የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ውጤታማ ለማድረግ ቁልፍ ዓላማ ይዞ የተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም ነው። የኮንስትራክሽን ዘርፉ በዋጋ፤ በጥራት፤ በጊዜ እና በአካባቢ ደህንነት ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል ትልቅ ተልዕኮ ወስዶ እየሰራ ነው።
በዛሬው የተጠየቅ ዓምዳችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ፣ እያጋጠሙት ባሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ የባለሥልጣኑን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን ነገዎ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ክፍል ሁለት ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- በዘንድሮ በጀት ዓመት ለመስራት ያቀዳችኋቸው ዋና ዋና ተግባራት ምንድናቸው ?
ኢንጂነር መስፍን፡- የኮንክሪት ታይፕ ድሮ የምንጠቀምበት እና አሁን ያለን ስታንዳርድ አንድ አይደለም:: ያሉን ስታንዳርዶች ትልልቅ የሚባሉ ፕሮጀክቶችን ታሳቢ ያላደረጉ ናቸው:: ይሄንን ለማውጣት የሚደረገው ጥናት ከባድ ነው ፤ ስታንዳርዱን የጠበቀ እንዲሆንም ከሌላ ሀገራት ልምድ በመውሰድ የሚሰራ ነው::
ልምድ ስንወስድ ከእኛ የጂኦሎጂካል እና የጂኦግራፊ አቀማመጣችን ጋር፤ ከአየር ንብረት እና ካለው የንፋስ አቅም ጋር የሚሄድ ነው:: ምክንነቱም በእኛ ሀገር ከባድ ለሚባል ንፋስ ተጋላጭ አይደለንም:: ስለዚህ ሀገር ውስጥ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ‹‹ሞዲፋይ›› ይደረጋል:: እንደነዚህ አይነት ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በኢትዮጵያ ተጠንቶ መልመድ‹‹አዳብት›› ማድረግም ካለብን አድርገን ለአይሶ (ኢንተርናሽናል ሰታንዳርድ ኦርጋናይዜሽን) ማሳወቅ አለብን:: በእኛ የደረጃዎችን ምዝገባ መመዝገብ አለበት::
ሌላው የምንሰራው መስሪያ ቤቱ የሕንጻ አዋጅ እንጂ የኮንስትራክሽን አዋጅ የለውም:: ምን ማለት ነው? አዋጅ 624 የሕንጻ አዋጅ ነው:: ኮንስትራክሽን ማለት ደግሞ ከሕንጻ በላይ ነው:: ሕንፃ እና መሰረተ ልማትን እንዲሁም ሌሎችን ይጨምራል:: ማንኛውም ከምድር በታች እና ምድር ላይ የሚሰራ፤ የሚገጣጠም እና የሚተከል ነገር ሁሉ ኮንስትራክሽን ነው::
በዘርፍ ስንከፍለው ደግሞ የሕንጻ፤ የትራንስፖርት እና ኮምዩኒኬሽን፤ የኢነርጂ እና ውሃ በተጨማሪም የስፔሻል ዘርፍ ነው:: ይሄን ሁሉ ዘርፍ የሚይዝ አዋጅ ይፈልጋል:: አዋጁ ያስፈለገው ኮንትራክተሩ፤ ዕቃ አቅራቢው ሆነ ለሚመራው አካል የሕግ ማቀፍ ወይም ልጓም ስለሚያስፈልገው ነው:: ልክ እንደ ሕንፃ ኮንስራክሽን የራሱ አዋጅ ሊወጣለት ግድ ይላል:: ከአዋጅ በታች ደግሞ ደንብ ይኖራል::
አሁን የኮንስትራክሽን አዋጅ አዋጅ ሆኖ በሚመጣበት ጊዜ የሕንፃ አዋጅ ወደ ደንብ ይወርዳል:: መመሪያዎችም ይኖራሉ:: በየጊዜው መንግስት እየወሰነ የሚያስተላልፈው ሰርኩላሮችም ይኖራሉ:: ከዛ ደግሞ ማንዋል እና የአሰራር ስርዓቶች ይኖራሉ::
ይሄ እርግጠኛ ነኝ በ2017 ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ላይ ይጸድቃል:: እሱም ከፀደቀ ለእኛ በተለይ ቁጥጥር በማድረግ ተጠያቂ ለማድረግ ያግዘናል:: በጣም የምንቸገረው በደምብ እንድንቆጣጠር ስልጣን ተሰጥቶን አዋጅ ላይ ግን የለም:: ደምብ ደግሞ አዋጅን መሻር ስለማይችል ይሄንን እንዲቀርፍልን 2017 ዓ.ም ትልቁ የያዝነው የእቅድ ስራ ነው::
ሌላው ‹‹ሴፍቲ ፋክተር›› የሚባል አለ:: የእኛ ስታንዳርድ ከአውሮፓውያን እጥፍ ነው:: ለምንድን ነው የእኛን እጥፍ የሆነው ከተባለ ‹‹የወርክ ማንሺፓችን›› ደካማ ስለሆነ ነው:: አሁን ግን በዛ መሄድ የለብንም:: ኢንጂነሪንግ ማለት ደህንነት ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚም ነው:: ገንዘብ መቆጠብ አለበት:: አላስፈላጊ ኮንክሪት መጠፍጠፍ ኢኮኖሚያዊ የሆነ አካሄድ አይደለም::
