የናይል የትብብር ማኅቀፍና ፋይዳዎቹ

ወደሜድትራንያን ባህር እየተገማሸረ የሚነጉደው የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ዓባይ፣ በኢትዮጵያውያንና በመንግስቷ ታታሪነት ጋብ ብሎ ብርሃን መፈንጠቅ ከጀመረ ጥቂት ጊዜ ተቆጥሯል። ይህ ተስፋም ብርሃን ፈንጣቂው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ፤ በመንግስት አነሳሽነትና በሕዝብ ይሁንታ ሲገነባ ቆይቶ ፍጻሜውን ሊያገኝም የወራት ያህል እድሜ ብቻ እንደቀረውም ተነግሯል።

በእርግጥ ዛሬ ላይ ለመድረስ የታለፈበት መንገድ አልጋ በአልጋ ሆኖ እንዳልነበር ይታወቃል። የፈተናው አይነት መልከ ብዙ ነው። የሚመጣበትም አቅጣጫ የተለያየ ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ ሁሉን እንደአመጣጡ በመመከት የብርሃን ጭላንጭል ለማየት ታድላለች። ከግድቡ ጋር ተያይዞ ከአገር አቀፍ ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ መድረክ የነገሰውን ውጥረት በብልሃትና በዲፕሎማሲያዊ አካሔድ በማርገብ ከተራራው ጫፍ ደርሳለች። በገዛ የተፈጥሮ ሀብቷ የበይ ተመልካችነቷ አክትሞ ከገበታው መቋደስን “ሀ” ብላ ጀምራለች።

በቀዳሚነት ውሃ አመንጪዋ አገር ኢትዮጵያን ባይተዋር ስታደርጋት የዘለቀችው ግብጽ፣ ዛሬም ኢትዮጵያ ከገበታው እጇን ስትዘረጋ ማየት እንዳመማት ቀጥሏል። ባገኘችው አጋጣሚና በተለያየ መድረክ ላይ “የናይል ውሃ ታሪካዊና ሕጋዊ ባለቤት እኔ ነኝ” ስትል ከርማለች። ይህን አባባሏን እወቁልኝ በማለት ብቻ ሳትወሰን “ውሃ ይቀነስና ዋ!” ስትልም በመዛት ተጠምዳ ዘልቃለች። ከዚህም ባለፈ ወደጦርነት እንደምትገባ ስትዝት ኖራለች። በተለይም ውዥንብር ስትፈጥርና አቧራ ስታስነሳ ከመኖሯ በተጨማሪ በየአህጉሩ የ“ደግፉኝ” ጥሪ ስታሰማ እዚህ ደርሳለች፤ ኢትዮጵያ ምንም አይነት ብድርና ርዳታ እንዳታገኝ ማድረግ ደግሞ የየዕለት ጥረቷ ሆኖ አብሯት የኖረ ውትወታዋ እንደሆነ የሚታወስ ነው።

ግብጽ፣ በተለይ “ሕጌ ነው!” የምትለው ያፈጀ እና ያረጀውን የ1929 እና የ1959 የናይል ወንዝ ስምምነትን የሙጥኝ ማለቷ የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ የተፋሰሱን አገራት ባይተዋር ያደረገ ስለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህን “አሜን!” ብሎ መቀበል የሰለቻት ኢትዮጵያ፣ ኢፍትሃዊ የሆነውን የተፋሰሱን የውሃ ሀብት አጠቃቀም በፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም ለመለወጥ የአንበሳውን ድርሻ ስትወጣ ቆይታለች። የናይል ወንዝ የትብብር ማኅቀፍም ሕጋዊ ሰነድ ሆኖ ተግባራዊ እንዲሆን የመሪነቱን ሚና ስትወጣ ቆይታለች።

ታዲያ ከሰሞኑ ይህ ሚናዋ ፍሬ አፍርቶና ዲፕሎማሲያዊ አካሄዷ ውጤታማ ሆኖ ጎረቤት አገር ደቡብ ሱዳን ታሪካዊ የባለቤትነት ፊርማዋን በማኖር በአገሯም የትብብር ማኅቀፉን አጽድቃለች። ለመሆኑ የተፋሰሱ አገራት ተፈጥሮ በቸራቸው ሀብት እስካሁን ሊጠቀሙ ያልቻሉት አሳሪ ነገር ምንድን ነው? በቅርቡ ስድስት አገራት በአገራቸው ያጸደቁት የትብብር ማዕቀፍስ ለተፋሰሱ አገራት ያለው ፋይዳ ምንድን ነው? ስንል የየዘርፉን ምሁራን ጠይቀናል።

