ካዛኪስታን የመጀመሪያውን የኒዩክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ሕዝበ ውሳኔ አካሄደች

ካዛኪስታን የመጀመሪያውን የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ለመገንባት ባቀረበችው ሃሳብ ላይ ዜጎቿ ድምጽ እንዲሰጡበት አድርጋለች ። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ካሳይም ጆማርት ቶካየቭ በካይ የድንጋይ ከሰል ሃይል ማመንጫዎችን ለመተካት የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ የመገንባቱን ሃሳብ አቅርበዋል።

ይህን ተከትሎ ዕሁድ እለት ዜጎች ድምጽ የሰጡበት ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነም የሩሲያው ሮሳቶም የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫውን ይገነባዋል ተብሏል። የካዛኪስታን ካቢኔ ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሚሆነውን የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ኡልከን በተባለ ስፍራ እንዲገነባ ማቀዱንም ነው የዘገበው።

20 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ካዛኪስታን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ቢኖራትም አብዛኛውን የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎቷን የምታሟላው በድንጋይ ከሰል በሚሠሩ የሃይል ማመንጫዎች ነው። ከሩሲያ ኤሌክትሪክ የምትገዛው የማዕከላዊ እስያ ሀገር በካይ ከሆነው ድንጋይ ከሰል ወደታዳሽ ሃይል አማራጮች ፊቷን በማዞር መሆኗን ገልጻለች።

ካዛኪስታን ከዓለማችን ከፍተኛ ዩራኒየም አምራች ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ፕሬዝዳንት ቶካየቭ ከሕዝበ ውሳኔው በፊት “ከዓለም እድገትና ፍላጎት ጋር ራሳችን ለማስተካከል የተሻለ ተፎካካሪ የሚያደርገንን አማራጭ መጠቀም ይኖርብናል” ብለዋል።

የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት አካል የዩራኒየም ሀብቷ ከፍተኛ ቢሆንም ማዕድኑን ሃይል ለማመንጨት በሚያስችል መልኩ የማብላላት አቅም አልገነባችም። በሩሲያው የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ገንቢ ተቋም ሮስታም እንዲገባ ለታቀደው የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ከ10 እስከ 12 ቢሊየን ዶላር ወጪ ሊጠይቅ እንደሚችል ተገምቷል። ተቺዎች ወጪው ከፍተኛ መሆኑንና የሶቪየት የኒዩክሌር ጠባሳ ባልለቀቃት ሀገር የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ መገንባት አሳሳቢ መሆኑን ይናገራሉ።

በፈረንጆቹ 1986 የቾርኖብል የኒዩክሌር ቀውስ ሲከሰት የሶቪየት ህብረት አካል የነበረችው ካዛኪስታን በመቶዎች የሚቆጠሩ የሶቪየት የኒዩክሌር መሣሪያዎች መሞከሪያ ጣቢያዎች የሚገኙባት ናት። የኒዩክሌር መሞከሪያ ሥፍራዎቹ በርካቶችን ለጤና ችግር ዳርገው ነዋሪዎችን ከቀያቸው ማፈናቀላቸውን የሚያወሳው ዘገባው፥ ማንኛውንም ከኒዩክሌር ጋር የተያያዘ ጉዳይ የሚፈሩ ዜጎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑንም ያብራራል ሲል የዘገበው አል ዐይን ነው።

አዲስ ዘመን  መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You