እንደነዚህ አይነት አካሄዶች የጥናቱ አንድ አካል ናቸው:: ጥናቱ የሚጠናው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን ነው:: ይሄም አንዱ የኢንዱስትሪያል ሞደርናይዜሽን አካል ነው:: ከውጪ የሚመጡ የኢንዱስትሪው ካንፓኒዎች የእኛን አሁን ኋላ ቀር ነው የሚሉት በዚህ በዚህ ምክንያት ነው::
በዘንድሮ ዓመት የምንሰራው ሌላው ስራ እኛ ሀገር የሌለ ዲዛይን ኤንድ ቢዩልድ (ዲ.ቢ) የሚባል በስፋት እየተተገበረ የሚገኝ ስታንዳርድ አለ:: በእኛ ሀገር ግን ይህ ስታንዳርድ ቢል ዶክመንት የለውም:: ዘንድሮ ግን ወደ ስራ ይገባል::
ከዚህ ጋር ተያይዞ ንግድ ባንክ ትልቅ ችግር ነበረበት:: የቻይና መንግስት ትልቁ ሰው መጥቶ እስከሚፈታ ድረስ ትልቅ ውዝግብ ነበር:: የተዋዋሉት በኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን ኦፍ ኮንስትራክሽን ስታንዳርድ ነበር፤ ከእኛ ጋር ደግሞ ሕጋዊ መሰረት የለውም:: ክስ ከተነሳ ክስ የሚፈጸመው በኢንተርናሽናል ኮርት ፍርድ ቤት ነው:: ስለዚህ አሁን እንደምናደርገው የራሳችን ናሽናል የዲ.ዲ ሞዳሊቲ ይኖራል::
ወደ ሰባት አይነት ‹‹ተርም ኪ ሞዳሊቲዮች›› አሉ:: እነሱን ስታንዳርድ ሰጥተን የእራሳችን አድርገን ኢንዱስትሪው በሚመቸው መልኩ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የምናለማ ይሆናል::
አሁን ቱሉ ቦሎ ጂኦ ተርማል ዲዛይናቸውን አፅድቁልን ብለው መጡ:: እኛ እንዴት እናፅድቅ? ስታንዳርዱ የለንም:: ከአፍሪካ እራሱን ፈልገን አጣን:: እንደዚህ አይነት ጉዳይ ሲያጋጥመን ያደረግነው አማካሪው (ኮንሰልታንቱ) የኦስትሪያ ሀገር ነው:: የኦስትሪያ ሀገርን ወስደን የእነሱ በአፍሪካ ሕብረት የጸደቀ ስለሆነ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት አለው:: እሱን ወስደን የሚመጣውን ኪሳራ ወደነሱ አዘዋወርን:: ‹‹ፌል›› ቢያደርግ እነሱ ተጠያቂ ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- የኮንስትራክሽን ባለስልጣንና የግንባታ ቁጥጥር ባለስልጣን አንድ አይነት የሚመስሉ ስራዎችን የሚሰሩ ይመስላሉ ፤ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለው ልዩነት ምንድ ነው?
ኢንጂነር መስፍን፡- በኮንስትራክሽን ባለስልጣን እና በግንባታ ቁጥጥር ባለስልጣን መካከል ግልጽ የሆነ የስልጣን እና ኃላፊነት ልዩነት አለ:: ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ስንል በፌደራል መንግስት ደረጃ የተቋቋመ ነው:: ግንባታ ቁጥጥር ባለስልጣን ብዙ ጊዜ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች የሚገኝ ተቋም ነው:: ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማን አስተዳደር ብንወስድ በከተማ አስተዳደሩ የሚከናወኑ ማንኛውንም አይነት የግንባታ ተግባራትን የሚቆጣጠረው የግንባታ ቁጥጥር ባለስልጣን ነው:: በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ የፌዴራል ይሁን የሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያከናውኗቸውን ግንባታዎች ጭምር የሚቆጣጠረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ቁጥጥር ባለስልጣን ነው::
ይሁን እንጂ የፌደራል ተቋማት ግንባታ በሚከናወንበት ሰዓት ምንም እንኳን የግንባታ ቁጥጥር ስራውን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ቁጥጥር ባለስልጣን ቢከናወንም የዲዛይን ክለሳ ስራውን ግን የሚያከናውነው በኮንስትራክሽን ባለስልጣን ነው::