ከእነዚህም መካከል አንዱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሥራ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ብርሃኑ ደኑ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ የአባይ ውሃ በሱዳንና በግብጽ ስር የነበረ ነው። ምክንያቱም ቀደም ሲል ግብጽን በቅኝ የገዛቻት እንግሊዝ፤ ለዚህ ዋንኛ ተዋናይ የነበረች ናት። ይህችው አገረ እንግሊዝ፣ በ1902 ስምምነት እንዲፈረም ያደረገች ናት።

ስምምነቱም የተካሔደው በኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት አጼ ምኒልክ እና በታላቋ ብሪታንያ መካከል እንደሆነ ጠቅሰው፤ ስምምነቱ ከሚያካትታቸው ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያ የውሃው አመንጭ አገር ሆና ሳለ አንዳች እንዳታደርግ የሚያዝ እንደሆነ አስታውሰዋል። ይህንንም ዘርዘር አድርገው ሲጠቅሱ እንዳሉት፤ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር አስቀድሞ ሳይስማሙ የውሃውን ፍሰት የሚያሳንስ አሊያም ሊያቋርጥ የሚችል አንዳች ተግባር ኢትዮጵያ እንዳታደርግ የሚከለክል ነው፤ “ይሁንና” ይላሉ ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ በዚህ ስምምነት ውስጥ ኢትዮጵያ በወንዙ አትጠቀምበት የሚል ነገር አለመቀመጡን ይገልጻሉ።

ብርሃኑ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በወቅቱ ተካሒዶ የነበረው የውጫሌው ስምምነት በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመጻፉ በሁለቱ ቅጂዎች መካከል ልዩነት ሊፈጠር ችሏል፤ በእንግሊዝኛው ላይ ባለው ውል ኢትዮጵያ ግዴታ እንዳላት አድርገው አቀረቡ። እነሱ የጫኑት ሕግ ሆነ እንጂ ኢትዮጵያ ግን ያንን መቀበል ስላልፈለገች አላጸደቀችውም።

ምሁሩ፣ በኋላ ላይ ደግሞ ግብጽ እና ሱዳን የ1959 ስምምነት መፈራረማቸውን ይጠቅሳሉ። ይህ ስምምነት ኢትዮጵያን ያላካተተ ስምምነት ነበር። ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ መነሻ አገርነቷ ወደጎን ተደርጎ ግብጽ ከወንዙ 55 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ (75 በመቶ) ስትወስድ፣ ሱዳን ደግሞ 18 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሜትር ኪየብ ውሃ (25 በመቶ) ድርሻ መውሰዷን አስታውሰዋል።

እንደ ብርሃኑ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ይሁንና ወንዙ 84 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የሚያመነጨው ከኢትዮጵያ ነው። ይህን ያህል ውሃ የምታመነጭ አገር ኢትዮጵያ፣ በወቅቱ በነበረው ስምምነት ግብጽና ሱዳንን እንጂ አንቺን አይመለከትሽም በሚል ሳትካተት ቀርታለች። ስምምነቱ የሚያሳየው ውሃውን ሁሉ ግብጽ እንድትቆጣጠረው ተደርጎ መቀረጹን ነው።

ሌላው ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተባባሪ ፕሮፌሰር እና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ተፈሪ መኮንን (ዶ/ር) ናቸው። እርሳቸው በበኩላቸው፤ የዓባይ ተፋሰስ ለብዙ ሺ ዓመታት የታችኛዎቹን ተፋሰስ አገራት ተጠቃሚ፤ ሌሎቹ ደግሞ የበዪ ተመልካች አድርጎ የዘለቀ ነው ይላሉ። ኢትዮጵያ በተፋሰሱ ሳትጠቀም የመቆየቷ ምክንያት የመልካም ምድር ገጽታውና የአየር ጸባይ ሁኔታው በመወሰኑ እንደሆነ አስረድተውዋል።

ለዚህ ምክንያታቸውን ሲጠቅሱ፤ ከተፋሰሱ አገራት ኢትዮጵያን ብንወስደው ብዙም ተጨማሪ ውሃ ሳያስፈልጋት ለረጅም ግዜ ቆይታለች። ነገር ግን የአየር ንብረቱ ሁኔታ እየተቀያየረ መምጣት ሲጀምርና የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ የግድ የሚል ነገር መከሰቱን ተፈሪ (ዶ/ር) ይናገራሉ። በመሆኑም ይህ ገፊ ምክንያት ኢትዮጵያ፣ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፓወር ለማመንጨትና ለመስኖ የሚያገለግል ውሃ በእጅጉ እንዳስፈለጋትና ወደስራ እንድትገባ እንዳደረጋት ያመለክታሉ።

