አዲስ አበባ፡- የምግብ ዘይትን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ በመሻሻሉ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የምግብና መጠጥ ምርምርና ልማት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ መኩሪያ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤የምግብ ዘይትን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ተግባር ውጤት እያስገኘ ነው።
የምግብ ዘይት ፍጆታን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት ወደ ሥራ ከገቡት በተጨማሪ በሰፊው የማምረት አቅም ያላቸው አዳዲስ የዘይት ፋብሪካዎች እየተቋቋሙ ነው ያሉት አቶ በቀለ፤ በጥሬ እቃ አቅርቦት፣ ፋብሪካዎቹን በማስፋፋትና በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ የድጋፍ ክትትል እንዲሁም የተለያዩ የአቅም ግንባታ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
እንደ አቶ በቀለ ገለጻ፤ ከሦስትና አራት ዓመት በፊት ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የምግብ ዘይት ፍጆታ ከውጭ የሚገባ ነበር። አሁን ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የምግብ ዘይት መጠን 81 በመቶ ዝቅ እንዲል ማድረግ ተችሏል።
አቶ በቀለ አክለውም፤ በዚህ በጀት ዓመት ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን የምግብ ዘይት ፍጆታ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ ነው ያሉ ሲሆን፤ በሁለትና በሦስት ዓመትም እስከ 80 በመቶ በላይ የሚሆነውን በሀገር ውስጥ ለመተካት እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
በቅባት እህሎች አቅርቦት ዙሪያ የተለያዩ መሻሻሎች በመኖራቸው በቀጣይም የተሻለ ውጤት ይመጣል የሚል ግምት መኖሩንም ነው አቶ በቀለ የገለጹት።
የምግብ ዘይትን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የውጭ ምንዛሪ ወጪ ከማስቀረትና ኢኮኖሚው ከመደገፉም በላይ ለጤና ተስማሚና ጥራት ያለው ምርት ለመጠቀም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።
ምርትና ምርታማነትን መጨመር ብሎም በኢንዱስትሪውና በግብርናው ዘርፎች ተቀናጅቶ መስራት ይገባል ያሉት አቶ በቀለ፤ከዚሁ ጎን ለጎንም የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እንዲሁም ለዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ህብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርት በስፋት እንዲጠቀም ግንዛቤ መውሰድ ተገቢ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለምግብ ዘይት የሚሆኑ የተለያዩ የግብዓት አቅርቦቶች፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና የሥራ ማስኬጃ ካፒታል የምግብ ዘይት ፍጆታን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ተግዳሮት እየሆኑ ካሉ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አቶ በቀለ፤ በተጨማሪም የሰው ኃይል እጥረት የቴክኖሎጂ ውስንነቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ያሉ ውስንነቶች ለማሟላትና በተለይ በቅባት እህሎች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2017 ዓ.ም