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚከናወኑ ግንባታዎችን የሚቆጣጣረው የአዲስ አበባ ከተማ የግንባታና ቁጥጥር ባለስልጣን ቢሆንም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ማረጋጋጫ እስካልሰጠ ድረስ የገንዘብ ሚኒስቴር በጀት አይለቅም:: ይህ ማለት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን አንደኛ ጥራት ያረጋግጣል:: ሁለተኛ ጥራቱ በበቂ ደረጃ ለተከናወነ ግንባታ ደግሞ በጀት እንዲለቀቅ የማድረግ ስራ ይሰራል::
በተጨማሪም አዲስ አበባ ክልል ውስጥ ለሚከናወን ማንኛውም ግንባታ የአዲስ አበባ ከተማ የግንባታና ቁጥጥር ባለስልጣን የግንባታ ፈቃድ ይሰጣል:: የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሰልጣን የግንባታ ፈቃድ አይሰጥም::
በአዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኙ የግለሰቦችን የግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር የሚያደርገው የአዲስ አበባ ከተማ የግንባታና ቁጥጥር ባለስልጣን ቢሆንም በግለሰቦች በኩል ቅሬታ ከመጣ የተነሳውን ቅሬታ ለመፍታት በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ጣልቃ ሊገባ ይችላል::
ለምሳሌ አዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ፈቃድ እና ማረጋገጫ ሰጥቶት የተገነባ አንድ ሕንፃ ቢደረመስ አዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ራሱን ተጠያቂ ሊያርግ አይችልም:: በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን የጥራት ምርመራ ያደርጋል::
ቅሬታ ባይመጣም እንኳን ኮንስትራክሽን ባለስልጣን በድንገት ያልታሰበ ኢንስፔክሽን ስራ ያከናውናል:: በዚህም ድንገተኛ ኢንስፔክሽን በእያንዳንዱ የሕንጻ ክፍል በመግባት የግንባታ ዲዛይኖቹን ወስደን ፈቃድ የተሰጠው የኢትዮጵያን ስታንዳርድ አሟልቶ ነው? የሚለውን የመቆጣጠር ስራ ይሰራል:: ምክንያቱም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እንደ ሀገር የራሱ የሆነ ስታንዳርድ አለው::
በእርግጥ የቤት ቁመት እንደሀገር ባለን ስታንዳርድ አይለካም:: ለምሳሌ ሰመራ እና አዲስ አበባ የሚኖረው የግድግዳ ርዝመት ስታንዳርድ አንድ ሊሆን አይችልም:: ስለሆነም የቤት ቁመት እንደየ አካባቢው የአየር ንብረት የሚወሰን ይሆናል:: ይሁን እንጂ እንደሀገር የሚወጡ ስታንዳርዶች አሉ:: በሀገር አቀፉ ደረጃ የኮንስትራክሽን ዘርፍ አስራ አራት መመዘኛ መስፈርቶች አሉት፤ አዲስ አበባም ሆነ ሰመራ መጣስ የማይችሉት፤ እኛም ልንጥሰው የማንችለው ዓለም አቀፋዊ ደረጃዎች አሉ::
ከዚህ አንጻር የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሰዎች በሆቴሎቻችን ውስጥ የሚተኙት የአይሶን ስታንዳርድ በመተማመን ነው:: የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አንዱ የአይሶ ደረጃ አባል ነው:: ዓለም አቀፋዊ ደረጃዎችን ጠብቆ የሚሰራው ነው ብለው ስለሚያምኑን ነው:: ይህ ባይሆን ኖሮ አንዳንድ የእርሻ ምርቶቻችን ደረጃውን አላሟላም ብለው እንደሚመልሱ ሁሉ በሆቴሎቻችንም ውስጥ አይተኙም ነበር::
በአጠቃላይ በግንባታና ቁጥጥር ባለስልጣን እና በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሰልጣን መካከል ከፍተኛ የሆነ የኃለፊነት እና የስልጣን ልዩነት መኖሩን መገንዘብ ይገባል::
አዲስ ዘመን፡- በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የግንባታ ጥራት ጉድለት እንዳለ ቅሬታ ይነሳል:: ከዚህ አንጻር ባለስልጣኑ የሕንጻዎችን ጥራትና ደህንነት ከመቆጣጠር አኳያ ምን ሰርቷል፤ እየሰራነው?