እንደ ተፈሪ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ቀደም ባለው ጊዜ ግን ኢትዮጵያ በዝናብ ጥገኛ በሆነ እርሻ ሕዝቧን መመገብ ትችል ነበር። ስለዚህ ይህ በእንዲህ እንዳለ ለረጅም ጊዜ የታችኛዎቹ ተፋሰስ አገራት የእነርሱን ፍላጎት ወይም ጥቅም አስጠብቆ ለመቀጠል የተለያዩ ስምምነቶችን ይጠቀሙ ነበር፤ ለአብነት ያህል አንዱ የ1902 ስምምነት የሚባለው ነው። እንዲሁ 1929 እና 1959ም ተጠቃሽ ስምምነቶች ናቸው። እነዚህ ስምምነቶች ደግሞ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ውሃውን ለታችኞቹ ሁለቱ ተፋሰስ አገራት ብቻ ማለትም ለግብጽና ለሱዳን ሙሉውን ያከፋፈሉ ናቸው። የላይኞቹን የተፋሰሱን አገራት ግን የበይ ተመልካች ያደረጉ ስምምነቶች ናቸው ሲሉ የብርሃኑ (ዶ/ር)ን ሐሳብ ይጋራሉ።

ተፈሪ (ዶ/ር)፣ ለረጅም ጊዜ የቆየን የሕግ ማኅቀፍ ለመቀየር ግን ለብዙ ዓመታት በኢትዮጵያ በኩል ስራ ሲሰራ መቆየቱን ይናገራሉ። ለዚህ ለትብብር ማኅቀፍ ስምምነት ስኬት ለ13 ያህል ዓመታት ድርድር ሲካሔድ እንደነበርም ይታወቃል ይላሉ። ነገር ግን ግብጽና ሱዳን ስለማይቀበሉት እስከ 2004 ድረስ ምንም ማድረግ ሳይቻል መቆየት ግድ ብሎ ነበር። በ2004 ላይ ግን የላይኞቹ ተፋሰስ አገራት የትብብር ማኅቀፉን ፈርመዋል። የትብብር ማኅቀፍ ስምምነት በእያንዳንዱ የተፋሰስ አገር መብታቸውንና ግዴታቸውን በተለይ ደግሞ ውሃውን በተቀናጀ መልኩ ለማልማትና ለቀጣም ትውልድም እንዲጠቅም ታስቦ የተደረገ ነው ይላሉ።

እንደሚታወቀው ግብጽና ሱዳን ፊርማው ሲፈረም እኛ አንፈርምም ብለው ዘልቀዋል የሚሉት የታሪክ ምሁሩ፣ አሁንም ያልፈረሙት እነርሱ ናቸው ብለዋል። ስለዚህ የትብብር ማኅቀፍ ስምምነቱ ከዚህ በፊት የነበረውን ኢ-ፍህትሃዊ የሆነውን ሕግ ለመቀየር፣ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለመጠቀምና በዘለቄታ ተፋሰሱን ለማልማት የሚያስችል ነው ሲሉ አስረድተዋል።

የቀደመው ስምምነት ያገለለው እኛን ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ሌሎቹንም የተፋሰሱን አገራት ጭምር ነው የሚሉት ብርሃኑ (ዶ/ር) ደግሞ በኢትዮጵያ አነሳሽነት የናይል ትብብር ማኅቀፍ በትኩረት ሲሰራበት ቆይቶ ፍሬ ማፍራት ጀምሯል ሲሉ የተፈሪ (ዶ/ር)ን ሐሳብ አጠናክረዋል። በአሁኑ ወቅትም የትብብር ማኅቀፍ ስምምነቱን ሰባቱ አገራት እንደፈረሙ ገልጸው፤ ከእነዚህ አገራት መካከል ከአንዷ በስተቀር ስድስቱ ደግሞ ማጽደቃቸውን አመልክተዋል። ያልፈረሙት አራቱ አገራት ሲሆኑ፣ እንደሚታወቀው አንዷ ግብጽ መሆኗን አስታውሰው፤ ሌላኛዋ ደግሞ ሱዳን ስትሆን፣ ቀሪዎቹ ኤርትራ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ናቸው ብለዋል።

