢያ ሲሆኑ፣ ሀገሮቹ የኢትዮጵያን ቡና በከፍተኛ መጠን ይገዛሉ:: በሁለት ወራት ውስጥ ያለው የገበያ መረጃ የሚያሳየው ደግሞ ጀርመን 20 በመቶ ያህሉን የኢትዮጵያ ቡና በመግዛት ቀዳሚ አገር እንደሆነች ነው::

በአሁኑ ወቅትም ከጀርመን በመከተል ጃፓን፣ ደቡብ ኮርያ፣ ቻይናና ቤልጅየምም እንዲሁ የኢትጵያን ቡና በመግዛት ወደ ቀዳሚዎቹ ተርታ እየመጡ ናቸው:: ደቡብ ኮርያና ቻይና አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎች ሲሆኑ፣ በእነሱ ላይ በስፋት እየተሰራ ነው:: በተለይም ቻይና የኢትዮጵያን ቡና በመጠቀም በጣም በፍጥነት እየመጣች ያለች አገር እንደመሆኗ ይህንን ዕድል አሟጦ ለመጠቀምና አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎች ማፈላለግ ላይ በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል::

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም

Recommended For You