ኢንጂነር መስፍን፡– ጥያቄው ጥሩ ነው፤ ግን ከባድም ነው:: ጥያቄው ከባድ ቢሆንም ለመመለስ ያህል ግን የእኛ መስሪያ ቤት ከተቋቋመ በኋላ የተሰራ ኮንዶምንየም የለም:: ነገር ግን የእኛ መስሪያ ቤት ከመመስረቱ በፊትም ሆነ በኋላ እየተገነቡ ያሉት ሪል ስቴቶች ናቸው:: ለዘርፉ ፈቃድ የሚሰጠው ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ የግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ነው:: ይህም ሆኖ ግን እስካሁን በጥራት ችግር ሳቢያ ወድቋል ተብሎ ሪፖርት የመጣ ሪል ስቴት የለም:: በእርግጥ ባለፈው ልደታ አካባቢ የአንድ ጅምር ሕንጻ ሁለት ኮለን የወደቀበት ሪል ስቴት ነበር:: እሱንም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጣልቃ ገብቶ ሁኔታውን አጣርቶታል:: ዲዛይኑንም እንደገና አሻሽለውታል:: ግን አሁንም ጥብቅ ቁጥጥር ይፈልጋል::
እኔ እራሴ የምኖርበት መንግስት የሰጠኝ 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት የጥራት ችግር አለበት:: በዚህም በጣም አዝናለሁ:: አንዳዶቹ ቤቶች ላይ ከላይ ቤት ሲያጥቡ ከታች ውሃ ይፈሳል:: ጉራጌ አካባቢ የተሰሩ ሳር ቤቶች ከላይ ልብስ ቢታጠብ ውሃ አያፈሱም:: ነገር ግን ከሕንጻዎቻችን ጋር ተያይዞ ከመሬት በታች ያሉ ስራዎች ብዙ ጉድለቶች ይታዩቧቸዋል:: ከሕንጻ ጋር በተገናኘ ስብራቶቻችን ብዙ ናቸው::
የጋራ መኖሪያ ቤት መኖሩ ለድሃው የሕብረተሰብ ክፍል ጥሩ ሆኖ ሳለ የጥራት ጉድለቱ ግን ዘግናኝ ነው:: ይህን ችግር ለመፍታት በ10 ዓመቱ ዕቅድ ላይ ለፍተሻ የሚያገለግሉ 10 ቦታዎች ላይ ላብራቶሪዎችን ለማቋቋም እየተሰራ ነው:: ይህ ተፈቅዶ ስራ ሲጀምር ቁጥጥሩ ይዘምናል:: አሰራሩ የሕንጻ ሹም ካላቸው ከተሞች ጋር ይተሳሰራል:: በዚህ አሰራር በሩቅ ቦታ ላይ የሚገኝ አንድ ሕንጻ ለመገንባት ፍቃድ ያገኘ ግለሰብ ስለሚያከናቸው አጠቃላይ የግንባታ እንቅስቃሴዎች ቢሯችን ቁጭ ብለን መቆጣጠር እንችላልን::
በ10 ዓመቱ ዕቅድ ላይ ያስቀመጥነውን ለፍተሻ የሚያገለግሉ ላብራቶሪዎችን ስናቋቁም የሕንጸዎችን የጥራት ደረጃ የምንለካበት ‹‹ስካን›› የሚያደርግ መሳሪያ ይኖረናል:: ሕንጻው ከመሰራቱ በፊት ደግሞ የጥራት አንሹራንስ ሲስተም እንዲኖረው ይደረጋል:: ባለሙያው ኃላፊነቱን ወስዶ እያረጋገጠ መረጃ እንዲይዝ እና የተያዘው መረጃ ሪከርድ እንዲደረግ ያግዛል::
አሁን ላይ እኛ ባደረግነው ምልከታ እና ምርምራ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሕንጻ የነበረ ጂ+3 የሆነ አራት ብሎክ አስፈርሰናል:: አራት ኪሎ አካባቢ የነበረ የተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት ጀምሮ የነበረው አንድ ሕንጻ ‹‹ስትራክቸሩ›› ካለቀ በኋላ የጥራት ችግር ገጥሞት ነበር:: ይህን የጥራት ችግር ማወቅ የተቻለው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባደረገው ምርመራ ነው:: ከምርምራው በኋላ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሕንጻውን ችግር መቅረፍ ተችሏል::
በነገራችን ላይ የማንኛው የጥራት ችግር የኢንጂነሪንግ መፍትሔ አለው:: ማንኛውም የጥራት ችግር ግማሹን ኬሚካሎችን ተጠቅሞ ማስተካለል የሚቻል ሲሆን ግማሹ ደግሞ በጥራት ኦዲት ይስተካከላል:: አዲስ አበባ ላይ ባለሙያዎቻችንን አሰማርተን ብናስፈትሽ በእርግጠኝነት በበርካታ ሕንጻዎች ላይ ከፍተኛ ችግር ይገኛል:: ምልክቱ የሚያሳየን ይህን ነው::
አዲስ ዘመን፡- በእናንተ ግምገማና ግኝት ብዙ ሕንጻዎች የጥራት ችግር እንዳለባቸው አመላካች ነገሮች እንዳለ ገልጸዋልና ይህ ክፍተት ከምን የመነጨ ነው? እዴትስ ይቀረፋል?