ግብጽ ዋናው ያለመፈረሟ ጉዳይ በዓባይ ወንዝ ላይ ታሪካዊ መብት አለኝ ከሚል ሐሳብ የመነጨ ነው። እኛ በግብጽ በሚመረት ነዳጅ ወይም ከሚወጣ ማዕድን የ”ይገባኛል” ጥያቄ መጠይቅ እንችላለን? ሲሉ ብርሃኑ (ዶ/ር) ይጠይቁና ያንን ማድረግ እስካልቻልን ድረስ ግብጽ በኢትዮጵያ የውሃውን መጠቀም መብት ላይ ጥያቄ ማንሳት አይኖርባትም ሲሉ ለጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ይሰጣሉ።

እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እያለች ያለው የተፈጥሮ ሀብታችንን በሰላም እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንጠቀም ነው። አንዱን ጠቅሞ ሌላው የበይ ተመልካች አድርጎ ያገለለን ስምምነት አንቀበልም ነው። መርሃችንም ውሃውን ለጋራ እድገት እንጠቀም የሚል ነው። ምክንያቱም የዓባይ ውሃን እግዚአብሔር ለሁላችንም የቸራቸረን የተፈጥሮ ሀብት ነው። ስለሆነም የተፋሰሱ አገራት እንደየሁኔታው ሲፈልጉ ኃይል የሚያመነጩበት፣ አሊያም ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚያውሉት፤ ወይም ደግሞ ለመስኖና ለመሰል ልማት የሚጠቀሙበት መብቱ እንዳላቸው ሊዘነጋ አይገባም።

ነገር ግን እስካሁንም ይህን እንዳያደርጉ ችግር ሆኖ የዘለቀው የግብጽ ባፈጀ ሕግ የሙጥኝ ብላ መጣበቋ ነው ይላሉ። ይሁንና ይህ ያፈጀና ያረጀ ስምምነት መጨረሻው ደርሷል። የግብጽ “ማንም አይንካኝ” ትርክት ዛሬ ላይ ማብቃቱ በግልጽ እየታየ መጥቷል ሲሉ ያስረዳሉ።

አሁን ስምምነቱ እዚህ መድረሱ ለተፋሰሱ አገራት ታሪካዊ መፍትሔ የሚያስቀምጥና በሀብታቸው እንዲጠቀሙበት የሚያስችል ነው። ስምምነቱን ቢያንስ ስድስቱ አገራት መፈረማቸውና በአገራቸው ማጽደቅ መቻላቸው ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተፈጥሮ ሀብታቸውን መጠቀም የሚያስችላቸው ነው። በተለይም ልማታቸውን በመተሳሰብ ላይ ተመስርተው እንዲያካሒዱም የሚያግዛቸው ነው። ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማካሔድም የሚረዳቸው ነው። በተለይም ደግሞ እንደ ሕዳሴ አይነት ግድብ መስራት የሚያስችል ነው ሲሉ ብርሃኑ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

እርሳቸው እንዳስረዱት፤ በትብብሩ ማኅቀፉ ከተካተተው ነጥብ አንዱ የተፋሰሱ አገሮች ችግር እንኳ በሚያጋጥማቸው ጊዜ ተወያይተው በጋራ መፍትሔ ማስቀምጥ የሚችሉ መሆናቸውን ነው። ሌላው ቀርቶ በብቸኝነትና ለራስ በማሰብ ብቻ የእኔ ነው ስትል ለቆየችው ግብጽም ሆነ ለሱዳን የትብብር ማኅቀፉ መጽደቅ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በመሆኑም ማኅቀፉ ጸድቆ ሕግ መሆን ጥቅሙ የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የተፋሰሱ አገራት ስኬት ነው። ስምምነቱ የሕዝቦችን የጋራ ጥቅም ማዕከል ባደረገ ሁኔታ የተቀናጀ በመሆኑ የግብጽን ሕገ ወጥ የሆነ ዓላማ የሚያኮላሽ ነው።

ስምምነቱ ሕጋዊ እውቅና አገኘ ማለት ኢትዮጵያ የግብጽን ሕዝብ ውሃ እንዲጠማ አደረገች ማለት አይደለም ያሉት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው በጨለማ ውስጥ ያለውን ሕዝቧን ወደብርሃን የማውጣት ጥረት እንጂ የትኛውንም አገር የመጉዳት ሙከራ አይደለም ብለዋል። ይህን ማድረግ ደግሞ ሕጋዊ የሆነ መብቷ መሆኑን አስምረውበታል። ይህ መብት ደግሞ ሉዓላዊ መብት ነው ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።