ኢንጂነር መስፍን፡– የእኛ መስሪያ ቤት የተቋቋመበት ዋና ምክንያት በዘርፉ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ታስቦ ነው:: ችግሩ አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን ዘመን ችግሩን በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ነበር ለመፍታት የሞከሩት፤ ግን ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም:: አሁንም ችግሩ እየከፋ ሲሄድ፤ በተለይም ኮንደሚኒየሞች ላይ እንደዚህ አይነት ጥናቶች እራሳቸውን እየገለጡ ሲመጡ ለዘርፉ ለብቻው ተቆጣጣሪ ባለስልጣን አስፈለገው:: ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከመቋቋሙ በፊት ኢንዱስትሪው ሁለት ተጫዋቾች ያለ ዳኛ የሚጫወትበት ሜዳ ነበር:: ስለዚህ ዳኛ ይፈልጋል::
ይሁን እንጂ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለበት የበጀት ችግር የተነሳ በዓመት በእቅድ ከሚገነቡ ከሁለት ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ውስጥ ምርመራ እና ክትትል ማድረግ የተቻለው ከ120 እስከ 130 የሚደርሱ ፕሮጀክቶችን ብቻ ነው:: ይህ የሚያመላክተው መታየት እና ምርምራ መደረግ የነበረባቸው ግንባታዎች ላይ የቁጥጥር ክፍተት እንዳለ ነው::
በዚህ አካሄድ ሁለት ሺህ ፕሮጀክቶች ቁጥጥር የመደረግ እድል የሚያገኙት በሶስተኛው ዓመት ወይም ከዚያ በላይ በፈጀ ጊዜ ውስጥ ነው:: ግንባታው ከተጀመረ በሶስተኛ ዓመቱ ላይ ሰንደርስ ምንአልባትም ሕንጻው ተጠናቆ ቀለም ሊቀባ ይችላል:: ስለዚህ ቁጥጥሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊደረግ ይገባል:: ይህም ሊደረስ የሚችልን ጉዳት ይቀንሳል፤ ያስቀራልም:: በግንባታ ላይ ጥቃቅን የሚመስሉ ግን ትልቅ ችግር የሚፈጥሩ ስህተቶች አሉ:: እነዚህን ችግሮች መቅረፍ ያስችላል::
የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት ሰው ሳይጎዳ ሰውን በሕይወት ለማትረፍ የሚያስችል የሕንጻ አሰራር አለ:: ይህን እዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል:: ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ከቦሌ ቡልቡላ የተሰማ እስከ ሁለት ነጥብ ሶስት ሬክተር ስኬል የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ነበር:: በዚህ ጊዜ ሰውን ሳይጎዳ ቶሎ እዲወጣ ማድረግ የሚያስችል የሕንጻ ጥራት ሊኖር ያስፈልጋል:: ካለው የሰው ኃይል አንፃር ሲታይ እና ካለው የፕሮጀከት ብዛት አኳያ አንድ መቶ ፐርሰንት ተደራሽ እየሆነ ይሰራል ብዬ አላምንም::
አዲስ ዘመን፡- የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምን ያህል ጥራት አላቸው? እነዚህ ቤቶች ችግር እንዳያደርሱ ከመከላከል አንጸር ምን እየሰራችሁ ነው?
ኢንጂነር መስፍን፡– ማንኛውም የኢንጅነሪንግ ችግር የራሱ መፍትሄ አለው:: የኢንጂነሪንግ ምልክቶች ተገምግመው እስካልፈረሱና ይፍረሱ እስካልተባለ ድረስ መፍትሄ አላቸው:: በዚያ መሰረት ችግሮች ይቀረፋሉ:: ነገር ግን ሀገራችን የምትከተለው የፌዴራሊዝም ስርዓት በመሆኑ አዲስ አበባ ላይ ሄደን ማስገደድ አንችልም:: እናስገድድ ብንል እንኳን በከተማዋ ካለው የቤት ችግር አንጻር ጦርነት ይፈጠራል:: አዳማ ሄጄ ላስገድድ ብልም የሚፈጠረው ተመሳሳይ ችግር ነው::
በነገራችን ላይ የጥራት ስራ የሚጀምረው ከመረጃ ላይ ነው:: መደረግ ያለበት ሂደት ተከትሎ ነው ዲዛይን የተደረገው? የትኛውን የግንባታ ዘዴ ነው የተጠቀመው? ወዘተ የሚሉት መረጃዎች ይሰበሰባሉ:: ከመረጃው ስብሰባ በኋላ ሌሎች ቴክኒካል ምርመራዎች ይደረጋል:: ለአንድ ሕንጻ ይህን ምርመራ ለማድረግ በርካታ ቀናትን ይወስዳል:: ከፍተኛ ጉልበት እና የገንዘብ ወጭንም ይጠይቃል::
በነገራችን ላይ አንድ ሕንጻ ሲገነባ ሁለት ሺህ የሚሆኑ የስራ አይነቶች አሉት:: የመንገድ ስራ ደግሞ በጣም ጥቂት ስራዎችን የያዘ ነው:: ስለዚህ የአንድን ሕንጻ ግንባታ ቁጥጥር ለማድረግ እጅግ ፈታኝ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ ከተቋራጮች ጋር በተያያዘ ምን ችግሮች አጋጠሙት? ችግሮችን ለመፍታት የሄደበት መንገድ ምን ይመስላል?
ኢንጂነር መስፍን፡– ከተቋራጭ ጋር የገጠመን በጣም ሰፊ ችግር ነው:: አንደኛ ተቋም ናቸው ብሎ መናገር ይከብዳል:: በእናንተ ዕድሜ ስንት ተቋራጭ ነበሩ? የኮስትራክሽን ድርጅቶች አሁን ላይ ከፍተኛ ቢሊዮን ብር እያንቀሳቀሱ አቅማቸው ግን ዝቅተኛ ነው:: እየተደበደብን ያለነው እነሱ በሰሩት ሀጢያት ነው:: መንገድ ሆነ ሕንጻ ሲገነቡ የነበሩት እነዚህ ተቋማት ናቸው::
ፕሮጀክቶቹን አስይዘው ከባንክ ተበድረውበታል:: በአዲሱ አደረጃጀታችን ደረጃ ይሰጣቸዋል:: በሰው ኃይል፤ በፋይናንስ፤ አደረጃጀትና በአቅም ማደራጀት አስፈላጊ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ከተማችን ላይ በርካታ ሕንጻዎች ውበት እንደሌላቸው በብዙዎች ዘንድ ይነገራል የናንተ ተቋም ሕንጻዎቹ ውበት እንዲኖራቸው የምታደርጉት ቁጥጥር አለ?
ኢንጂነር መስፍን፡- ውበት እንደ ባለቤቱ ነው:: ውብት ሲባል እንደ ተመልካቹ ይወሰናል:: ለአንዱ ቆንጆ የሆነ ለሌላ አካል ውብ ላይሆን ይችላል:: ቻይናዎች ሕንጻቸው የሚሰሩበት መንገድ ልዩ ነው:: ትናንሽ ነገር በመጨምር ያሳምራሉ:: እኛ ሀገር ላይ በረንዳው ወይም ኮሊደሩ በዝቶ ይታያል:: እማንጠቀመው ነገር ግን ለውበት ብቻ ዋጋ የወጣባቸው ነገሮች ይበዛሉ::
ወደ ውበት ከመጣን ዲዛይን አስተዳደር የሚባል ቢሮ አለ፤ እሱ በትምህርት ቤት በኩል ቢሰራ መልካም ነው:: ስለዚህ እኛ የምንለው ተግባራዊ ይሁን የሚል ነው:: ቦታ ኢኮኖሚ ይሁን ነው:: ሌላው ደግሞ በማስተር ፕላን የኮሪደር ልማቱ ያመጣው አንድ አዲስ አሰራር አለ:: ለምሳሌ ድሬዳዋ የራሷ የሆነ የክሬም ቀለም ኮድ ነበራት:: ይህን ያስተዋወቁት ፈረንሳዮች ነበሩ፤ ነገር ግን መሃል ላይ ተበላሸ እና ተዝረከረከ እንጂ አንድ አይነት ቀለም ሕንጻዎች ይቀቡ ነበር::
አዲስ አበባም ነበራት ግን ተግባራዊ ሆኖ አያውቅም:: አዲስ አበባ 10 ማስተር ፕላን አስተናግዳለች፤ 10ሩም የቀለም ኮድ አላቸው:: ዘጠኙ አልተተገበሩም:: አስረኛው ዕድለኛ ሆኖ እየተተገበረ ነው:: አሁን ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ማስተር ፕላኑ ነው:: የኮሪደር ልማቱና የከተማ ማዕከልነት ስራው የማስተር ፕላኑ አካል ነው:: አሁን የተጀመረው የቀለም አይነት ውበት ያመጣል:: ቀለም በማህበረሰብ ባህሪ፤ አኗኗር ውስጥ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው::
አዲስ ዘመን፡- ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በሚያጓትቱ እና በአግባቡ በማይሰሩ የኮንስትራክሽን ተቋማት ላይ ምን አይነት እርምጃ እየወሰዳችሁ ነው?
ኢንጂነር መስፍን፡– ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መጀመሪያ ሲቋቋም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ተብሎ ነበር:: ከኮንትራክሽን ሚኒስቴር ወደ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ስንመጣ ከተሰጠን ኃላፊነት ውስጥ እርምጃ ይወስዳል የምትል አንቀጽ የለችም:: የመጀመሪያ ቁጥጥራችን ላይ ፈልገን ነበረ:: ግን በሁለተኛው ሪፎርም ባለፈው ዓመት ላይ ነው የፀደቀልን:: የዚያን ጊዜ ነው እርምጃ እንደምንወስድ እና ‹‹ላይሰንስ›› እንደምንቀማ የተሰጠን::
አሁን ላይ ባለው ሁኔታ ኮንትራክተሮች ስራ የላቸውም:: ሁለተኛ ደግሞ ‹‹ኮምፒቲሽኑን›› መቋቋም አልቻሉም:: በሌላ በኩል ግብአት የለም:: ለምሳሌ ሲሚንቶ ማግኘት በጣም ከባድ ነው:: ብዙዎቹ ቁጥጥር የምናደርግባቸው ሲሚንቶ አምጣ ‹‹ኦቨር ናይት›› እሰራልሃለሁ ይላል:: የፕሮጀክቱ ባለቤት ይህን ይለያል:: የፕሮጀክት ባለቤቱ ለይቶ አማካሪው ከለየ በኋላ ተጠያቂ ላድርግ ብትል ፍርድ ቤት ይሄዳል:: ይህ ተጠያቂ ያደርገናል:: በአሁኑ ሰዓት እርምጃ ለመውሰድ ተቸግረናል::
አዲስ ዘመን፡- ወደፊትስ በዚህ መልኩ መቀጠል አለበት ይላሉ ?