ስምምነቱ ዓለም አቀፋዊ እውቅና የሚያሰጥ ነው። ከዚህ በኋላ ለአፍሪካ ኅብረት ይቀርብና ከዚያም ማኅቀፉን የሚከታተል አካል ይኖራል። ስለዚህ ሕጋዊ መብት እንዲኖረው ለአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም ለተባበሩት መንግስታት ሒደቱን ጠብቆ የሚሄድ ይሆናል። ኢትዮጵያ የምትከተለው ሰላማዊ እድገትና ከሌሎች ጋር እኩል የመልማትን መርህ ነው። ይህ ስምምነት ሕግ ለመሆን የሚያስችል ይሁንታ እንዲያገኝ መቃረቡ በኢትዮጵያ በኩል ብዙ ተደክሞበት በመሰራቱ ነው። በተለይም ዲፕሎማሲያዊ አካሔዱ ጠንካራ በመሆኑም ጭምር ነው ብለዋል።

የታሪክ ምሁሩ ተፈሪ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ የትብብር ማኅቀፉ ፋይዳ በጣም ትልቅ ነው። እኛም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለመጀመር የቻልነው ልክ እንደሕግ መሰረት ሆኖንና ስምምነቱን የፈረሙ የተፋሰሱ አገራት እኛን በመደገፋቸው ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ለዘመናት ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ይኑር ስትል ድምጿን ስታስተጋባ የቆየች አገር መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን፣ ሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች ኢትዮጵያን እየደገፉ ያሉትም ከዚህ በመነጨ ነው።

“በእርግጥ” ይላሉ የታሪክ ምሁሩ፣ በዓባይ ውሃ ፖለቲካ ውስጥ ሁለቱ ዋና አገሮች ግብጽና ኢትዮጵያ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ግብጽ ምንም አይነት ውሃ አበርክቶ የላትም። እንዲያውም ሊጠቀስላት የሚችል ነገር ቢኖር አሉታዊ አበርክቶዋ ነው። ምክንያቱም ብዙ ውሃ በግብጽ በረሃ ይባክናል ብለዋል። ኢትዮጵያ ደግሞ የውሃውን 86 በመቶ በላይ አመንጪ አገር እንደሆነች ተናግረው፤ ነገር ግን ደግሞ ዜሮ በመቶ ተጠቃሚ የሆነች አገር ናት ብለዋል። በመድረክ ላይ ሲገናኙ ደግሞ ትልቁ ውዝግብ ያለው በእነዚሁ ሁለት አገራት መካከል ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ስለዚህ በአሁኑ ወቅት የተፋሰሱ አገራት ኢትዮጵያ የተመሰረተችበት መርህ ፍትሃዊነት ላይ እንደመሆኑ እስካሁንም የተፋሰሱ አገራት እየደገፏት ይገኛሉ። ይህ ደግሞ ለአገራችን ኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው ብለዋል።

እንደሚታወቀው ግን ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን አቋም ሲደግፍ አይስተዋልም ያሉት ተፈሪ (ዶ/ር)፣ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ‘እናንተ ዝናብና ሌሎች ወንዞች አሏችሁ’ ከሚል እይታ የመነጨ ሀሳብ መሆኑን አመልክተዋል። ነገር ግን ሌሎቹ እኛን ደግፈው መቆማቸው ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። ውሃውንም በዘላቂነት በተቀናጀ ሁኔታ ለማልማት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

ግብጽ፣ ከዚህ በኋላ ምንም አይነት አማራጭ ስለማይኖራት የስምምነቱ ደጋፊ ልትሆን ይገባል፤ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ስምምነቱ በጣም የሚበጃት በመሆኑ ነው ሲሉ የብርሃኑ (ዶ/ር) ሐሳብ አጠናክረዋል። ምክንያቱም የስምምነት ትብብሩ መርሁ ያደረገው ፍትሃዊነትን በመሆኑ ብታጸድቅ ተጠቃሚ የሚያደርጋት እራሷኑ ነው። ከግጭትና ከእምቢተኝነት ወይም ከትምክኅተኝነት ብትወጣ የሚያዋጣት ራሷኑ እንደሆነ ተፈሪ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ምሁራኑ እንደሚሉት፤ የስምምነቱ ጸድቆ ሕግ መሆን፤ ፋይዳው ግብጽና ሱዳንን ጨምሮ ለሁሉም የተፋሰሱ አገራት ነው። ሁሉም በጋራ በመልማት መርህ ላይ መመስረት ይኖርባቸዋል። ነገር ግን በተናጠል የየራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን የሚሉ ከሆነ ግን በተፈጥሮ የተቸርነው ውሃ በራሱ ሊደርቅ ይችላልና ጥንቃቄ የሚያሻው ነው።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You