ኢንጂነር መስፍን፡– ደንቡ ሲጸድቅ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የሰጡት መመሪያ በሕዝብ እና በሀገር ገንዘብ ላይ የሚጫወት የትኛውም ካንፓኒ እንዲቀጥል አንፈቅድም የሚል ነው:: በበሰለ ሁኔታ የተወሰነ ካምፓኒ እርምጃ ብንወስድ እርግጠኛ ነኝ ይስተካከላል:: ኢንዱስትሪው ደንጋጣ ነው:: በውል እና በወረቀት የሚሰራ ስለሆነ እንደሌባ እና ፖሊስ ብዙ የተወሳሰበ አይደለም::
ወደ ፊት የዛሬ ዓመት በዚህ ሰዓት የምንጠብቀው ሁለት ጊዜ የተቆጣጠርነው ፕሮጀክት ግብረ መልስ ወስዶ የማያስተካክል ከሆነ ለተወሰነ ዓመት ከጨዋታው ውጭ እናደርገዋለን:: አሁን ከኢትዮጵያ ምግብና እና መድሃኒት ቁጥጥር ተሞክሮ የወሰድነው የተወሰነ የእገዳ ግዜ አላቸው:: ካላስተካከለ ግን ከኢንዱስትሪው ያስወጣሉ:: ስለዚህ እኛም እንደዚህ አይነት አካሄድ እንከተላለን::
መረጃ ቋቱ ከመጣ ግን እርግጠኛ ነኝ ፍላጎቱ ያለውን ሰው ሁሉ መደበቅም አይቻልም:: አንደኛ ‹‹ደህንነቱንና የአስተዳደሩን ስራ›› የምንሰጠው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ነው:: ሁለተኛ ተደራሽነቱ ጋዜጠኞችም መጠየቅ አያስፈልጋቸውም:: ሲስትሙ ሪፖርት ያደርግላቸዋል:: የሚጠይቁት መረጃ ማግኘቱን ነው:: እሱ ከተሰጣቸው ማንንም ለምን ብለው መጠየቅ ይችላሉ:: ስለዚህ ተጠያቂነቱ ተቆጣጣሪውም ተግባሪውንም ጭምር ነው:: በሚቀጥለው ዓመት ተሳክቶልን ቢጀመር በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ኢንዱስትሪው ቢያንስ በቂ ኢፎርሜሽን ይኖረዋል::
አንዳንድ ቦታ ላይ የሚያጋጥመን ነገር የሚያሳዝን ነው:: የፕሮጀክቶች ስትራክቸር ላይ ዛፍ በቅሎ አይተን ፍርድ ቤት ስንሄድ፤ ዶክመንቱን አይቶ በቂ አይደለም ብሎ ይለቅብናል:: ወይ ደግሞ አምስት ዓመት ያቆይብናል ይሄ ደግሞ ሌላ ኪሳራ ነው:: ዝም ብለን ደግሞ ማባረር አንችልም:: እግድ ካለብን በቃ እንታገዳለን:: ስለዚህ አሁን ኤ.ዲ. አር ከተፈቀደልን እና የኮንስትራክሽን ኦዲት ካደረግን ጥሩ የቁጥጥር ስርአት ይኖረናል:: አሁን አምስት ፕሮጀክት ላይ የጀመርነው የኮንስትራክሽን ኦዲት ስራ አለ:: እሱም አንድ ሌላ የቁጥጥር መንገድ ነው::
አንድ ተቋራጭ ከኳሊቲ አንጻር ስራውን ጨርሻለሁ ብሎ ከወጣ በኋላ በጥቆማ ቢደርሰን:: የኳሊቲ ኦዲት ይደረጋል:: መሳሪያዎች አሉ:: መቆርቆር ሳያስፈልግ የቱ ጋር ነው ብልሽቱ የሚለው በደንብ ሪፖርት ያደርጋል:: ስለዚህ እንደ በፊቱ አበላሽተን አንዱስትሪው ውስጥ የምንኖርበት እድል እየጠበበ ይመጣል::
አዲስ ዘመን፡- ከሌሎች የኮንስትራክሽን ተቆጣጣሪ አካላት ጋር ያላችሁ ተናቦ መስራት ምን ይመስላል?
ኢንጂነር መስፍን፡- ግንኙነታችን የፌደራሉን ስርዓት የጠበቀ ነው:: የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ጋር የሪፖርቲንግ ሲስተም የለንም:: ‹‹የኮንፍሊያንስ›› ኦዲት ስናደርግ ነው የምናገኛቸው:: ለምሳሌ አዋጅ 624 እዚህ ጋር ተጥሷል ካልን ምክረ ሃሳብ ለክብርት ከንቲባ ነው የምንሰጠው:: ከንቲባዋ ደግሞ አስተዳደራዊ እርምጃ ይወስዳሉ:: ግንኙነታችን ይሄ ነው::
ሌላው ደግሞ አዳዲስ ነገሮች በሚመጡበት ጊዜ አብረን እንሰራለን:: ለምሳሌ የስታንዳርድ ክፍተት አለብን ብለው በደብዳቤ ይጠይቁናል በደብዳቤ እንመልሳለን:: ግን የትኛውን ዓለማቀፍ ስታንዳርድ እንደሚጠቀሙ እንግባባለን:: በዚህ አብረን እንሰራለን::
አደጋ ሲደርስ ደግሞ ምርመራው ላይ እኛም እንሳተፋለን:: ሌላው ከኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር እና የመንግስት ፕሮጀክት የኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት ጋር ሆሪዞንታል ግንኙነት አለን:: አንደኛ የወርሃዊ አፈጻጸም ግምገማ ላይ እንገማገማለን:: በፊት የስራ መደበላቀቅ ነበር:: አሁን ግን በአዲሱ አሰራር ለኮንትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አቅም ግንባታ ላይ ነው የሚሰራው:: እኛ ደግሞ የእነሱን ጥናቶች ወደ ኢንዱስትሪው ሕግ ሆኖ ሲገባ እኛ ተቀብለን አተግባበሩን እንከታተላለን::
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ሁሌም የሚያጓጓኝ አንድ ፕሮጀክት አላቸው:: ኮንክሪት በተለመደው መንገድ እየጠፈጠፉ መሄድ ሳይሆን ሲሚንቶ ውድ አይደለ? ሲሚንቶ የሚተካ ፕሮጀክት አላቸው:: አሁን ስለማይጠና እንጂ ሐዋሳ አካባቢ ክላስ ቢ ብሎኬት የማምረት አቅም ያለው እንዲያውም ከክላስ ቢ በላይ አቅም ያለው በተፈጥሮ የተገኘ ግብአት አለ::
እነኚህ ምርምሮች ቢያንስ መሃከለኛ ግንባታዎችን ለመስራት ሲሚንቶን ሊተኩ የሚችሉ ምርምሮች ናቸው:: እነሱ አረጋግጠው ከደረጃ መዳቢዎች ማረጋገጫ እና ፓተንት አግኝተው ወደ ገበያ ሲገባ እኛ ደግሞ ቁጥጥር እናደርጋለን::
እኛ የኳሊቲ ቁጥጥር ስራ ነው የምንሰራው:: ለምሳሌ በቁጥጥር ያገኘነው ብረቱ ሁሉንም ነገር አሟልቶ ቁመቱ ላይ ሀምሳ ሳንቲም ቁመት ይቀሽባሉ:: ያ ሲጠራቀም መዓት ነው የሚሆነው:: ስለዚህ በ‹‹ኮምፎርሚቲ›› ሄዶ የተረጋገጠ እና ሳንፕል ወስደን ስናይ በሁሉም ነገር ዝቅ የሚል አለ:: አሁን በዚህ የጥራት ችግር የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ፋብሪካዎች አሉ::
ችርቻሮም ላይ ሄዶ ያለ ‹‹ሌብል›› ሲሸጡ ያገኘናቸው አሉ:: ሌብል ስላልተደረጉ ታአማኒነት የላቸውም:: ይህ ማለት ለኮንስትራክሽኑ የማይታወቅ መድሃኒት መስጠት ማለት ነው:: ጥራት ቁጥጥር ላይ ጀመርን እንጂ በበቂ ሁኔታ ሰርተናል ማለት አንችልም::
አዲስ ዘመን፡- የአባይ ግድብ በእናንተ በኩል የግንባታ ቁጥጥር ይደረግበታል?
ኢንጂነር መስፍን፡- የአባይ ግድብ የሚሰራው በእኛ እስታንዳርድ ሳይሆን በውጭ ስታንደርድ ነው:: ምክንያቱም የእኛ ሃገር ስታንዳርድ ሲወጣ ታሳቢ አላደረገውም:: እውነት ለመናገር የአባይ ግድብ ጋር አልሄድንም:: ምክንያቱም ግድቡ ላይ ያለው መቆጣጠሪያ በጣም ትልቅ ነው:: ከኛ ይልቅ ጥራቱን የሚቆጣጠሩለት ብዙ አይኖች አሉት::
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን የቃለመጠይቅ ግዜ እናመሰግናለን::
አቶ መስፍን፡- እኔም አመሰግናለሁ::
በምርመራና መልካም አስተዳደር ቡድን
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም